“ሲፒጄ የሃገራችንን ስም ለማጥፋት ስለሚፈልግ ነው እንጂ፣ በጻፈው ጽሑፍ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም፡፡ 3 ጋዜጠኞች የታሠሩት አሸባሪ ተብለው ነው” ~ አቶ አንተነህ አብርሃም (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ኅብረት /ኢብጋኅ/ ፕሬዚደንት)“[ሲፒጄ] ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ናት ብሏል፡፡ ይሄ ከዚህ በፊትም ሆኖ የማያውቅ ግነት ነው፡፡ የታሰረ የለም።” ~ አቶ ወንደወሰን መኮንን (የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማኅበር /ኢነጋማ/ ሊቀመንበር)“በጻፈው ተፈርዶበት የታሰረ አለ ከተባለ ዶክመንቶችን ማገላበጥ ያስፈልጋል፡፡ ማንም ደግሞ አልታሰረም። ይህ አልሆነም፡፡ ከምላሴ ላይ ፀጉር ይነቀላል፡፡” ~ አቶ ሽመልስ ከማል (የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ)
ከላይ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከወጣ
ቃላቸው ቀንጭቤ ያስነበብኳችሁ አስተያየቶች ውስጥ ምንም ዓይነት መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን አንዱ በመንግሥት ባለሥልጣን
እና የቀደሙት ሁለቱ ደግሞ የጋዜጠኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋዜጠኞች ስም ከተመሠረቱ ማኅበራት ኃላፊዎች የተደመጡ ንግግሮች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ስምንት የጋዜጠኞች ማኅበራት ሲኖሩ ሦስቱ እንደአካባቢና
ጤና ባሉ የተለዩ ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩረው የሚሠሩ ሲሆን ቀሪዎቹ የተለያዩ ጋዜጠኞችን እንወክላለን በሚል የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
ሆኖም በአብዛኛው ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር ጋብቻ በመፈፀም የመንግሥትን (የገዢውን ፓርቲ) ጥቅም በማስጠበቅ ሥራ ላይ ተሰማርተው
እናገኛቸዋለን፡፡ በመሀከላቸው ፉክክር ቢኖር እንኳን ለማኅበራቱ መሪዎች ጥቅም እንጂ በጋዜጠኞች ጥቅም ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡
ማኅበራቱ አንዳንዶቹ የአሳታሚ ድርጅቶች ባለቤቶች በመሆናቸው መንግሥት ድርጅታቸውን እንዳይጣላባቸው ሲሉ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን
በደል በሙሉ አፍ ማጋለጥ አይደፍሩም፡፡ ሌሎቹ አሉን የሚሏቸው አባላት ቢኖሯቸው እንኳን የማኅበሩ አባላት የሚያገኙት ጥቅም የላቸውም፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ጭራሹኑ እራሳቸው ለጋዜጠኞቹ ደኅንነት አደጋ ናቸው፡፡
የአንጋፋው ኢጋማ /ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚደንት/ አቶ
መሠረት አታላይ ለምሳሌ‹የሚሚ ጠረጴዛ› በመባል በሚታወቀውና የኢሕአዴግ ደጋፊ ጋዜጠኞች ብቻ በሚሰየሙበት በዛሚ ኤፍ ኤም
90.7 ላይ በሚቀርበው ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› የውይይት መድረክ ላይ በተደጋጋሚ ይቀርባሉ፡፡ ‹‹ክብ ጠረጴዛው›› በብዛት
በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እና ‹እነእከሌ ይታሰሩ› የሚል ብያኔ የሚበዛበት ሲሆን፣ የጋዜጠኞች ጉዳይ ሲነሳም ተመሳሳይ
ዝንባሌዎች የሚታይበት ነው፡፡ ባጭሩ አቶ መሠረት አታላይ ከሚሚ ስብሃቱ ጋር በመሆን መታሰር ስላለባቸው ጋዜጠኞች ከመወያየት በቀር
ለጋዜጠኞች ወገንተኝት ያሳዩበት አጋጣሚ የለም፡፡
የኢብጋኅ ፕሬዘዳንቱን - አቶ አንተነህን ከዚህ በፊት አግኝቻቸው
የነበረ ሲሆን በነበረን ጫወታ የታዘብኩት ሦስት ነገሮች፤ አንድ - ማኅበሩን እንደግል የቢዝነስ ድርጅታቸው እንደሚቆጥሩት፣ ሁለት
- ራሳቸውን ከኢሕአዴግ አባል ለይተው እንደማያዩ እና ሦስት - የብስለት ደረጃቸው አዋቂነት ላይ ያልደረሰ እንዲያውም የልጃልጅ
ዓይነት መሆኑን ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ሦስተኛውን ነጥብ የቀድሞው የኅብረቱ ፕሬዚደንት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በስደት የሚገኙት
ጋዜጠኛ ደረጄ ሀብተወልድ ‹የአመራር አባላቱን ብስለትም እጠራጠረዋለሁ› በማለት ነበር የገለጹልኝ፡፡
አንደኛውን ነጥቤን ለመደገፍ ያክል፣ አቶ አንተነህ ለምሳሌ ከአቶ
