Pages

Thursday, January 9, 2014

“ገዳይ ሲያረፋፍድ፣ ሟች ይገሰግሳል!”

የማላየው የአማርኛ ፊልም የለም፣ ሁሉንም እያየሁ መበሳጨት ልምዴ ነው፡፡ ሁሉንም አይቼ ‹ቂም› እያጠራቀምኩ በአደባባይ የተሳደብኩበትም ጊዜ እንዲሁ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ገዳይ ሲያረፋፍድ›› የሚለውን ፊልም ገና ከመውጣቱ በፊት ወድጄው ነበር፤ በሁለት ምክንያት - አንድም በርዕሱ፣ አንድም በፖስተሩ፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ሆኖ ነው መሰለኝ ፊልሙም ተነስተው የሚያጨበጭቡለት ዓይነት ነው፡፡ ስለፊልሙ ለመጻፍ የተነሳሳሁባቸው ሁለት ምክንያቶች ናቸው፡፡ አንደኛው የሚያበሳጩኝን ፊልሞች ስሳደብ ከርሜ የሚያስደስተኝን ለማሞገስ ምላስ ሲያጥረኝ ራሴን ስለታዘብኩት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በቀደም ዕለት ዮፍታሔ ሲኒማ አካባቢ ሁለት ወጣቶች ሲያወሩ የሰማኋቸው ስላናደደኝ ነው፡፡


አንዱ፤ ‹ገዳይ ሲያረፋፍድ›ን እንዳታየው፣
ሌላው፤ ለምን?
አንዱ፤ ያስጠላል፡፡

እኔ በማላውቃቸው ሰዎች ጣልቃ ገብቼ፤ ‹አይተኸዋል?› አልኩት ‹አንዱ› በማለት የተገለጸውን አንዱን፡፡

አንዱ፤ ‹አላየሁትም፤ ግን ሰዎች ማስታወቂያውን አይተው አስጥንቅቀውኛል…›

እንግዲህ ይታያችሁ፤ እሱ ራሱ እንኳን ማስታወቂያውን አላየውም፡፡ የአገራችንን ፊልሞች እንደኔ ለትዝብት ብቻ ለማየት ላልቆረጠ ሰው፣ እየተጠቋቆሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጥቆማ ግን ከደረጃ በታች ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ሁለቴ ያየሁት ሰውዬ ብመሰክር ይሻላል፡፡ ለልጆቹ የሰጠኋቸው መልስ ‹‹አንደኛ ነው፤ እዩት›› የሚል ነበር፡፡ የቻልኩትን ያክል ለማጋነን ፈልጌ ነበር፡፡ ግን የምሬን ነው፡፡

‹ገዳይ ሲያረፋፍድ› በጣና ኢንተርቴይመንት የቀረበ የናኦድ ለማ ፊልም ነው፤ በፊልሙ ላይ የከተማ ገጽታ ብቻ ሳይሆን የሰለቸናቸውን የከተማ ተዋናዮችንም አናያቸውም፡፡ ፊልሙን ለመውደድ ያበቃኝም አንዱ ይኸው እርምጃው ነው፡፡ ብዙኃኑ የማያውቀውን የከተማ ባለፀጎች ሕይወት ከሚያስኮመኩሙ የፍቅር ኮሜዲዎች በአንዴ ዘሎ ወደገጠር መቼት፡፡ ደፋር ደግሞም የተዋጣለት እርምጃ ነበር፡፡

ፊልሙ ውስጥ እያንዳንዱ ገፀ-ባሕሪ የየራሱን ሚና ድንቅ አድርጎ ከመጫወቱም በተጨማሪ ዳይሬክተሩ ለእያንዳንዷ ዝርዝር እንቅስቃሴ የሰጠበት ሁኔታ ውጤታማ አድርጎታል፡፡ የገጠር ሕይወት እውቀት ለሌለው መማሪያ፣ ላለው ደግሞ ትዝታ ይሰጣል፡፡ የሴቶች እና የወንዶች የገገጠር ቤት፣ መስክ ውስጥ ሚና፤ ማኅበራዊ አኗኗሩ፣ እምነቱ፣ ወዘተርፈው በጥንቃቄ የሚገለጽበት ፊልም ነው፡፡

ጠቅላላ ታሪኩ አገር ባስቸገረ ሽፍታ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ሽፍታው ቅምጥ አለችው፤ ቅምጡን ሊቀላውጥ የከጀለ አንድ ገበሬ ከሽፍታው ጋር የሚፋጠጥበት ታሪክ ነው፡፡ በትወናው ላይ የአገሬው ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ከአነጋገራቸው ጀምሮ መላ አኗኗራቸውን በአንድ ሰዓት ተኩል እጥር፣ ምጥን፣ ጥፍጥ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡

መጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት፤ ገና ፊልሙን ሳላየው በፊት ርዕሱን ወድጄው ነበር፡፡ ርዕሱን ግን የወደድኩት፣ በሌላ እሳቤ ነበር፡፡ ‹ገዳይ ሲያረፋፍድ የቀረ ይመስላል› በሚል የራሴ መደምደሚያ ሰጥቼው፡፡ ነገርዬው ከራሴ ጋር በተገጣጠመ ነው፡፡ የማኅበራዊ አውታር የመንግሥት ተቺ እንደመሆኔ ጓደኞቼ ‹ዶሮ አስረዝመው ሲያስሯት የፈቷት ይመስላል› እያሉ ይቀልዱብኛል፡፡ መንግሥታችን የተበሳ ጨ ዕለት ጉድህ ፈላ እንደማለት፡፡ ልክ በዚያ ስሜት ነበር እኔም ርዕሱን የወደድኩት፤ ፊልሙ ግን በሚከተለው ሀገራዊ ዜማ ላይ ተመስርቶ ነው የተሰየመው፤ እዩትና ትወዱታላችሁ፡፡

‹‹ገዳይ ሲያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል፣
አንዱም የመሞቻው፣ አንዱም መሰደጃው ደርሷል፡፡›› (ግጥሙን ተሳስቼ ሊሆን ይችላል)

2 comments:

  1. ይህን ፊልም እንዳየው እያስገደድከኝ ነው :)

    ReplyDelete
  2. ገዳይ ሲያርፋፍድ ሟች ይገሰግሳል
    ኣንዱም መሰደጃው፥ ኣንዱም ቀኑ ደርሷል።
    የእህል ውሃ ነገር ከፊቴ ከፊቴ፥
    ከኩርባቱ ማዶ ይጠብቃል ሞቴ።

    ReplyDelete