በዚህ ርዕስ ረዥም መጣጥፍ መጻፍ ከጀመርኩ ረዥም ግዜ ሆነኝ፡፡ እስካሁን አላለቀም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ጉዳዩ ስሜት የሚነካ እና በስሜት የሚነዳ ስለሆነ ፈርቼው ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋስኦዋችንን በተከታተልኩት ቁጥር የተረዳሁት አንድ ነገር ቢኖር "ብሔርተኛ ነኝ" በሚሉ እና "ብሔርተኛ አይደለሁም" በሚሉት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ብሔርተኝነትን የማመን እና የመሸሸግ ችሎታ ልዩነት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንዴ ልዩነቱ ግለሰቦቹ የሚያራምዱት ብሔርተኝነት የሚያቅፋቸው ሰዎች ቁጥር የበዛ መሆኑ ‹ብሔርተኝነቱን› የመሸሸግ ዕድል ያገኛል፡፡ በጣም በተሳሳተ መደምደሚያ ላለመጀመር ያክል "ብሔርተኝነት" ደረጃው እና ልኩ ይለያይ ይሆናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከውስጡ የወጣለት ሰው የማግኘት ዕድላችን ጠባብ ነው ብለን እንስማማ፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ‹ብዙኃን ብሔርተኛ ናቸው› የሚል መደምደሚያ ይዤ ነው ይህንን የምር አጭር ያልሆነ መጣጥፍ፣ ረዘመብኝ ካልኳችሁ መጣጥፌ ጨልፌ እና ጨምቄ የማስነብባችሁ፡፡ የመጀመሪያው አንቀፄ እንደሚያመለክተው ‹ብዙኃን ብሔርተኞች ናቸው›፡፡ ‹ብሔርተኝነት ቅዱስ ነው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ ማንሳት ‹ብዙኃን ቅዱስ ናቸው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ እንደማንሳት ያስፈራል፡፡ ቢሆንም እንጋፈጠዋለን። ብሔርተኝነት ሲበየን ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ለብሔርተኝነት ያላቸው ንቀት የትየለሌ ነው፡፡ ንቀቱ አንድም ብሔርተኝነት ‹ማኅበራዊ ፈጠራ› (social fabrication) ነው ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሰው ልጅን ያክል ባለ ብሩሕ አእምሮ በአጋጣሚ በበቀለበት ማኅበረሰብ ብቻ መበየን ከእውነታው የራቀ ስለሚሆን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የብሔርተኝነት የመዝገበ...
Passionate about the ideas of liberty and dignity, and of course prosperity too.