አላሙዲ (ወይም ከድርጅቶቻቸው) ኅብረቱ የተለገሰውን አንድ ሚሊዮን ብር አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹አላሙዲ አንድ ሚሊዮን ብር ሰጠኝ››
ብለው ነው፡፡ ሼክ አላሙዲ (ወይም ድርጅቶቻቸው) ለአቶ አንተነህ የጋዜጠኞች ኅብረት የሰጡት አንድ ሚሊዮን ብር አዋዋሉ የሼኩን
ድርጅቶች የሚያጥላሉ ጽሑፎችን ብቻ የሚጽፈው ጋዜጣ - ሪፖርተር - ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ የሚመራውን ‹ሀፒ› የተሰኘ ማኅበር እንዲቀናቀን ነው፡፡
በእርግጥም ኅብረቱ ተልዕኮውን በመወጣት አባል የሆነበት የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፍዴሬሽኑ (IFJ) አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ
አቶ አንተነህ የሚድሮክን ድርጅቶች በማስጎብኘት ስለጋዜጠኞች ሳያወሯቸው መለሷቸው፡፡ በነገራችን ላይ አቶ አንተነህ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ታሪክ መርሴዲስ የሚነዱ
ብቸኛው ሀብታም ‹‹ጋዜጠኛ›› ናቸው፡፡
አቶ አንተነህ ራሳቸውን ከኢሕአዴግ ለይተው አያዩም እንድል ያሰኘኝ
ደግሞ በታሰሩ ጋዜጠኞች እና በኢትዮጵያ ባለው የሚዲያ አያያዝ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ነው፡፡ እንደእርሳቸው አስተያየት፣ የኢትዮጵያ
ጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው እና ያለመንግሥት ቁጥጥር መረን የሚወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰባቸው የጋዜጠኞች
ኅብረት ፕሬዚደንት ሳይሆን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ያስመስላቸዋል፡፡
አቶ አንተነህ አብርሃም የምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ማኅበራትም
ምክትል ፐሬዘዳንት ናቸው፡፡ ይህ የምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ማኅበር የሚባለውም ከእርሳቸው የኢትዮጵያ ማኅበር የተሻለ ነው ለማለት
የሚያስደፍር ነገር አላገኘሁበትም፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚደንት ሶማልያዊው ኦማር ፋሩክ በሲቪል ማኅበረሰቡ ዘንድ በተለያዩ ማጭበርበሮች
ይታማሉ፤ ሌላው ቀርቶ ዘንድሮ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ጋዜጠኞች መድረክን ለመታደም በተጭበረበረ ፓስፖርት ወደአዲስ
አበባ ሲገቡ ተይዘው
ታስረው እንደነበር አውቃለሁ (እስካሁንም መፈታታቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡) ለዚህም ነው ኢብጋኅ አባል የሆነበትን IFJን
በሙሉ ልብ ማመን የሚሳነኝ፡፡
አቶ ደረጄ ሀብተወልድን ስለኢብጋኅ በጠይቅኳቸው ጊዜ የሰጡኝ መረጃ
ጠቅላላ ይዘት ‹‹የኅብረቱ የመጀመሪያ ሊቀመንበርና መሥራች የነበሩ ሲሆን፣ ኅብረቱ በጥቅመኞች የተያዘና ለኢሕአዴግ ወገንተኛ ነው››
የሚል ነው፡፡ እርሳቸውም የኃላፊነት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በፊት በግል ፈቃዳቸው የለቀቁት በዚሁ ሳቢያ እንደሆነ አጫውተውኛል፡፡
ስለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበራት የገዢው ፓርቲ አሽከርነት ብዙ
ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም - ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም እንዲሉ - ከላይ የተጠቀሰው ላይ አንባቢዎች የየራሳቸውን ትዝብት
እንዲሞሉበት መተዉ የተሻለ ነው፡፡ ከመደምደሜ በፊት ግን አዲስ
የጋዜጠኞች ማኅበር ለመመሥረት በሒደት ላይ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም አዲስ ለሚመሠረተው ማኅበር
ከሌሎቹ መማር የሚችሉበትን ዕድል ለመስጠት የሚያስችል መልዕክት ማስተላለፍ ነው፡፡
እንደመዝጊያ አቶ አንተነህ (የኢብጋኅ ፕሬዚደንት) በመቋቋም ላይ
ስላለው ማኅበር ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሰጡትን አጭር ፖለቲካዊ (የመንግሥት ወኪል የሰጠው የሚመስል) አስተያየት እንመልከት፡-
‹‹…ሊቋቋሙ ይችላሉ መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እነማን ናቸው የሚያቋቁሙት፣ እንዴት ነው የሚቋቋሙት፣ ከጀርባ እነማን አሉ ---- ይሄን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ትልቅ ጉዳይ አይደለም፤ ኖረንበታል፡፡ ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፡፡…››
Comments
Post a Comment