Pages

Friday, June 29, 2012

አምስት የኢትዮጵያ ጠላቶች

From Africa Ave, Addis Ababa, Ethiopia

‹‹ኢትዮጵያ አገሬ›› ከሚለው ሐረግ በቀር በዚህ ዘመን አንገት የሚያስቀና ነገር ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ፣ ፍቅራችን እየጠወለገ፣ ተስፋችን እየመነመነ.. መጥቷል፡፡ መንስኤው እንደውጤቱ እልፍ ነው፡፡ እኔም እንደወትሮዬ አምስት አጀንዳዎችን አንስቼ አንድነታቸውን የማስደመድምበት ምክረ መጣጥፍ ይዤ ቀርቤያለሁ - እነሆ!

1ኛ
‹‹ገበታ ንጉሥ ነው››
ገበታ እንደንጉሥ የሚቆጠርባት ኢትዮጵያ ገበታን ለማግነን ምክንያት አላት፡፡ የዓለም ስልጣኔ እምብርት የሆነችው ግብጽ ጥንታዊና ዘመናዊ ከተሞቿ የተቆረቆሩት በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ ግብጽ ምድሯ ውሃ ባያፈልቅም ከደጇ በሚያልፈው ውሃ ሕዝቦቿን ከረሃብ ለመታደግ ችላለች፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ምሳር ይቆረጣል›› ነውና ተረቱ ኢትዮጵያ ግን የረሃብ ምሳሌ ነች፡፡ ከሰማይ ዝናብ ዘነበ/አልዘነበ በሚል የምግብ ዋስትናዋን በሚትዮሮሎጂ ዕድል ላይ የጣለችው ኢትዮጵያ የረሃብን ነገር ታውቀዋለች እና ‹‹ገበታ ንጉሥ ነው›› እያለች ብትተርት አይፈረድባትም - ረሃብ አንደኛ ጠላቷ ነውና፡፡

2ኛ
‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም››
ኢትዮጵያውያን አማኞች ናቸው፡፡ ክርስትና ከመፈጠሩ በፊት አክሱም ሃውልትን ያስቆማቸው እምነታቸው ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በፈጣሪ ፈቃድ እንጂ በሰው ጉልበት ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡ ይህንን በርካታ ምሳሌና የኑሮ ዘይቤያቸው ይመሰክራል፡፡ እርግጥ በዘመናዊዋ እና በቀድሞዋ ኢትዮጵያ መካከል ልዩነት ይኖራል ብሎ መጠርጠር መልካም ነው፡፡ እንደምሳሌም ጥንታዊዎቹ የአክሱም ሐውልትን ያቆሙት በትግል እንጂ በዕድል አይደለም፤ ሌላ ምሳሌ፣ ቀደምት የላሊበላ ታሪክ ጸሃፊዎች ላሊበላ የታነፀው እነዚህ ታሪክ ጸሃፊዎች የኢትዮጵያውያንን የእጅ ሥራ ‹‹ታድለው›› እንጂ ‹‹ታግለው›› ያገኙት ስላልመሰላቸው ከነዚያኞቹ እነዚህኞቹ ያንሳሉ - እምነትን በመምረጣቸው ብቻ ሳይሆን መታደልን ቁጭ ብለው በመጠበቃቸው፡፡

‹‹ጠንቋይ መቀለብ›› የተሰኘች አባባል አለች፤ ‹‹ማወቅን›› ትወክላለች፡፡ በአገራችን ‹አዋቂ› የሚለው ቃል ‹ጠንቋይ› ከሚለው እኩል ያገለግላል፡፡ የእጅ ሥራ ባለሙያዎች ጥሩ ስም የላቸውም - ‹‹ቡዳ›› ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ በሥራው ግን በቶሎ የተሳካለት ሰው/ነጋዴ ‹‹ምን የተለየ ሥራ ሰርቶ ነው?›› ብሎ ሊማርበት ከሚፈልገው ይልቅ ‹‹አስጠንቁሎ/አስደግሞ ነው›› እያለ የሚያማው ተመልካች ይበዛል፡፡ ከሥራ ይልቅ ምትሃት ዋጋ አለው፡፡ ድህነቱንም ሮጦ ያመለጠ ሰው ግፋ ቢል ‹‹ፈጣሪ ረዳው›› ይባል እንደሆን እንጂ ‹‹ለፍቶ አገኘ›› የሚባልበት ጊዜ እምብዛም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች - ዜጎቿ ለስኬት አቋራጭ መንገድ ያስሳሉ - አምልኮን ወይም እምነትን የሙጢኝ ብለው ‹‹የቆጡን ሲጠብቁ፣ የብብታቸው››ን ያጣሉ፡፡

