Pages

Friday, July 8, 2011

እንኳን ኢሕአዴግ ደርግም ወድቋል

ደርግ አንቀጥቅጦ በመግዛት አቻ የለውም፡፡ የሰራዊቱ ግዝፈት እንኳን ተራ ሽፍቶች የተደራጀ ጦር እንኳን የሚደመስሰው አይመስልም ነበር፡፡ የሰራዊት ግዝፈት ለአንድ ስርዓት ዋስትና ሊሆን እንደማይችል የተረጋገጠው በደርግ ውድቀት ነው፡፡

ለደርግ መውደቅ የራሱ የሰራዊቱ አስተዋፅዖ ቢኖርበትም እምነት አጉዳዩ የደህንነት ቢሮ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በወታደራዊ ስልት እዚህ ግባ የማይባል ዕውቀት የሌላቸውብሶት የወለዳቸውሽምቅ ተዋጊዎች ዘመናዊ አደረጃጀት ያለውን ግዙፉን ወታደራዊ መንግስት የገረሰሱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ደርግ ነገሮችን በጉልበት ለመቆጣጠር በሞከረ ቁጥር የሕዝብ ይሁንታን እያጣ በመምጣቱ ከሰራዊቱም ሆነ ለስርዓቱ ዋስትና ከሚሰጠው ደህንነት ቢሮ ታማኞችን ማፍራት አልቻለም ነበር፡፡ ”11ኛው ሰዓትእየታፈሱ ወደጦር ሜዳ የተሸኙት ወጣቶችም ቢሆኑ ለጠላት እጃቸውን በመስጠት ነገሩን ባጭሩ ይቀጩት ነበር፡፡
ነገሩ እንደዚህ በምሳሌ ሊጠቃለል ይችላል፡፡ አንድ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ያለቀጫጭን ፌሮ ብረቶች፤ የቱንም ያህል ሲሚንቶ ቢደፈደፍበት፣ የቱንም ያክል ቋጥኝ ቢገተርበት ወድቆ መንኮታኮቱ አይቀርም፡፡ ቀጫጭኖቹን ፌሮ ብረቶችን እንደ ሕዝባዊ ይሁንታ መመልከት ይቻላል፡፡
ወደአለንበት መንግስታዊ ስርዓት ስንመለስ አሁን እነዚያብሶት የወለዳቸውሽምቅ ተዋጊዎች ስልጣን ያባለጋቸው፣ ለሌሎች ብሶተኞች መወለድ ምክንያት ለመሆን የበቁ ጨቋኞች ሁነዋል፡፡ ሕዝባዊ ይሁንታ አላቸው ለማለትም የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ ማታለል ግን ይችሉበታል፡፡

የድሮው የአሜሪካ ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንከን በአንድ ወቅት “You can fool all of the people some of the time, and some of the people all of the time, but you can't fool all of the people all of the time” (ሁሉንም ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ወይም ጥቂት ሰዎችን  ለሁልጊዜ ማታለል ትችላላችሁ፤ ሁሉንም ሰዎች ለሁልጊዜ ማታለል ግን አትችሉም፡፡) ብለው ተናግረው ነበር፡፡ የነፃነት ትግል ተምሳሌት ልንለው የምንችለው ቦብ ማርሌይም ይህንኑ ንግግራቸውን Get up, stand up በተሰኘው ቆስቋሽ ዘፈኑ በመጠኑ ደቁሶ አቀንቅኖታል፡፡

ስለዚህ መንግስት ሁሉንም ሕዝብ እያታለለ ሁል ጊዜ መኖር አይችልም የምንለው ይህንን እውነታ ስለምንረዳ ነው፡፡ በርግጥ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ሰው በአቦ ሰጡኝ ብትመርጡ በኢሕአዴግ ስርዓት የተማረረ ሰው የማግኘት ዕድላችሁ 75 በመቶ በላይ እንደሚሆን እወራረዳለሁ፡፡ ሁሉም ብሶተኛ ግን ደፍሮ ይናገራል ማለት አይደለም፤ ከሚያምናቸው ወዳጆቹ ጋር ሲሆን ብቻ ምሬቱን ይተነፍሳል፡፡ ከዚያ ውጪ ጎመን በጤና ነው፡፡

ይሄ በጨቋኝ ስርዓት ስር ያሉ ሕዝቦች መለያ ነው፡፡ በደርግ ጊዜም ቢሆን ሕዝቡ በይፋ የመቃወም ድፍረትም መብትም አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ያኔ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ሰራዊቱም፣ ሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱም ልቡ ሸፍቶ ነበር፡፡ አሁንስ? አሁን ነገሩ ይለያል፡፡ የሰራዊቱ እና የደህንነት ቢሮው ቁንጮ ቦታዎች በሙሉ ከአንድ ጎሣ በተውጣጡ ቡድኖች ተይዘዋል፡፡ እነዚህ ከአንድ ጎሣ የመነጩ፣ ነገር ግን ለመነጩበት ጎሣ ራሱ የማይበጁ ቡድኖች ዋስትናቸውን በመንግስቱ ሕልውና ላይ ስላስቀመጡ ለስርዓቱ ያላቸው ታማኝነት ጠንካራ ነው፡፡

