Pages

Saturday, November 26, 2011

“ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ እያለች ሃገር የላቸውም”


“በዓለም አንደኛ ነው፤” በሚል በገዛ ጓደኞቼ ተጠቁሜ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ገብቼ ያየሁት “ዘመቻ ድንግልን ፍለጋ” የተሰኘ ፊልም አንደኝነቱን ለደረጃ አጣሪ ኮሚቴ ሰጥቼና እምባዬን ወደሰማይ ረጭቼ ከውስጡ ያገኘሁትን ዓረፍተ ነገር ለወጌ ርዕስነት መርጬዋለሁ፡፡ ዓረፍተ ነገሩ “7ተኛው ሰው” የተባለ ሌላ “በዓለም አንደኛ” ፊልም አስታወሰኝ፡፡ ሰባተኛው ሰው ወደአሜሪካ ለዎርክሾፕ ከሄዱት ሰባት ሰዎች መካከል ወደሃገሩ ተመልሶ የመጣው እና በፊልሙ ዓለም ውስጥ በነበሩ ምሁራን፣ ተቃዋሚ እና ገዢ ፖለቲከኞች ብሎም በቤተሰቦቹ ሳይቀር የመገለል ዕጣ የደረሰበት ነበር፡፡ ለምን ተመለስክ በሚል፡፡

እዚህ ፊልም ላይ የታየው ታሪክ እንዳልተጋነነ ለማወቅ ከፈለጋችሁ አንድ የእውነተኛ ታሪክ ልጨምርላችሁ፡፡ ፋንታሁን ሸዋንቆጨኝ በብሔራዊ ቲያትር አንጋፋ ድምፃዊ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በባለሙያዎች የተወደሰ አልበም አውጥቶ ብዙም አድማጭ አላገኘም ነበር፡፡ በርግጥ ዜማዎቹ ለአሸሸ ገዳሜ የማይመቹ ስለሆኑ፣ የዘመኑን መስፈርት አያሟሉም ነበር፡፡ ብዙዎቻችሁ ከጂጂ ጋር በማሲንቆ ያዜማቸውን እና ከሸገር ሬዲዮ በቀር በሌላ ሬዲዮ ጣቢያ እምብዛም በማይደመጡት ዜማዎቹ ታውቁታላችሁ፡፡ ስለርሱ ነው የምነግራችሁ፡፡

አርቲስት ፋንታሁን ከጥቂት ዓመታት በፊት ሙሉ የኪነት ቡድን በመሪነት ይዞ አውሮፓና አሜሪካ ደርሶ ሲመለስ፣ ልክ ሰባተኛው ሰው ላይ እንደነበረው ሰባተኛ ሰው ብቻውን ነበር የተመለሰው፡፡ ታዲያ እሱም ወይ ቆጭቶታል፣ ወይ መገለል ደርሶበታል፣ አሊያም ደግሞ በቢፒአር ጦስ ከደረጃው ዝቅ በመደረጉ ተበሳጭቷል ለድጋሚ ዙር ወደአሜሪካ እንደወጣ በዚያው ቀርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብም ይሁን በለጋሽ ሃገራት ድጎማ፣ በቡድንም ሆነ በተናጠል፣ ለትምህርትም ሆነ ለሴሚናር የሚላኩ ኢትዮጵያውያን በወጡበት መቅረት ከጀመሩ ቆዩ፡፡ ጉዳዩ እየጨመረ መጣ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ አንድ 30 ዓመት ያልሞላው፣ መቀሌ ዩንቨርስቲ ውስጥ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ አስተማሪ ለሦስት ወራት ስልጠና ወደአሜሪካ መሄድ ነበረበት፡፡ የወቅቱ አለቃው አሜሪካዊ ስለነበር ቪዛ ለማግኘት አልተቸገረም ነበር ነገር ግን የአሜሪካ ኤምባሲዋ ቪዛ ኃላፊ ‹‹ቪዛውን የምሰጠው እንደሚቀር እያወቅኩ ነው›› አለችው ለአሜሪካዊው አለቃው፡፡ አለቅዬውም ‹‹አይቀርም›› ብሎ ተወራረዳት፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች በወር ደሞዛቸው አስያዙ፡፡ ይህንን ጉዳይ ወጣቱ አልሰማም፡፡

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሦስት ወር አለቀና ወጣቱ ከጀመርመን ሁኖ ደወለ - ለአለቃው፡፡ ‹‹በሉፍታንዛ እየበረርኩ ነው፡፡ አሁን ጀርመን ላይ ለትራንዚት አርፌያለሁ፤ ነገ አዲስ አበባ ነኝ›› አለው፡፡ የቪዛ ጉዳይ ኃላፊዋ ተሸነፈች፡፡ ታሪኩን በዝርዝር ሲሰሙት በጣም ያስደስታል፡፡ ይሄ ታሪክ ግን አሁን አልፎበታል፡፡ አለቅዬውም አምኖ አይወራረድም፡፡

አንዲት እኔ በቅርብ የማውቃት ሴት ለአጭር ጊዜ ስልጠና አሜሪካ ከገባች በኋላ በሳምንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጂ20 ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን ለመቃወም በተጠራ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ፊት ለፊት መፈክር ይዛ ቆማ ዩቱዩብ ላይ አየኋት፡፡ ልጅቱ እዚህ እያለች አንድም የተቃውሞ ድምጽ ስታሰማ አላስታውስም ነበር፤ የኋላ ኋላ ግን ፖለቲካዊ ጥገኝነት እንደጠየቀች ሰማሁ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት የሚባል ነገር ቢኖር ኖሮ አሪፍ ነበር፡፡ ምክንያቱም እሷን መሰሎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች የእውነት ፖለቲካዊ ስጋት ተጋርጦባቸው ለሚሰደዱትን ዜጎች መጠጊያ የሚያሳጣ ጥርጣሬ እንዲያጋጥማቸው መንስኤ ሆነዋል፡፡

