Pages

Sunday, July 22, 2012

የእንቆቅልሹ እንቆቅልሾች


ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ሲሞቱ፣ መኳንንቱ ለሕዝቡ የ‹እምዬ›ን ሞት ለማርዳት ፈርተው ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊስ ዳግማዊው ‹ዳግማዊ-ምኒልክ› ለመሆን በቅተው ይሆን እንዴ? ይህቺን ጽሁፍ እስካሰናዳሁባት ሰዓት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው፣ በጠና ታመዋል እና ሞተዋል የሚሉ ‹‹ታማኝ ምንጮች›› ከየአቅጣጫው እየፈለቁ ነው፡፡ እውነታውን ምሎ የሚናገር ሕዝብ ወይም የሕዝብ አባል ግን የለንም፤ ጉዳዩ በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው፡፡

አሁን፣ አሁን ገዢው ፓርቲ የራሱ ዋሾነት ሳያንሰው የአማራጭ መረጃ ምንጮችን ታማኝነት እስከወዲያኛው ለማድረቅ ሆነ ብሎ የሚጫወተው ‹ጌም› ያለ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ በ‹‹ታማኝ ምንጮች›› በኩል የሐሰት መረጃዎችን ማፍሰስ፣ በጣም እስኪናፈሱ መጠበቅ፣ ወሬዎቹን በከፊል የሚያረጋግጡ መግለጫዎችን መስጠት፣ መጨረሻ ላይ ግን ወሬዎቹ በሙሉ ‹‹ከአሉባልታ›› ያልበለጡ መሆናቸውን አረጋግጦ የዜና ምንጮቹን ተአማኒነት መግደል፡፡ ለኔ፣ መለስ ቢያንስ በቅርቡ ወደቢሯቸው መመለስ ከቻሉ ተናፋሽ ወሬዎችን ለማመን ይሄ የመጨረሻዬ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት የዚህ እንቆቅልሽ እነቆቅልሾች ስለሆኑት ነገሮች ትንሽ ልበል፡፡

እንቆቅልሽ አንድ፡- የግልጽነት ነገር
የገዢው ፓርቲ አባላት እና የመንግስት ባለስልጣናት ከረፈደ በኋላም ቢሆን መለስ መታመማቸውን አምነዋል፡፡ በርግጥ እነሱ በማሕበራዊ አውታሮች እንደሚወራው ሕመማቸውን አላካበዱትም፡፡ ሆኖም መታመማቸውን ለማመን ሁለት ሳምንታት ስለፈጀባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎችም ሆኑ ነቃፊዎች እውነታውን ለማወቅ ሲወዘወዙ ከርመዋል፡፡ መንግስት አትናዱት እያለ በሚመክረን ሕገመንግስቱ አንቀጽ 12 ላይ እንዳስቀመጠው ‹‹የመንግስት ጉዳዮች ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው›› ይላል፡፡ ሆኖም ማንም ከቁብ የቆጠረው ያለ አይመስልም፤ አንደኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን የሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ አልተነገረንም ነበር፣ ሁለተኛ ማን እንደተካቸው ሊነገረን አልተፈቀደም፤ ምክንያቱ እንቆቅልሽ ነው!

እንቆቅልሽ ሁለት፡- የአመኔታ ነገር
የመንግስት ባለስልጣናት ስለመለስ የጤና ሁኔታ መግለጫ ከሰጡ በኋላም ቢሆን የመለስ የጤና ችግር በጣም ከባድ እንደሆነና እንዲያውም ሳይሞቱ እንዳልቀረ መወራቱ ቀጥሏል፡፡ መንግስት ይፋዊ መግለጫ አለመስጠቱ ኅብረተሰቡን ሲያምሰው መክረሙ አንሶ መግለጫ መስጠቱም መፍትሄ ያወረደ አይመስልም፡፡ የመንግስት መግለጫ ፋይዳ የሌለው በምን ምክንያት ነው ብንል ምናልባት ካስለመደን ውሸት የመነጨ ነው ሊባል ይችላል - ታዲያ ለምን ነበር የመንግስት ሰዎች መግለጫውን እንዲነግሩን የፈለግነው፣ የምንፈልገውን ለመስማት? እንቆቅልሽ ነው!

እንቆቅልሽ ሦስት፡- የስርዓት ነገር
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሞቱ ማነው ስልጣናቸውን የሚወስደው ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው መልስ የሚሆነው፣ ‹‹ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ወክለዋቸው እየሰሩ ይቆዩና ፓርላማው በምትካቸው ይመርጣል›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ይሄ መልስ የሚዋጥለት ሰው (ቢያንስ ከተቃዋሚው እና ‹መሃል ሰፋሪ› ነን ከሚሉት ወገን) ማግኘት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ሕገመንግስቱን ካፀደቀ ከ17 ዓመታት በኋላም እንኳን ቢሆን ዘርግቼዋለሁ በሚለው ስርዓት ላይ እምነት ያለው ሕዝብ አላፈራም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ሲሰራ ከረመ? እንቆቅልሽ ነው!

እንቆቅልሽ አራት፡- የአብዮቱ ነገር
በመንግስት እርምጃዎች የመንግስት ሠራተኛው፣ ነጋዴው፣ ባለንብረቱ፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣…ሥራ ያጣው ወይም ደሞዙ የማያኖረው ከተሜ፣ ማዳበሪያ መግዣ ያጣው ወይም የማዳበሪያ እዳውን መክፈያ የቸገረው ገበሬ፣… ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሆነ መንገድ ተቀይሟል፡፡ ይሄ ቅያሜው ደግሞ ከየአቅጣጫው ቀስበቀስ እንደፍም እየጋለ ነበር፣ ይሄ ግለት አንድ ቀን ሲፈነዳ ‹አብዮት› ይባላል፡፡ መለስ ከሞቱ (ወይም ቢሞቱ) የተጀመረው አብዮት ይቀለበሳል ማለት ነው? የአንድ ሰው መሞት የችግሮችን ሁሉ ቁልፍ ይፈታል ማለት ነው? የተበሳጩ ዜጎች አብዮቱን ለመቆስቆስ የሚጠቀሙበትን ወናፍ አስቀምጠው አገር አማን ነው ይሉ ይሆን? እንቆቅልሽ ነው!

እንቆቅልሽ አምስት፡- የኢሕአዴግ ነገር
ላለፉት 21 ዓመታት በመለስ አመራር ስር ያለው ኅወሓት/ኢሕአዴግ ሲያጠፋ በመለስ ሲሳበብ ቆይቷል፡፡ ኅወሓት/ኢሕአዴግን ለቅቀው የወጡት ቡድኖች እና ግለሰቦች ሳይቀሩ የሚወቅሱት መለስን ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ መለስ ባይኖሩበት ኖሮ ወደኢሕአዴግ ተመልሰው መግባት የሚፈልጉ እስኪመስለን ድረስ በጥርጣሬ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ እሺ ‹መለስ› ኢሕአዴግን እንዲህ ጨቁነውትና በራሳቸው መስመር እየጎተቱ አስቸግረውት ከነበር፣ ለኢ-ዴሞክራሲያዊነት ብቻቸውን ዳርገውት ከነበር፣ የኢሕአዴግ ስህተቶች የግለሰቡ ችግሮች እንጂ የፓርቲው ካልነበር፣ አሁን ከሞቱ (ወይም ቢሞቱ) ኢሕአዴግ ነፃ ይወጣ ይሆን? እንቆቅልሽ ነው!

No comments:

Post a Comment