ብዙዎቹ ይሄ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ቦታው የሚመጥናቸው ባለመሆናቸው በታማኝነት ስርዓቱን ካልጠበቁ አሁን ያላቸው ስልጣንና ክብር አብሯቸው አይዘልቅም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ፍፁም በጎሣዊ አስተሳሰብ ታውረዋል፡፡ ይሄ ስርዓት ተገርስሶ ከወደቀ የነርሱ ጎሣ በኢትዮጵያ ተስፋ የሌለው እንደሆነ አምነዋል፡፡ እውነት አላቸው፡፡ የገዛ ስርዓታቸው የፈጠረው የከፋፍለህ ግዛ አካሔድ ሕዝቡን በአንድ ጎሣ ጨቋኝት አበሳውን እያየ እንደሆነ እንዲሰማውና ቂም እንዲይዝ አድርጓል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የኢሕአዴግ መንግስት ሰራዊትም ሆነ የደህንነት ቢሮ ታማኝነት ሰርጎ መግባት በማያመች ሁኔታ ታጥሯል፡፡ ሆኖም አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ ደጋግሜ ለማመላከት እንደሞከርኩት ሕዝባዊ ይሁንታ ከማንኛውም ሰራዊት፣ ከየትኛው የደህንነት ቢሮ መራቀቅ የበለጠ ኃይል አለው፡፡

ሌላው የማይታበል ሐቅ ደግሞ፤ በተለያዩ የወቅቱ ስርዓት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተሰየሙ ሰዎች፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኤምፓየር የመመስረታቸው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ የትልልቅ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ናቸው፣ የሚያከራዩት ሕንፃ፣ የሚኖሩበት ቪላ ገንብተዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የመንግስት ደሞዝ የለም፤ አመጣጡን ጨክኖ የሚጠይቅ ስርዓትም የለም፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ ከተገረሰሰ ጠያቂ መምጣቱ አይቀሬ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች በታማኝነት የመንበራቸውንና የስርዓቱን ደህንነት ይጠብቃሉ፡፡

ጓድ መንግስቱ - የደርግ ሊቀመንበር ‹‹አንድ ሰው እና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋጋለን›› ብለው አልተሳካላቸውም፡፡ ነገር ግን እሳቸው ሲሰደዱ እዚህ የሚቀራቸው የኢኮኖሚ ኢምፓየር አልነበራቸውም፡፡ አሁንም በዝምባቡዌ ያላቸው አንድ መርሴዲስ፣ አንድ ቤት እና የእርሻ ቦታ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ግን በውጭ ያኖሩት ሃብት የቱንም ያህል ቢሆን አንኳ፣ እዚህ ያፈሩትን ሃብት ጥሎ ለመሸሽ አያስደፍራቸውም፡፡

መሳሪያውን ያነገቡት ሰዎች የስርዓቱ ታማኞች በሆኑበት ሁኔታ ኢሕአዴግን መጣል ቀላል አይሆንም፤ ሆኖም ይቻላል፡፡

በአንድነት፣ የሚታገሉለትን እና የሚታገሉትን በሚገባ በማወቅ፣ በቁርጠኝነትና በትዕግስት ጥቂቶቹን የፈርኦን (ገዢው ፓርቲ) ታማኞች መሰረት ያደረገውንና በማታለል ከደርግ ለበለጠ ጊዜ የነገሠውን ሥርዓት በብዙሐኑ ፈቃድ መገርሰስ ይቻላል፡፡

ሕዝባችን ከላይ የጠቃቀስኳቸውን ባሕሪያት ቢያጣ እንኳን ኢሕአዴግ ከጊዜያት በኋላ በገዛ ራሱ መውደቁ አይቀርም፡፡ የስርዓቱ ታማኞች የግል ተጠቃሚዎች እንደመሆናቸው፣ ጥቅማቸውን የሚነካ ነገር በተፈጠረ ቁጥር እየተሰነጣጠቁ መሰረቱን ፈረካከሰው ይጥሉታል፡፡ ይሔ ተፈጥሯዊ ሒደት ነው፡፡ ልክ እንደማንኛውም ነገር መንግስታዊ ስርዓትም ይወለዳል፣ ያድጋል፣ በመጨረሻ ይሞታል፡፡ ቀባሪ አያሳጣው፡፡

No comments:

Post a Comment