ያደግነው/የተነገረን እና ካደግን በኋላ/የምናየው/የምንሰማው ስለአገራችን
የውጭ ዜጎች ይኖራቸዋል ብለን የምናስበው አመለካከት አናት የሚበጠብጥ ነው፡፡ እኛ ጀግና ሕዝቦች፣ የድንቅ ቅርስና የተፈጥሮ ሀብት
ባለቤት፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ኩሩ፣ ምናምን… እንባላለን ብለን ስናስብ ኢትዮጵያን ከጎበኟትም፣ በስም ብቻ ከሚያውቋትም ሰዎች የምንሰማው
(ወይም የአገራችንን ስም ሲሰሙ ወደህሊናቸው የሚመጣው) ድህነታችንን፣ በዚሁ ሳቢያ በየሰዉ አገር ስደት መሰማራታችን፣ በጦርነት
መባላታችንን … ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘወትር የምንዘምርላቸውን ሥነ-ሕንፃዎቻችንን
እንኳ የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው፤ እነርሱን ሊጎበኙ መጥተው ዘግናኝ ድህነታችንን እና የከተማ ስርዓታችንን ስርዓት አልበኝነት ብቻ
በትዝብት እያስታወሱ የሚኖሩ እልፍ ናቸው፡፡
ምናልባት ብዙ የውጭ ዜጎች የሚስማሙበት ሁለት ነገሮች ቢኖሩ የሴቶቻችንን
ቁንጅና እና የቡናችንን አሪፍነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ የኢትዮጵያ እና ሊቢያ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ ‹ኮሜንታተሩ› ስለኢትዮጵያውያን
ደጋፊዎች መልካምነት (ብሎም መልከ መልካምነት) ሲያወራ ስሰማ ምንም እንኳን ለኳስ እምብዛም ብሆንም ከዕለት ዕለት በልቤ እየደደረ
የመጣውን የመልካም ስም ናፍቆት ቆሰቆሰው - “ምናለ ኳሱን በድል ወጥተው ረሀባችን ባይረሳም እንኳ ከጎኑ፣ መልከ መልካምነታችን፤
ልክ እንደሩጫው ኳስ ተጫዋችነታችን ገጽታችን (brand) ቢሆንልን?” እያልኩ የዋህ ምኞት እመኛለሁ!
ኢትዮጵያውያን ለውጭ ዜጎች
ለዚህ ጽሑፍ ማሳያ የሚሆነኝን ነገር ከጉግል ፍለጋ ላይ ነው ይዤ
የመጣሁት፡፡ Ethiopia እና Ethiopian People የሚሉትን ሁለት ቃላቶች በጉግል ምስል ውስጥ አስሳችሁ የምታገኙት የማታውቋትን (ቢያንስ የማታስቧትን) ኢትዮጵያ ቢሆንም
እንኳ - የውጭ ዜጎች የሚያስቧትን ኢትዮጵያ ነው፡፡ ከካርታው ውጪ ራቁታቸውን ያሉ ሰዎች፣ የተራቡ ሰዎች፣ የተጎሳቆሉ መንደሮች
ምስል ነው፡፡ ማነፃፀር ካሻችሁ ደግሞ ብዙም ሳትርቁ የዛሬ ጎረቤታችን የKenyaን እና Kenyan People የጉግል ምስል ሐሰሳ ውጤት
ተመልከቱ - የሚያምሩ የመሬት አቀማመጦች እና የዱር እንስሳት፣ በሚያማምሩ የባሕል ልብሶች ያጌጡ ሕዝቦች ይመጡላችኋል - የዛሬ
ሃምሳ ዓመት ነጻ የወጣችው፣ የኛን ግማሽ ሕዝብ ብቻ ያላት ኬንያ የጉግል ገጽታ የእኛን ያስከነዳል፡፡
በይነመረብ ላይ የተለያዩ ወደኢትዮጵያ ለሚደረጉ ጉዞዎች የተሰጡ
ምክሮችን ሳነብ ይህንኑ ነው የሚነግሩኝ፡፡
ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ገጽታችንን በአግባቡ ስላልገነባን?
የእኛን መልካም ገጽታ ሊያጠፉ የሚፈልጉ ስላሉ? ወይስ፣ እኛ ውስጡ ስላለን የማይታወቀን (የማይሸተን) እውነታ ስለሆነ?
በግሌ በጉግል ምስል ሐሰሳ ላይ የምትመጣዋን ኢትዮጵያ ያክል የከፋን
ነን ብዬ አላስብም፣ ነገር ግን ያንን ያክል ያልከፋን ነን ብዬ ለማለት የሚያስችለኝ በቂ መረጃ የለኝም፡፡ እያደግን ነው እንዳልል፣
ዛሬም ገበሬው ከበሬ ትከሻ ላይ አልወረደም፡፡ እያደግን አይደለም እንዳልል ከተማ ውስጥ ብልጭልጭ አያለሁ፡፡ የብልጭልጩንም ባሰብኩ
ቁጥር የኔ ሰፈር (ፈረንሳይ ለጋሲዮን) እና ቦሌን ሳወዳድር አሁንም ያው የድሮው ይሆንብኛል፡፡ ልጅ እያለሁ ቦሌ የሀብታም ሰፈር
ነው፣ አሁንም የኔ ልጆች ለሚሆኑ የሰፈሮቼ ልጆች ቦሌ የሀብታም ሰፈር ነው፡፡ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን እስከ አራት ኪሎ በቅርብ ጊዜ
(እንበል በሁለት ዐሥርት ዓመታት) የተገነባ ሕንፃ የለም፣ የተሠራ አዲስ መንገድ የለም (አሁን አንዱ ተስተካክሎ እየታደሰ ነው)፣
የነዋሪው ቁጥር ግን ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ በከተማችን ካሉ ቦሌዎች ቁጥር የፈረንሳይ ለጋሲዮኖች ቁጥር ይበልጣል፡፡
ቦሌዎችም ወደላይ መመንደጋቸውን ሌሎቹም ወደታች መቆርቆዛቸውን የሚያስረግጡ እንጂ የማያስረግጡ መረጃዎች የሉኝም፡፡
No comments:
Post a Comment