3ኛ
‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ››
ኢትዮጵያውያን ንግሥና እና ሰማይን የምናነፃፅር ብቸኛ ዓለመኞች ነን፡፡ ንጉሥ ካ’ሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረዱ በቃ - አበቃ ብለን እጅና እግራችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ሰዎች ነን፣ ጭቆና ከንጉሥ ከመጣ አሜን ብሎ የሚሸከም ጫንቃ ያለን ፍጡሮች ነን - በልምድ፡፡ ይሄ ልምድ ከንጉሥ ጀምሮ እስከታችኛው እርከን ይወርዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የሥራ ቦታ አለቆቻችን ሲሳሳቱ ደፍረን አናርማቸውም፣ ሲጨቁኑን አንታገላቸውም፣ መስመር ሲስቱ አንመልሳቸውም - ምክንያቱም ንጉሥ አይከሰስም፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ አምባገነኖችን ፈጥረናል፣ ገና እንፈጥራለን - ንጉሥ ባለመክሰስ፡፡

4ኛ
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል››
የጉበኝነት፣ ሙሰኝነት፣ በስልጣን መባለግ ወይም መበልፀግ በአገራችን ዕድሜው ስንት እንደሆነ ለማወቅ ይሄ ተረት መተረት የጀመረበትን ጊዜ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሹመኞች ሊያገለግሉት የተሾሙለትን ሕዝብ መበዝበዝ እንደመብት ይቆጥሩታል፡፡ ጥንት ጀምሮ እስከዛሬ የዘለቀው የሹመኛ የመብላት ‹‹መብት›› ተሹሞ የማይበላውን፣ በተሾመበት መስክ ባይተዋር የሚያደርግ ነው፡፡ ተሹሞ ባለመብላቱ እንደሚቆጭ እየተነገረው አለመብላትን የሚመርጥ ምናልባትም ለሌሎች ሹመኞች ስለማይመች የሚወገድበት መንገድ ይመቻችለታል፤ ባልሰራው ወንጀል ይከሰሳል፣ የበይዎቹን ገፈት ይቀምሳል፡፡ ሹመኞች ሲበሉ የሚመለከቱ ሰዎች ‹‹ባለጊዜ›› ብለው ያልፏቸው እንደሆን እንጂ እንደወንጀለኛ አይሷቸውም፣ አይወቅሷቸውም፣ አያጋልጧቸውም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹን ሹመኞች የሚያባልጓቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ፣ ዛሬ ብዙዎች ሹመትን የሚመኙት ለመብላት የሆነው - ሌላው ጠላታችን፡፡

5ኛ
‹‹እል’ፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል››
የተማረው፣ ያልተማረው፣ ድሃው፣ ሃብታሙ፣ ከተሜው፣ ገጠሬው - ሁሉም አንድ ሕልም አለው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ አንዱ አገር መኮብለል፡፡ እርግጥ ከላይ ተረቱ ‹‹ዛሬን ሲያልፉ ነገ እልፍ ይገኛል›› የሚል ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ችሎ ማሳለፍ፣ ‹ታግሎ› ሳይሆን ቅድም እንደታዘብነው ‹ታግሶ› ማሳለፍ ላይ ነው ዓላማው፡፡ ከዚያም በከፋ ግን ኢትዮጵያውያን አልፎ መሄድ እየተማርን ነው፡፡ ከ5 ዓሥርት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ የወጡ ሰዎች ስም ዝርዝር በጋዜጣ ይታተምባት የነበረችው አገር ዛሬ በፈላሾቿ (diasporas) ቁጥር አንድ አገር መመስረት የምትችል ሆናለች፡፡ ምክንያቱም ዜጎቿ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህም አገራችን እልፍ የሚሰሩ ክንዶች፣ እልፍ የሚፈጥሩ ጭንቅላቶችን አጥታለች - ስደት ጠላቷን እየተከተለች፡፡

ድምር ውጤቱ?
ለጠላቶቻችን ማጣቀሻነት ተረትና ምሳሌዎቻችን የተጠቀምኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ተረትና ምሳሌ የብዙዎች አስተሳሰብ ብዙዎችን በሚያግባባ መንገድ የሚገለፅበት ቋንቋዊ ዘይቤ ነው፡፡ እነዚህ ተረትና ምሳሌ ስር የሰደዱ ባሕልና አስተሳሰባችንን (mentality) ይነግሩናል፡፡ ሁሉም ታዲያ የምስራች የላቸውም - እዚህ እንደጠቀስኳቸው ያሉቱ መርዶ ናቸው፡፡ መርዶዎቻችንን ደምረን ስንመለከታቸው ድምራቸው አንድ ነው፡፡ ሁሉም የተዘረዘሩት የዕውቀት ማነስ ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህንን መቅረፍ ደግሞ የሚቻለው በትምህርት ነው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም በማዳረስ፡፡

No comments:

Post a Comment