Pages

Tuesday, November 22, 2011

የኢሕአዴግ ‹‹ትርፍ›› እና ኪሳራ


ኢሕአዴግን ፀሃዩ መንግስት እያለ በሽሙጥ የሚያንቆለጳጵሰው አበበ ቶላ በካድሬዎች ሽንቆጣ ብዛት ኮበለለ፣ የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተርና የ2010 CPJ ፕሬስ ነፃነት ተሸላሚው ዳዊት ከበደም እያሻቀበ በመጣበት ትንኮሳና (እንደራሱ ገለፃ ‹‹ማክሰኞ፤ ሕዳር 12፤ 2004›› ሊታሰር ስለነበር) ወደ ሃገረ አሜሪካ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ የምንወዳቸው፣ ጽሁፎቻቸውን የምንናፍቅላቸው ጋዜጠኞች በሙሉ ከፊሎቹ ተሰደዱ፣ ከፊሎቹ አቋማቸውን አለዘቡ፣ ከፊሎቹ ብዕራቸውን ሰቀሉ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ታሰሩ፡፡ ‹‹ሂስ ቀረበብን ብለው ሃገር ጥለው ፈረጠጡ›› በሚል በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተተቹት እነ ዐቢይ ተክለማርያም እና መስፍን ነጋሽ በአሸባሪነት በሌሉበት በተከሰሱበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት የሃገራችን የፕሬስ ነጻነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ አቶ በረከት ስምዖንን፣ ሚሚ ስብሃቱን፣ ሳምሶን ማሞን ወይም የኢቴቪ ሚዲያ ዳሰሳ አዘጋጆችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡

በተቃራኒው WorldPress Freedom Index 2010 የኢትዮጵያን የፕሬስ ነፃነት ‹‹አስቸጋሪ ሁኔታ›› (ለመጨረሻ ሩብ ጉዳይ) ላይ እንዳለ ይነግረናል፡፡ የ2011 ውጤት ሲታወቅ ደግሞ ‹‹በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ›› (የመጨረሻ ደረጃ ላይ) ነው ብሎ እንደሚፈርጀው መገመት አይከብድም፡፡ በFreedom of the Press Global Status ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ‹‹ነፃ ያልሆነች›› ተብላለች፡፡ ጋዜጠኞችንም በማሰር ቢሆን ኢትዮጵያን ከኤርትራ በቀር የሚበልጣት እንደሌለ chartsbin.com በዝርዝር ያስነብበናል፡፡ እኛ ማንን እንመን? በመንግስት ቲፎዞነታቸው የምናውቃቸውን እኒያን ግለሰቦች ወይስ በጥናት ላይ ተመርኩዘው የሚነግሩንን እኒህ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ድርጅቶች? ግዴለም የምናየውን እንመን፤ የታሰሩትንና እየተሰደዱ ያሉትን ጋዜጠኞች አይተን እንፍረድ፡፡
የአገራችን የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ በወረቀት ጋዜጠኞች ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ የመንግስትን ስህተት ከመንቀፍ የማይቆጠቡት እነ voa.com፣ addisnegeronline.com፣ ethiopianreview.com፣ ethioguardian.com፣ ethiomedia.com እና nazret.comን ጨምሮ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸውን ሌሎች በርካታ ድረዓምባዎችን በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ አግዷቸዋል፡፡

የፕሬስ ነፃነቱ ደረጃ በዚህ ብቻ አይገለፅም፤ በአገራችን ሆነ ተብሎ በሚመስል ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ ዋጋው እያሻቀበ የመጣው የወረቀት እና የሕትመት ዋጋ ጋዜጦችንም ሆነ ንቁ ሕዝብ መፍጠር የሚያስችሉ መጽሃፍትን የቅንጦት ንብረት እያስመሰላቸው ነው፡፡ በአሳለፍነው 10 ዓመት ውስጥ የጋዜጦች ዋጋ በ466% ጨምሯል (ከ1 ብር ከ50 ወደ 7 ብር፤ ከምርጫ 97 ወዲህ ደግሞ በ280%)

