Pages

Thursday, November 10, 2011

“Every nation deserves its government” - ኦቶ ቮን ቢስማርክ

ሠላም ሰፍኗል፡፡ ሠላም የሚያሰፍን ግን አንዳችም ነገር የለም፡፡ የኑሮ ዋጋ ከሕይወት ዋጋ በልጧል፣ በቂ ቀርቶ ግማሽ ነፃነት የለም፤ ሕዝቡ ግን አይበሳጭም ወይም ብስጭቱን አፍኖ ተቀምጧል፡፡ ‹‹የባሰ አታምጣ›› እያለ የምድራዊውን ገዢ በደል ‹‹በሰማያዊው›› ላይ ያሳብባል (‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› መባሉ ተዘንግቷል!) - የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን መንግስት እንደሚጠላው እና እንደተማረረበት ቢታወቅም - ‹በቃኸኝ› ሊለው ግን አልፈለገም ወይም አልደፈረም፡፡

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ኢትዮጵያውያን ለአብዮት የሚያበቃ ብስጭት ላይ ደርሰዋል? ባሉት ጽሁፋቸው ላይ ‹‹ሕዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ የመነሳት ዕድሉ በብዙሐኑ ስነልቦናዊ ዝግጅት ላይ የተመረኮዘ ነው›› በማለት የስነልቡናው ዝግጅት አናሳ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመጽ፣ በቅርቡ ይቀሰቀሳል ብሎ መጠበቅ እንደማያዋጣ አመልክተዋል፡፡

ሕዝባዊ አመጽ ያስጠላል፡፡ ሁሉም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ይወዳል፡፡ ነገር ግን ከጊዜያዊ ሰላም ይልቅ ዘላቂ ለውጥ ይበልጥ አስፈላጊ ነው፡፡ የማንበላ መብላት፣ የታረዝን መልበስ፣ የታሰርን መፈታት ያምረናል፡፡ እንዳምና ካቻምናው ሁሉ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ጋር ተጣብቀነ በምግብ ራስን ስለመቻል እና የነፃነት አየር ስለመተንፈስ ማውራት ያሰለቻል፤ እንደሌሎች ሃገራት ስለዓለም ዓቀፍ ገበያ፣ ስለኅዋ ሳይንስ እና ስለሁለተኛ ፍላጎቶቻችን የማውራት ወግ ያምረናል፡፡ አምሮታችንን ለመወጣት ደግሞ እንቅፋት ከፊት ለፊታችን ተደቅኖ ይታየናል - ለውጡ ባይመጣስ ብለን እንፈራለን ወይም ደግሞ የለውጥ ሒደቱን ከወዲሁ ስናስበው ይደክመናል፡፡
"ተፈፅሞ እስኪታይ ድረስ ሁሉም ነገር የማይቻል ይመስላል" ያሉት ኔልሰን ማንዴላ ይህንን የኛን ሁኔታ የሚመስል ሲገጥማቸው ይመስለኛል - የምንፈልገው ለውጥ ባይመጣስ ብሎ መስጋት፡፡ ሌላው ራሳቸው ኔልሰን ማንዴላ ‹‹ጉዞ ወደነፃነት›› በሚል በሰየሙት መፅሃፋቸው ላይ ትግሉ ቀላል ወይም አጭር ይሆናል ብዬ ጠብቄ አላውቅምባሉት አባባል መመሰል ይገባናል፡፡ በአንዴ የሚፈነዳ አብዮት ጉዳይ መጨረሻው፣ ሁላችንም እንደምንፈራው ‹‹አምባገነን አውርዶ፤ አምባገነን ማውጣት ነው፡፡›› የምንፈልገውን ዓይነት ለውጥ የምናመጣው በምኞት እና በትዕግስት ብቻ ሳይሆን በላብና በደምም ጭምር ተናውጠን ስናበቃ ነው፡፡ (‹‹ለውጥ ያለ ነውጥ አይመጣም›› እንዳለው ዲያቆን)

በመሰረቱ መንግስታዊ ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ጉልበታቸውን የሚያገኙት ከሕዝቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም አምባገነን መንግስታት ሕዝባቸውን ለማባበል እና ለማታለል የሚታገሉት፡፡ ሕዝቡ ግን ያንን ኃይል እንደአሰጣጡ መንሳት እንደሚችል የሚዘነጋበት ተደጋጋሚ ዕድል አለ፡፡ ለዚህም ነው መንግስታት ኃያል እንደመሰሉ ለበርካታ አሥርት ዓመታት መግዛት የሚችሉት፤ ኃያል እንደመሰሉ ይገዛሉ እንጂ ኃያል እንደመሰሉ የሞቱ አምባገነኖች ግን እንደሌሉ ከታሪክ መማር ቀላል ነው፡፡

