ኅወሓትን ለ10
ዓመታት የመሩት አቦይ ስብሃት፣ የመሪነቱን ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈቃዳቸው ካስረከቡ 23 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ለአዲስጉዳይ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ፣ አቦይ ስብሃት ‹‹የኅወሓትም ሆነ የኢሕአዴግ ሕገ-ደንብ አንድ ኃላፊ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን
ዓመት አይገድብም፡፡…›› ብለው ተናግረዋል፡፡ እውነት ነው፤ እንኳን የፓርቲው የአገሪቱ ሕገ-መንግስትም ለ‹‹ትዕምርትነት››
የሚቀመጠውን ፕሬዚደንት የስልጣን ዘመን ሲገድብ፣ የክልል ፓርላማን እስከመበተን ስልጣን የተቸረውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመነ መንግስት
አይወስነውም፡፡
‹‹የተመቻቸ ጊዜ ልጠብቅ ካልኩ፥ 50 ዓመትም አይበቃኝ፤›› ዶ/ር
እሌኒ - ለሪፖርተር ጋዜጣ፡፡
ኢሕአዴግ እንዲህ
ዓይነት ነገር ይወዳል፡፡ ለምሳሌ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ላይ ‹የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል› ብሎ ይጽፍና
‹መገንጠል›ን ምን አመጣው ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀር እና በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩት የመለያየት መብት እንዳላቸው
ስንነግራቸው ነው›› ብሎ ይከራከራል፡፡ በዚህ ‹‹ሕገ-መንግስታዊ አተረጓጎም›› ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመነ መንግስት አለመገደብን
የምመለከተው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ
(ወይም የኢሕአዴግ) የስልጣን ዘመን አለመገደቡ፣ አንድ፤ አቦይ ስብሃት እንዳሉት ‹‹…ፕሮግራሙን ማዕከል አድርጎ የጋራ አመራርን እስካረጋገጠ ድረስ…›› ችግር የለውም ለማለት ይመስላል፣ ሁለት፤
የስልጣን ዘመኑ ሳይገደብ በገዛ ፍቃዱ ይለቃል የሚል ተስፋ ይዞ ይሆናል - ልክ እንደመገንጠል/አለመገንጠሉ፡፡ ሦስት፤ የፓርቲው
ሊቀመንበር ቁጭ ባሉበት የሊቀመንበሩ የሥልጣን ዘመን ይወሰን የሚል ጥያቄ ማንሳት ለአባላቱ አስፈርቷቸው ይሆናል፡፡
አንድ ሰው
ለረዥም ጊዜ አንድ ቦታ ላይ ሲቀመጥ የቦታውን ኃላፊነቶች በአግባቡ እያወቀ እና የካበተ ልምድ እያፈራ ይመጣል፤ ታዲያ ለምን የለመደውን
ሰው አስነስቶ አዲስ መተካት ያስፈልጋል?
