በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተስፋን-በጥንቃቄ (cautious optimism) ካነገቡት ሰዎች አንዱ ነኝ። የተስፋዬ መሠረቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድ፣ የገቧቸው ቃልኪዳኖች እና አሁን የታየው መረጋጋት ናቸው። አሁን የታየው መረጋጋት ስል የቄሮዎች የአደባባይ ተቃውሞ መቆሙን ማለቴ አይደለም። ተቃዋሚዎችን እያሳደዱ መከታተል፣ ማዋከብ እና ማሰር ርቀን ሳንሔድ አምና ከነበረው አንፃር እንኳ ልዩነቱ የትየለሌ ነው። ለዚህ የራሴን ስሜት እና ተሞክሮ ነው በምሳሌነት የማቀርበው። በፊትም አሁንም ሐሳቤን በነጻነት እገልጻለሁ። ነገር ግን አምና እና ካቻምና ከያንዳንዱ ጽሑፎቼ/ንግግሮቼ ቀጥሎ እስር ይመጣል እያልኩ እየሰጋሁ ነበር የማደርገው። አሁን ምን ያክል ይዘልቃል የሚለው ቢያሰጋኝም እታሰራለሁ እያልኩ በየደቂቃው አልባትትም። በፊት ሲያስሩ፣ ሲያዋክቡ እና ሲከስሱ ከነበሩት አንዳንድ ኃላፊዎችም ጋር ባጋጣሚዎች አውርቻለሁ። ከላይ ለውጥ ያለ ሲመስል እነርሱም ከታች ይለወጣሉ። አንድ ከፍተኛ የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊ የኛን እንቅስቃሴ "የበፊቱ አመራር እንደ ወንጀል ያየው ስለነበር ወንጀል ነበር። አሁን ግን እንደወንጀል አይታይም" ብለውኛል። ይህ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች ላይ የተፈጠረው የ"ለውጥ መጥቷል" ስሜት እና የፍርሐት ማጣት ከተጠቀሙበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ትልቅ ዕድል ነው። ሌላው ሌላው ሁሉ ለዘለቄታው ለመቅረፍ ረዥም የፖለቲካ እና የሥራ ባሕል አብዮት የሚፈልግ ፈርጀ ብዙ የሁላችንም ችግር ነው።
አሁን ስጋቴ ከግዜ ጋር የሚደረገው ፉክክር ነው። ጊዜ መጨቆኛ መዋቅሩን ለተቆጣጠሩት ጨቋኞችም፣ ባዶ እጃቸውን ለገጠሟቸው ተጨቋኞችም ዕኩል ነው የሚነጉደው። ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) "ጊዜ ከደጋጎች ይልቅ ክፉዎቹ የተሻለ የሚጠቀሙበት ይመስለኛል" ብሎ ጽፎ ነበር። ለዚህ ነው ማንም መጣ ሔደ ለመሪዎች ለውጥ ማስኬጃ በሚል ሰበብ አላግባብ ጊዜ መሸለም የማያስፈልገው። እውነተኛው ለውጥ በተቋማት ለውጥ እንጂ በሰዎች ለውጥ አይመጣምና!
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁ ተልዕኮ የ2012ቱ የኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ ምርጫ ነጻ እና ርትዓዊ እንዲሆን ማድረግ ነው ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ይህን "ብዙ መጠበቅ" ነው ብለውታል የኢትዮጵያን ጉዳይ በመተንተን የሚታወቁት ፈረንሳዊው ሬኒ ሊኾርት። እሳቸው እንደሚሉት ኢሕአዴግ የውስጥ ልዩነቱን ፈትቶ ሠላም ካላላገኘ፣ አገሪቱም ሠላም አታገኝም። ተረኩ የፓርቲውን መበተን ከኢትዮጵያ መበተን ጋር የሚያስተካክል ነው። የፓርቲው አባላት ሁሉንም ክልላዊ መዋቅሮች በተቆጣጠሩበት እንዲሁም አማራጭ የተደራጁ ኃይሎች በሌሉበት ሁኔታ ይህ አይሆንም የሚባል አይደለም። ነገር ግን ይህ የኢሕአዴግ ውስጣዊ ክፍፍል ተቀርፎ የሥልጣን መደላድል ከመጣ ሁሉም ነገር ወደነበረበት የጭቆና አዙሪት ይመለሳል የሚል ስጋት አለኝ።
የጠ/ሚኒስትሩ የሥልጣን ምንጭ ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኢሕአዴግ ውስጥ የተቃዋሚውን ቋንቋ በመናገር ነው ለሥልጣን የበቁት። በዝግ ስብሰባቸው ምን እንደተመከረ፣ ምን ዓይነት የማመቻመቻ ድርድር/ቃልኪዳን አድርገው አብላጫ ድምፅ ለማግኘት እንደቻሉ አናውቅም። ዞሮ ዞሮ መርጠው ለዚህ ያበቋቸው የኢሕአዴግ አባላት ናቸው። የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር (ኃይለማርያም ደሳለኝ) ያለግዜያቸው እንዲለቁ፣ እሳቸውም ከኢሕአዴግ ባፈነገጠ አካሔድ የኢሕአዴግን ሥልጣን እንዲቆናጠጡ ያደረጋቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነው። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ምንጭ ኢሕአዴግ እና ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በጣምራ ነው። ይህ በሥልጣን ዘመናቸው ሊሠሩ የሚችሉትን ማመላከቻ ነው። በርግጠኝነት ኢሕአዴግን ማፍረስ አይፈልጉም፤ ምናልባት ማደስ ግን ይፈልጋሉ። በምን ዓይነት መንገድ? ምናልባትም ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በመመለስ። ተቃርኖው የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው።
