Pages

Friday, January 13, 2012

ሰማንያ ሚሊዮን እስከምንደርስ እንታገላለን


አንድነታችንን የሚፈሩ ሰዎች ብቻ ናቸው የተለያየን እንደሆንን እና የተለያየ ፍላጎት እንዳለን የሚነግሩን፡፡ በፊት ኢትዮጵያውያን ነበርን አሁን ትግሬ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሞ…… አድርገውናል፡፡ አሁን ክርስቲያን፣ እስላም… አድርገውናል፡፡ አሁን አባል፣ ደጋፊ ወይም አሸባሪ ብለውናል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰሜንም፣ ከደቡብም፣ ከምስራቅም፣ ከምዕራብም፣ ከመሃል አገርም ብንመጣ አንድነታችን በምቾታችን ብቻ ሳይሆን በችግራችንም ሳይቀር ይገለፃል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ድሮም ሆነ ዛሬ ችግራችን እጦት ነው - የምግብ እጦት፣ የመረጃ ወይም የእውቀት እጦት፣ የነፃነት እጦት ነው፡፡

አንድነታችን እውነት ቢሆንም እኛን የመበታተኑ ትግል ግን አልተሳካም ማለት አይቻልም፡፡ ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን እንደጌጥ አንጠልጥለነው እንድንዞር እያደረገን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ምንም እንኳን በየጓዳችን ሁላችንም በመንግስታችን ሥራ ስንብሰከሰክ ብንቆይም ከጎናችን የተቀመጠውን ሰው ማንነት በርግጠኝነት መናገር እየፈራን፣ እሱ/እሷም እንደኛ በውስጧ የተማረረች መሆኗን ከማሰብ ይልቅ ልዩነታችንን በመጠርጠር ብቻ በዝምታ ታፍነን እና በስጋት ተበታትነን፤ ኢሕአዴግ በጣት በሚቆጠሩ ታማኝ ደጋፊዎቹ ብቻ እየታገዘ አገሪቷን እና ዜጎቿን እንደልብ እንዲያሾራቸው ረድተነዋል፡፡

በምርጫ 97 ወቅት፣ የኢሕአዴግ ከፋፍለህ ግዛ ውጤትን ማስተዋል የታደለ አንድ ወዳጄ የቋጠራት ስንኝ ሁኔታውን ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡

ገበሬውማ መሬት አዘጋጅቶ÷ ዘሩን ዘርቶ ሄደ
እንደሚያድግለትም ተስፋ አዝሎ ነጎደ
ተመላልሶም አየ÷ አረሙን ነቀለ
አዝመራው አሽቶ÷ በርግጥም በቀለ
ማሳውን ጠባቂ÷ ቢያዘጋጅም ቅሉ
ዝንጀሮዎች የሉም
ወፎች አልነበሩም
እርስ በርስ ሆነና ነገሩ
ገበሬን ማክሰሩ
በቆሎ ስንዴውን
ማሽላ ዘንጋዳን
ባቄላ አተርን
ይጠረጥር ጀመር
አንደኛው ሌላውን፡፡
ቢኒያም ገብረየስ፤ 1997 (ያልታተመ)

እኔ ግን እላለሁ፤ የኢሕአዴግ ከፋፍለህ ግዛ እያከተመ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የተበለሻሸ የአስተዳደር ዘመን ከላይ የከፋፈለን ቢመስልም÷ ከውስጥ ግን አንድ እያደረገን ነው፡፡ አሁን ሁላችንም በልባችን የምናሰላስለው ስለኑሯችን፣ ስለነፃነታችን እና ስለዜግነት ድርሻችን ነው፡፡ ስማችን ቢለያይም ሐሳባችንና ምኞታችን ግን አንድ ነው - ከኢሕአዴግ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን ማየት፡፡

ገዢዎቻችን የተሸወዱት ከአንድነታችን በላይ ልዩነታችን የሚያስደስተን የመሰላቸው ዕለት ነው፡፡ ልዩነታችንን እናከብራለን፤ ከአንድነታችን ግን አይበልጥብንም፡፡ ቢበልጥብን ኖሮ አብረን መኖር ባላስፈለገን!

ደርግ ‹‹አንድ ጠብ-መንጃና አንድ ሰው እስኪቀር እንታገላለን›› እያለ ይፎክር ነበር፡፡ ይሄ ዓይነቱ አባባል የተስፋ ቆራጦች ነው፡፡ ገና ሙሉ እያሉ እንደሚጎድሉ የሚያስቡ ሰዎች አባባል ነው፡፡ እኛ ቆራጦች እንጂ ተስፋ ቆራጦች አይደለንም፡፡ የእኛ ፖለቲካ የኑሮ ፖለቲካ ነው፣ የእኛ ኢኮኖሚ የኑሮ ኢኮኖሚ ነው፣ የእኛ ጥያቄ የእኩል ዜግነት ጥያቄ ነው፣ የእኛ ጥያቄ የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው፡፡ ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ይህንን ማግኘት ያስፈልገዋል - ምናልባት ደፍረን ጥያቄውን ያነሳነው ጥቂቶች ብንሆንም፣ ጥያቄው ግን የሁላችንም ነው፡፡ ስለዚህ ሰማኒያ ሚሊዮኖች ጥያቄውን እስኪያነሱትና መልስ እስክናገኝ ድረስ እንታገላለን፡፡

1 comment:

  1. Thank you Stay blessed. Will expect more and more.

    ReplyDelete