‹‹ትርፍ››
የዚህ አፈና ትርፉ ምንድን ነው የምትሉ ከሆነ መልሱ ቀላል ነው፤ ስልጣንን ማራዘም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለቻይና ‹‹ቀለም›› ተማሪዋ ነው፡፡ ቻይና ኢንተርኔትን በመገደብ ከአለማችን የሚወዳደራት የለም፡፡ ኢሕአዴግም ብዙ ተቃዋሚ ድረአምባዎች ቢኖሩት ኢትዮጵያን ከቻይና አያሳንሳትም ነበር፡፡ ምክንያቱም የቻይና ኮሙኒስቶች እስካሁን በስልጣን ላይ ተቆናጥጠው መኖር የቻሉት በዚሁ መንገድ መሆኑን ያምናል፡፡

እውነቱን ለመናገር በአገራችን እየተዘዋወራችሁ የምታገኙትን ሰው ብትጠይቁ ታዝናላችሁ፡፡ ስለ ኑሮ መወደድ ስታወሩ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደሆነ ሊነገራችሁ ይችላል፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ምነው እንዲህ ጠመዳት እስክትሉ ድረስ፡፡ ስለየኔሰው ገብሬ ሞት ብትጠይቁ፣ ‹‹ማነው ደግሞ እርሱ?›› የሚል አስደንጋጭ መልስ ታገኛላችሁ፡፡ ስለታሰሩት፣ ስለተሰደዱት ጋዜጠኞች እና ስለአሸባሪዎች አደን ብትጠይቁ ‹‹ደሞ እንደዚህ ዓይነት ነገር እኛ አገር አለ እንዴ?›› ትባላላችሁ - ከዚያ ተስፋ ትቆርጣላችሁ፡፡

መረጃ የሌለው ሕዝብ ‹‹ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ›› ብሎ የሚተርት ሕዝብ ነው፡፡ ይሄ ተረትና ምሳሌ ከኢትዮጵያ ዛሬም አልተነቀለም፡፡ ኢሕአዴግ በነፃው ፕሬስ አፈና የሚያተርፈው መረጃ የሌለው እና ፀጥ ለጥ ብሎ የሚገዛ ሕዝብ ነው፡፡

ኪሳራ
የፕሬስ ነፃነትን የሚያፍኑ መንግስታት ኪሳራ የሚታየው ዘግይቶ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት መታፈን የሕዝቦችን የለውጥ ጥያቄ ያዘገየዋል እንጂ አያስቀረውም፡፡ ማሕበረሰቦችን በመረጃ ማፈን ብቻ ከማሰብ ማስቆም አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሕዝባዊ ብሶቶች ምንም መረጃ ወይም የመረጃ ምንጭ በሌለበት ሁኔታም ቢሆን መገንፈሉ አይቀርም፤ ኪሳራው ይኸው ነው - ብዙ የሚከፈልለት የስልጣን ጥም ዘላለም አይዘልቅም፡፡ የኢሕአዴግ መንግስትም - በቅርቡ፣ እጅግ በጣም በቅርቡ ይህንን እውነታ መጋፈጡ እንደማይቀር ይሰማኛል፡፡ ይሁን እንጂ የፕሬስ ነፃነት አፈና በአንድ አብዮት ተደምስሰው ከሚከስሙ የስልጣን ጥመኞች ይልቅ ዘለቄታዊ ተፅዕኖውን የሚያሳድረው ታፍኖ በሚከርመው ማሕበረሰብ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ‹‹እጅግ በጣም በቅርቡ›› ያልኩት የኢሕአዴግ ምፅዓተ ፍፃሜ ዛሬ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ትርፍና ኪሳራ ሲወራረድ
ሕዝባዊ መሰረት የሌለው መንጠራራት ኋላ ለመፈጥፈጥ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹እየረገጥካቸው የምትወጣባቸውን ሕዝቦች እንዴት መያዝ እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ስትወርድ የምትወራረድባቸው እነሱኑ ነው›› ብሎ የሚመክረው አካል ያስፈልገዋል፤ ምክር የሚሰማ ከሆነ፡፡


አንቺም ዝም በል አልሽኝ፣ እኔም ዝም አልኩልሽ
ምንድን ነው ያጎደልኩት፣ አንቺስ ምን አተረፍሽ?
ስሀተትሽን ሸሽጌ ውድቀትሽን አፋጠንኩ
አንቺም አልተበጀሽ፣ እኔም አልተጠቀምኩ፡፡

No comments:

Post a Comment