ስልጣን በተለይም
ትላልቅ ተቋማትን እና ሃገርን የመምራት ስልጣን በአንድ ሰው ወሳኝነት ላይ (በተለይም እንደኛ አገር ባለው ተሞክሮ በፍፁማዊ ሁኔታ
በአንድ ሰው ወሳኝነት ላይ) ጥገኛ ሊሆን ቢችልም የቡድን ሥራ ውጤት ነው፡፡ በአመራር ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ኃላፊነት ነገሮች
መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ ብቻ ነው እንጂ ሌላው ሌላው የብዙዎች ድምር ፍሬ ነው፡፡
ይህንን በቀላል
ምሳሌ ብናየው እንዲህ ይሆናል፡-
አንድ ሹፌር
መኪና ሲነዳ (መሪ፤ ሃገር ሲመራ) እንደማለት ነው፡፡ ሹፌሩ (መሪው) መኪናውን (አገሪቱን) የሚፈለግበት ቦታ ለማድረስ መጀመሪያ
በአግባቡ የተጠረገ ጥርጊያ መንገድ (ፖሊሲ፣ ስርዓት) ያስፈልገዋል፣ ረዳት (አማካሪ) ያስፈልገዋል፡፡ መኪናው ጥሩ ኢንጂን (ተቋማት)
እና ነዳጅ (ምሁራን) ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከተሟሉ፤ አንደኛ ሹፌሩ ከተጠረገለት መንገድ ውጪ አይሄድም፣ ሁለተኛ
ተሳፋሪዎቹን (ሕዝቦችን) የሚፈለገው ቦታ ለማድረስ ብዙ ጥበብ አይጠበቅበትም፡፡ ነገር ግን ያለ እረፍት ለረዥም ሰዓታት ከነዳ
(ለረዥም ዓመታት ከመራ) መሃል ላይ በድካም መዛሉና መስመር መሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሹፌሩ ተቀያሪ ያስፈልገዋል፣ ኢንጂኑ
ሲያረጅ ‹ሰርቪስ› ይደረጋል፣ ነዳጁ ሲያልቅ ይሞላል/ይተካል፣ ረዳቱም ሲደክም ይቀየራል፡፡ በዚህ አካሄድ ተቀያሪው ያንኑ ጥርጊያ
ይዞ በአዲስ ጉልበት፣ በአልተሞከረ ዘዴ፣ በመስቀለኛ መንገዶች ሳይደናገር ወደመዳረሻው ተከታዮቹን ይዞ፣ መኪናውን ለአደጋ ሳያጋልጥ
ይዘልቃል፡፡
እንግዲህ መሪዎች
መተካት ያለባቸው ከስትራፖ (fatigue) እንዲተርፉ እና ሌሎች የሚታያቸውን አዲስ መንገድ ወይም አካሄድ እንዲከተሉ ነው፡፡ በእኛ
አገር ‹‹…የተጀመረው ልማት እንዳይደናቀፍ…›› የሚለው ምክንያት
ስልጣንን ላለመልቀቅ እንደምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ የተስተካከለ ስርዓቱ አለ ከተባለ በተተኪው አካል የተጀመረው ልማት የማይጨረስበት
ምክንያት ምንድን ነው? ተቋማት በአንድ ባለ ሙሉ ስልጣን መሪዎች (እነ መብራት (ወይም ‹‹መጥፋት››) ኃይልን ምሳሌ መውሰድ ይቻላል)
ብቻ ዘላለም ከተመሩ፣ አገር በአንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ በአንድ ፓርቲ ብቻ ከተመራች ለረዥም ጊዜ (ለምሳሌ ለ21 ዓመታት) እየተፈጠሩ
መፍትሄ ያጡ ችግሮችን በአዲስ መልኩ ተመልክቶ፣ በአዲስ መፍትሄ እንዴት መፍታት ይቻላል?
ከሰሞኑ በኢሕአዴግ
ቤት እና ጎረቤት ባልተሞከረ መልኩ ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን ከምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ መልቀቃቸው
በጣም አነጋጋሪ የሆነው ከኢሕአዴግ በወዳጅነት የሚሠራ ወይም አባላቱ ስልጣን በመልቀቅ ስለማይታወቁ ነው፡፡ ኢሕአዴጎቹ ምናልባትም
‹‹…የተመቻቸ ጊዜ…›› እየጠበቁ ይሆን የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ
ያቃጭልብኝ ነበር፡፡
‹‹…ምናልባት የጀመሩት ‹ልማት› የሚያልቅበትን - የተመቻቸ ጊዜ? ምናልባት
የተዘጋጀ ተተኪ የተፈጠረ የሚመስላቸው - የተመቻቸ ጊዜ? ምናልባት የሆነ የማናውቀው የተመቻቸ ጊዜ ይመጣ ይሆን?...›› እያሉ እየጠበቁ ይሆናል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ‹ያ የተመቻቸ
ጊዜ› መቼም እንደማይመጣ እያወቅኩት፡፡ ታዲያ ዶ/ር እሌኒ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ
ለአለቆቻቸው ለነ አቶ መለስ ዜናዊም ትምህርት ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡
Comments
Post a Comment