በሃገራችን ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ ታምመው የሞቱት ዳግማዊ ምኒልክ ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል (ንግስት ዘውዲቱ የነበራቸው ሚና ወሳኝ ስላልነበር) በ20ኛው ክፍለዘመን (በዋነኝነት) ያየናቸው ሦስት ገዢዎችን ብቻ ነው፡፡ ሁለቱ በሕዝብ ኃይል ሲሸኙ፣ ቀሪውም ይህንኑ እየጠበቀ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን የኢትዮጵያውያን ብስጭት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት መንግስት ቀሪውን ለመለወጥ በቂ አይደለም፡፡

በአንድ መንግስታዊ አስተዳደር ስር ያሉ ሕዝቦች በቂ የሥራ ወይም የሥራ ፈጠራ ዕድል ካልተመቻቸላቸው፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ በነፃነት የመናገርና የፈለጉትን ድርጅታዊ ወይም ግለሰባዊ አቋም መያዝ እና ማራመድ ካልቻሉ ከበላያቸው ያለው አምባገነናዊ አስተዳደር ነው ማለት ነው፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት “True individual freedom cannot exist without economic security and independence. People who are hungry and out of a job are the stuff of which dictatorships are made.”  ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ አምባገነንነት የሚገነባው በሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ነው - ነው አባባሉ፡፡ ሙሉ ነፃነት እና ዴሞክራሲ መጎናፀፍ የቻሉ ሕዝቦች ድሃ የሆኑበት ታሪክ የለም፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የተራበ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል›› ብለው ነበር፡፡ አባባሉ ፈረንሳዊው ደራሲ ቪክቶር ሁጎ “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right” ካለው ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሁለቱም ሰዎች ንግግራቸው አንድ ዓይነት ነጋሪት ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅታዊ ሁኔታ ግን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ተቃራኒ ነው፡፡ ከመቸገርና ከመጨቆን በላይ እምቢ ልንለው የሚገባን ምን ነገር አለ?

ይህንን ስል ለነውጥ እየወተወትኩ ሊመስል ይችላል፤ ነውጥ እና ለውጥ ይለያያሉ፡፡ ነገር ግን፤ ምንም እንኳን እኔ እየወተወትኩ ያለሁት ለለውጥ ቢሆንም ለውጥ የተወሰነ ነውጥ ማስተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ምንም ቢያስከትል ምን ለውጥ ደግሞ ያስፈልገናል፡፡ ጥያቄው የፖለቲካ አይደለም፤ የመኖር ነው፡፡ ግዴታ መሳሪያ ታጥቀን መሸፈት፣ ድንጋይ ወርውረን የሕዝብ ንብረት መሰባበር ወይም አገር ጥለን መኮብለል ላይጠበቅብንም ይችላል፡፡

ነገር ግን ‹‹እምቢ መብቴን አሳልፌ አልሰጥም፣ እምቢ ጭቆናን አልቀበልም፣ እምቢ መራብ አይገባኝም›› ማለት አለብን፡፡ ካላልን ‹‹እሺ ይደረግልኝ፤ ይገባኛል›› ብለን የተጫነብንን አምባገነናዊ ስርዓት እንደተቀበልን ይቆጠራል፡፡ እኔ በግሌ በዚህ መንግስት እና በስርዓቱ ላይ ያለኝን ተቃውሞ በሚያስፈራው ክበብ ውስጥ ሆኜም ቢሆን ከመናገር እና በኡኡታ ከመቃወም ያረፍኩበት ጊዜ የለም፡፡ የሚያሳዝነው ነገር፤ ይህንን ተቃውሞዬን የሚጋሩኝ ብዙ ወዳጆቼ እኔን ‹‹ድፍረት›› እንዳቆም ከመወትወት በቀር ‹‹የተጫነብኝን ጭቆና እቃወማለሁ›› በማለት በተግባር ሊቀላቀሉኝ ምንም እርምጃ ሲወስዱ አላያቸውም፡፡ በርግጥ ስጋታቸውን እኔም እጋራዋለሁ፤ በአገራችን ወቅታዊም ሆነ ነባር ታሪክ ተቃውሞ ማለት የጋለ ብረት መጨበጥ ነው፡፡

ቢሆንም ከላይ ያነሳሁትን ሐሳብ በእጅጉ አምንበታለሁ፡፡ አምባገነኖች ያለሕዝቦቻቸው ይሁንታ፣ ቸልተኝነት እና ዝምታ አምባገነን የመሆን አቅምም ዕድልም የላቸውም፡፡ በቃችሁ ካላልናቸው መቼም አይበቃቸውም፡፡ እኛ እነርሱን በቃችሁ ለማለት ካልፈቀድን፤ ልክ በርዕሴ እንዳጣቀስኩት አባባል ይህ አምባገነናዊ አገዛዝ - ለእኛ ለኢትዮጵያውያን - በርግጥም ይገባናል ማለት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ብዙሐን ኢትዮጵያውያንን የኢሕአዴግ አስተዳደር የሚመጥነን ከሆነ፤ ኢሕአዴግ የማይመጥናቸው ኢትዮጵያውያን ለብዙሐኑ ሲባል ተጨፍልቀው ማለፍ ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment