Pages

Thursday, January 7, 2021

አሜሪካ እና ማኅበራዊ ሚዲያ

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ጉዳይ አሜሪካውያን የማይደራደሩበት ጉዳይ ነው። ሕገ መንግሥታቸውን መጀመሪያ ያሻሻሉትም በዚሁ ጉዳይ ነው። "ፈርስት አሜንድመንት" (አንደኛው ማሻሻያ) "ኮንግረስ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም" ይላል። ዛሬ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአሜሪካውያኑ ኩባንያዎች ፌስቡክ እና ትዊተር ታግደዋል። አሜሪካውያንም ደንግጠዋል።  

ካፒቶል ሒል የሚሉት የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ አውጪ (ኮንግረስ) በነውጠኞች የሰው መንጋ ተደፍሯል። አሜሪካውያኑ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ እንዲህ ዓይነት ቅሌት አይተው አያውቁም። ለዚህ የዳረጋቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ያገነነው የሴራ ትንተና እና የተዛባ መረጃ ልቅ ፍሰት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ ድንገቴ መጣጥፍ የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ፋይዳ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦስ እና የነውጥ መከላከል ጉዳይን በጨረፍታ እዳስሳለሁ። 

የንግግር ነጻነት ለምን? 

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መከበር አለበት የምንለው ለአራት ወይም አምስት ዐቢይ ምክንያቶች ነው። 1ኛ) ተፈጥሯዊ ፍላጎት ስለሆነ፣ 2ኛ) እውነቱን በነጻነት ሳይነጋገሩ መረዳት ስለማይቻል፣ 3ኛ) የግለሰቦችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ፣ 4ኛ) አፈና የሚያስከትለውን ነውጥ ለማስቀረት፣ እና በቀደሙት ውስጥ ሊካተት ቢችልም፣ 5ኛ) ለሌሎች መብቶች መከበር አስፈላጊ ስለሆነ ነው። 

አመፅ ቀስቃሽ ንግግሮች እና የተዛቡ መረጃዎች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መከበር አለበት የሚያስብሉ ምክንያቶችን ይቃረናሉ። ለዚህ ነው ዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነቶች ስለሚገደቡባቸው ረገዶች (የጦርነት እና አመፅ ቅስቀሳ፣ የዘር ጥላቻ፣ ወዘተ…) እንዲሁም መርሖዎች (ሕጋዊነት፣ ቅቡልነት፣ አስፈላጊነት ላለው ዓላማ) ጥንቃቄ የተመላበት መዋቅር ለመዘርጋት የሞከሩት። ይሁንና የዘር ጭፍጨፋ አሰቃቂ ገጠመኝ ያላቸው አውሮጳውያን ሕጋዊ ጥንቃቄ ሲያበዙ፣ አሜሪካኖቹ ግን መፍትሔው ሁሌም ተጨማሪ ነጻነት ነው እያሉ ከርመዋል። 

በነገራችን ላይ የአውሮጳ እና የአሜሪካ ልዩነት በሕግ ረገድ ሰፊ ቢሆንም አውሮጳ (ለምሳሌ አክራሪዋ ጀርመን) ውስጥ ጋዜጠኞች በሙያቸው ይታሰራሉ ማለት አይደለም፤ ፖለቲካዊ ትችት ለመሰንዘርም ዜጎች አይፈሩም። አሜሪካውያንም ንግግሮችን በነጻነት ፈቅደው ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር (micro aggression) ሳይቀር በመልስ ምት እያብጠለጠሉ የአደባባይ ንግግሮች በንግግር እንዲመከቱ የሚያደርግ ባሕል ፈጥረዋል። የሐሳብን የመግለጽ አፈናዎች ጋዜጠኞች ላይ የሚያርፈው፣ ወይም ንግግሮች ያለ ምንም ተጠያቂነት ሊቀሩ የሚችሉት በአምባገነናዊ ወይም ከፊል አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ ነው። በርግጥ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር እና ሙያዊ ብቃትም ዝቅተኛ የሚሆነው በነዚሁ ከፊል/አምባገነን አገራት ነው። 

ሴራ መጎንጎን… 

ማኅበራዊ ሚዲያ ካመጣቸው ጦሶች መካከል ምንም ማስረጃ የሌላቸው መላምታዊ ሴራዎችን እንደ እውነት ማራገብ ማስቻሉ ነው። የተዛቡ መረጃዎች በመሠረቱ ጥንታዊ ናቸው። ቤንጃሚን ፍራንክሊን ከአሜሪካ "መሥራች አባቶች" ሁሉ አራቱም ቁልፍ የአሜሪካ ነጻነት እወጃ ሰነዶች ላይ የፈረሙ ሰው ናቸው። 'Like War' የተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ፖለቲካን የሚያትት መጽሐፍ ደራሲዎች ፍራንክሊንን "የአሜሪካ የተዛቡ መረጃዎች መሥራች አባት" ይሏቸዋል። ፍራንክሊን ለአሜሪካ ነጻነት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን በተዛቡ መረጃዎች እያዋዙ ሲጽፉ ከርመዋል። ብዙዎቹ የአገር ምሥረታ እና ሥልጣን ማደላደያ፣ እንዲሁም ሥልጣን መያዣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ባይዋሹ እንኳ የማይሥማማቸውን እውነት ይገድፋሉ፣ የሚሥማማቸውን ያጋንናሉ። የትኛውም ፖለቲካዊ መዋቅር ወይም ማኅበራዊ ስርዓቶች በዚህ ዓይነት መንገድ ነው የተገነቡት። ሆኖም የሰው ልጅ ሥልጣኔም ይሁን ስርዓተ ማኅበሮች እየተሻሻሉ የሔዱት ቢያንስ ባለፉት ዘመናት ላይ ያሉ ቅራኔዎች ላይ በከፊል እየተሥማሙ እና የተሻለ ስርዓተ ማኅበር ለመመሥረት ያልተጻፈ ቃል ኪዳን ገብተው ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ግን በሴራ ትንተና ተተብትበው አሻግሮ ማየት የተሳናቸውን ሰዎች እንዲደራጁ እና ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ዕድል በመስጠት የዓለምን ስርዓት ባፍጢሙ እንዲደፉት አቅም ሰጥቷቸዋል። 

ኪውኤኖን (QAnon) የሚባል የሴራ ወግ አለ። ነገርዬው በአሜሪካ ሰይጣን አምላኪ ዝነኛ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ድብቅ መንግሥት አላቸው ብሎ በማመን ላይ የተመሠረተ ነው። የዚህ ሴራ አማኞች ትራምፕ ከነዚህ ከሰይጣን አምላኪዎች ጋር ውጊያ ላይ ናቸው ብለው ያምናሉ። በስተመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ያሸንፉና ሰይጣን አምላኪዎቹ ይታሰራሉ ብለው ያምናሉ። ለዚህ ሴራ ትንተናቸው ምንም ማስረጃ አይፈልጉም። ከኪውኤኖን አማኞች ጋር ፖለቲካ፣ ርዕዮት ዓለም፣ ፖሊሲ አውርቶ መግባባት አይቻልም። ቁጥራቸው ደግሞ እየጨረመ ነው የሚሔደው። የትራምፕ ድጋፍ ሰልፎች ላይ ኪው (Q) የሚል ፊደል ያለበት ቲሸርት ወይም ኮፍያ ለብሰው ይወጣሉ። ትራምፕ እንዲህ ዓይነት ሰይጣን አምላኪ ማኅበር እንደሌለ እና እርሳቸውም ጦርነት ላይ እንዳልሆኑ እንዲናገሩ ቢጠየቁም ደጋፊዎቻቸውን ላለማጣት ሲሉ ("ይወዱኛል" ብለው) ሸፋፍነው አልፈውታል። ሕዳር ወር ላይ ከ70 በላይ የኪውኤኖን ንቅናቄ ደጋፊዎች ለኮንግረስ ተወዳድረው አንዷ ተመርጠዋል። በቅርቡ ፒው ሪሰርች እንደገመተው ከግማሽ በላይ አሜሪካውያን ስለንቅናቄው ቢያንስ ሰምተዋል። ይህ ሁሉ የጀመረው አንድ ራሱን የደበቀ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ባወራው ያልተረጋገጠ ወሬ ነው። 

ከሴራ ጉንጎና ባሻገር… 

የትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥም ሆነ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት ያለ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሆን ነገር አይመስልም። ነገር ግን የየአገራቱ ዜናዎች ሊያሳምኑን እንደሚፈልጉት የጠላቶቻቸው የእነ ራሺያ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ክፍፍል ለመፍጠር መጣር [ብቻውን] የፈጠረው ችግር አይደለም። የተጠራቀሙ ማኅበራዊ ቅራኔዎች እና አድኃሪነት ሲጋጩ እና ሲፋለሙ፣ ያለምንም አርትኦት እና ይዘት ቁጥጥር (moderation) እንዳሻቸው እንዲፈነጩ መደረጉ ያመጣው ጦስ ነው። 

ሚዲያ የተነፈጋቸው የሴራ ንቅናቄ አራማጆች እና ያለማስረጃ ተሟጋቾች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፈለጉትን የተዛባ መረጃ ጽፈው የፈለጉትን ያክል ተከታይ ያፈራሉ። የተዛባ መረጃቸው ሰለባ የሆኑ ተከታዮች የሚከፈለውን ሰብኣዊ መስዋዕትነት ከፍለው ለመሪዎቹ ግብ ይሰዋሉ። ትላንት ካፒቶል ሒል ገብታ በአስለቃሽ ጭስ እያለቀሰች ስትወጣ ሚዲያ የጠየቃት አንዲት ሴትዮ ለምን ወደ ሕንፃው እንደገባች ስትጠየቅ "ዐብዮት ላይ ነን" ("we are in revolution") ነበር ያለችው። ለነዚህ በተዛባ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ የታወሩ ሰዎች የምርጫው ውጤት እነሱ የሚፈልጉትን ውጤት ካላመጣ በስተቀር ምርጫው ተአማኒ አይደለም። ምክንያቱም፣ ፕሮፓጋንዳው ከሌላ ወገን የሚመጣውን ነገር በሙሉ እንዲጠራጠሩ አድርጎ ሠርቷቸዋል። 

የእነቻይና ተቃራኒ ጥፋት… 

ቻይና የአሜሪካውያኑን ማኅበራዊ ሚዲያዎች አገሯ ላይ አግዳለች። የራሷን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በምትኩ አኑራለች። የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መንግሥትን ተቃውሞ መጻፍ አይቻልም። እንዲህ ያሉትን ይዘቶች የሚያነፈንፈው 'አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ' መጀመሪያውንም እንዳይለጠፍ ይከለክላል። አምልጦ ቢለጠፍ እንኳን ቆይቶ ያወርደዋል። ይህ ተሞክሮ አምባገነናዊ እና ተፈጥሯዊ ነጻነትን የሚጋፋ ነው። አምባገነኖች ቢያገኙት ለምን እንደሚያውሉት ስለሚታወቅ ተቀባይነት የለውም። ነገር ግን ቢያንስ መሆን የሌለበትን ነገር ለማወቅ እና ቴክኖለጂውን ከላየረ በጠቀስነው መርሕ (ሕጋዊነት፣ ተቀባይነትና አስፈላጊነት ላላው ዓላማ) ማዋል እንደሚቻል መማሪያ ይሆናል (የኮምፒዩተር ቫይረስን በአንቲቫይረስ እንደመመከት)። 

በሌላ በኩል ማኅበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን እና ነውጠኛ ፅንፈኝነትን (violent extremism) የሚኮተኩቱ ሴራዎችን የሚያጠልሉበት ስርዓት ያስፈልጋል። የማጥለል ሥራው ሐሳብ እንዳያፍን ስለሚያስፈልግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የተረጋገጡ ገጾች ሰማያዊ ባጅ እንደሚደረግባቸው ሁሉ፣ ተደጋጋሚ ሴራ ጉንጎናዎች እና ሴራ ተንታኞችን መለየት የሚያስችሉ፣ ቢጫ እና ቀይ ባጆችን እስከመለጠፍ እና ለተደራሲያኑ ማስጠንቀቂያ ደወል በመስጠት ተፅዕኗቸውን መቀነስ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ከ'ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ' ( 'Third Wave of Democracy') ወዲህ የታየው የዴሞክራሲ እመርታ በቀኝ ዘመም አክራሪነት፣ በሴራ ጉንጎና፣ በተዛቡ መረጃዎች፣ እና በጥላቻ ንቅናቄዎች ይቀለበሳል። 

ማኅበራዊ ሚዲያዎች አምባገነን መንግሥታትን ለመታገያ አቻ የሌላቸው መድረኮች ናቸው። ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግን አደገኛ ተግዳሮት ሆነዋል። 

የኢትዮጵያ ፈተና… 

የማኅበራዊ ሚዲያ ወጎች የኢትዮጵያ ፈተና አልሆኑም ማለት ክህደት ይሆናል። በርግጥ አምባገነናዊ አሠራሮችንም በመገዳደር አቻ የለውም። ሆኖም መሬት ላይ ግጭት ለመቆስቆስ የሚያበቁ ሴራዎችን በመፍጠር እና የተፈጠሩ ግጭቶችን በማባባስ በቀውስ ላይ ቀውስ እንዲፈጠር መድረክ ሆኗል። ሕዝበኝነት የፖለቲካው አዲስ ባሕሪይ እንዲሆን ያደረገውም ማኅበራዊ ሚዲያ ነው። ከገዢዎቹ እስከ ተቃዋሚዎቹ ድረስ በነፍስ ወከፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪዎች አሏቸው። የሥልጣን ሽኩቻዎች የሚራገቡት በፌስቡክ ነው። 

መጪው ምርጫ የፈለገውን ያክል ቢቀዘቅዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። መራጮች ወደ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የሚሔዱት የተወዳዳሪዎችን አማራጮች ምንነት እና ልዩነት በቅጡ ተረድተው ከመሆኑ ይልቅ፥ በማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳዎች የተፈጠሩ እውነትም፣ ውሸትም አዘል ማንነቶች እና ፍረጃዎች ተማምነው የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። በዚህ ረገድ ምርጫውን በቅጡ ተረድተው (well-informed ሆነው) ከሚመርጡ ሰዎች ይልቅ፣ በክፋት ተሳስተው (ill-informed ሆነው) የሚመርጡ ሰዎች ይበዙበታል ማለት ንፉግነት አይደለም። ይህ የሚሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓትን መመከት የሚችል የመንግሥት ግልጸኝነት፣ የሚዲያ ሐቅ አረጋጋጭነት፣ የብዙኃን የመረጃ ይዘት ተረጂነት እና የማኅበራዊ ሚዲያዎች በቂ አደገኛ ይዘት አጥላይነት በሌለበት በመሆኑ ችግሩ የከፋ ነው። በኢትዮጵያ የፍትሕ መከታ ሳይሆን የገዢዎች በትር የሆነው ሕግም ቢሆን የፖለቲካ ከመሆን አይተርፍም። ሕግ እንኳን በኢትዮጵያ፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ባላቸው አገራት ሳይቀር እንዲህ ዓይነቱን የተዛባ ወረርሽኝ ለመመከት ፍቱን መድኃኒት አይሆንም። 

ለዚህ ነው ስለአሜሪካ ሲወራ ለእኛ ብለን እንስማ የምለው!

No comments:

Post a Comment