አንዲት የቅርብ ጓደኛዬ ከዕድሜዋ በእጥፍ ሲደመር አንድ ዓመት የሚበልጣትን አሜሪካዊ አገባች፡፡ በርግጥ እንደነገረችኝ ከሆነ ግንኙነታቸው “ፍቅር አለበት፤ በዚያ ላይ ከሐበሻ ወጣት አሜሪካዊ ጎልማሳ የተሻለ ሮማንቲክ” እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ነግራኛለች፡፡ እኔ ግን ከሰውዬው ባልተናነሰ መልኩ ከአሜሪካጋ ፍቅር እንደያዛት ይሰማኛል፡፡ ጉዳዩ ‘በምንም ምክንያት ይሁን በየትም በኩል ከኢትዮጵያ ውጣ፤ አለበለዚያ ያልፍብሃል’ ነው ጨዋታው፡፡

ከምንወዳት ሃገራችን ለመውጣት ሕይወታቸውን የሚከፍሉ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በኤርትራ ባሕር ወደየመን እና የሞያሌ ወደብን አሳብሮ ወደሱዳን ለማቋረጥ በሚደረጉ ተጋድሎዎች የሚያልፉትን ሕይወቶችና ባክነው የሚቀሩ ዜጎቻችንን ታሪክ ማንበብ ነዋሪ ምሳሌ ነው፡፡ በቅርቡ ሞዛምቢክ ውስጥ ወደደቡብ አፍሪካ ለማቋረጥ የተሸሸጉ ኢትዮጵያውያንን ማጋለጥ ያሸልማል መባሉ አንገት የሚያስደፋ የአደባባይ ገመና ነው፡፡

እዚህም ‹‹እዬዬ!›› እዚያም ‹‹እዬዬ!››
በሚገርም ሁኔታ አብረውኝ ያደጉ እና የኑሮ ዱብዱብ በተለያየ አጋጣሚ ያገናኙን በርካታ ሰዎች አሁን በፌስቡክ የጓደኞቼ ዝርዝር ውስጥ ተገጥግጠዋል፡፡ ባሕር ማዶ ያሉት ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡ እናም አንዳንዴ በቻት መስኮት ስናወጋ የሚነግሩኝ ነገር እዚህ እያሉ ከሚያማርሩት የተሻለ ዕድል እንዳልገጠማቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡
አንዱ፤ “ኢትዮጵያን በእንብርክኬ ይቅርታ ልጠይቃት እፈልጋለሁ” አለኝ፡፡ ይህ ሰው እዚህ እያለ መኖር አቁሞ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እዚህ አገር ሰርቶ ሰው መሆን እንደማይችል በቁርጠኝነት፣ በየአደባባዩ ይመሰክር ነበር፡፡ እዚያስ?
ሌላው፤ “የአሜሪካ ሕንፃ ለኔ ምኔ ነው፤ የዕለት ጉርስ ይሆነኛል?” ጠየቀኝ፡፡ “አየዋለሁ እንጂ አልገባበትም” እኔ መልስ እንደሌለኝ ጠፍቶት አይደለም፡፡ ብሶቱን እያራገፈ እንጂ! እንደርሱ አገላለጽ “አሜሪካ ተበልቶባታል፡፡” አሁን “እንዳህያ ሰርተው እንደ ጉማሬ ማውጣት ብቻ ነው የቀረው” ካለ በኋላ “እኔ እንደውም በድብርት ራሴን እንዳላጠፋ ነው የምፈራው” ብሎኛል፡፡
ሌላዋ፤ “ውጪ አገር መሄድ፤ የሃገር ፍቅርህን ይጨምረዋል እንጂ ጠብ የሚያደርገው ነገር የለም፤” ብላኛለች፡፡

እዚህ ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስኩት አንደኛው ሚስት እዚህ፣ ከባሏ በሚላኩላት ጥቂት ዶላሮች የሚታይ ለውጥ እያመጣች በመሆኑ ለብዙ ተመልካቾቿ የስደት ናፍቆትን አጠናክራለች፡፡ እዚያ ምንም ተሁኖ ቢሰራ፣ እዚህ መጠነኛ ፋይዳ ያለው ለውጥ ማስመዝገቡ ሁሉንም ሰው ወደማያውቁት ገዳም እንዲመንኑ አስመኝቷቸዋል፡፡

በሌላ በኩል እዚያ ሁነው የሚያማርሩት “ለምን ወደሃገራችሁ መጥታችሁ አትኖሩም?” ሲባሉ አለመስማማታቸውን፣ እዚህ ያሉቱ በጥርጣሬ እንዲመለከቱት እያደረጋቸው ነው፡፡ እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ሌሎች እንዳይደርሱ የሚያደርጉት የምቀኝነት ንግግር እስከሚመስል ድረስ፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞቹ እዚህ የጀመሩትን ኑሮ አቋርጠው በሰው አገር አዲስ ኑሮ ጀምረዋል፤ አዲሱ ኑሮም አልሞላም፡፡ እዚህ መጥተው ሦስተኛ ኑሮ መጀመሩ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደሚያስከፍላቸው ያውቃሉ፤ ስለዚህ ተመልሰው ይሄዳሉ፡፡ አንድ ቀን የሄዱበት ጉዳይ ከሞላላቸው ይመለሳሉ፤ ብዙዎቹ ግን ሳይሞላላቸው በፊት ለቀብራቸው ኢትዮጵያ ይመጣሉ - ኢትዮጵያ ውስጥ አልቅሶ የሚቀብራቸው ሰው አይጠፋም፡፡

No comments:

Post a Comment