የኢሕአዴግ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) ትልቁ ችግር ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በራሱ አውጥቶ፣ መልሱንም በራሱ መንገድ መስጠት ነው። ዴሞክራሲ ደግሞ በተቃራኒው ሕዝብ ችግሩን እንዲናገር በመፍቀድ እና ችግሩን በመቀበል፣ መፍትሔው ከሕዝቡ ፍላጎት አኳያ እንዲመለስ ማድረግ ነው። ይህ ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚያስገኝ አሠራር ግን የኢሕአዴግን ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥልበት ይችላል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልባቸው የያዙት፣ በቅንነት የተመራ የለውጥ ፍላጎት ካለ ይህንን ፈተና ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለባቸው። የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያለባቸው መልሶቹ ኢሕአዴግን ወደመቃብር የሚልኩት ቢሆንም እንኳን ነው። ይህ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢስማሙባቸው እንኳ በዝግ መክረው ለመረጧቸው የኢሕአዴግ አባላት የሚያስማማቸው ይመስላችኋል? እኔን ያጠራጥረኛል።
በ2012 ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ሜዳውን ለሁሉም ዕኩል ማደላደል እና ሁሉንም አካላት ማሳተፍ ነው። በርግጥ ምርጫ ቦርድ ያለበትን አድሎ ቀርፎ፣ ለማንም ወገንተኛ ባልሆኑና ልምዱና የትምህርት ዝግጅቱ ባላቸው ሰዎች ቢመራ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን የፖሊስ እና ደኅንነት አካላት (ከሥልጣን ያዥው ውጪ ያሉት) ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እና መራጮችን ማዋከብ ማቆም አለባቸው። የተሰደዱ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶችም ተስፋ አስቆርጦ ያሰደዳቸው እና ነፍጥ ያስነሳቸው መንስዔ ተቀርፎ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ዋስትና መስጠት የግድ ነው። ይህንን ለማድረግ በአንድ ወገን "ሁሉን ዐቀፍ ድርድር መደረግ አለበት" የሚል ሙግት አለ። የዚህ ሙግት ዋነኛ አራማጅ በቅርቡ ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው። በሌላ በኩል "ድርድሩ የግድ አያስፈልግም" የሚሉም ወገኖች አሉ። ለምሳሌ ፖለቲከኛው ግርማ ሰይፉ ጋር በአንድ ጫወታችን መሐል 'ተቃዋሚው ከኢሕአዴግ ጋር የግድ መደራደር የለበትም። ኢሕአዴግ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ ለነጻ ውድድር የምርጫ ሜዳውን በሐቅ ካመቻቸለት ከዚያ በኋላ ያለው የተቃዋሚው ሥራ ነው'። እርግጥ አሁን ከውስጥም ከውጭም ያለው ግፊት ከፊል ፍሬ አፍርቶ፣ "ለውጥ አይመጣም" ከሚል ድፍንፍን ያለ ግዜ "ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣ ይሆን?" ወደሚል ጉጉት ተሸጋግረናል። ይህንን የለውጥ ተስፋ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ብዙ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ባለው የተዝናና ሁኔታ ለቀጣዩ ምርጫ አገሪቷን ቢያዘጋጁ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች አፈር ከላሱበት ተነስተው በውስጣዊ ወጀብ የሚሰቃየውን ኢሕአዴግ መፈተናቸው አይቀሬ ነው። ፈተናው ኢሕአዴግን ወደለመደው ጫወታ የመመለስ ዕድሉም እንዲሁ ሰፊ ነው። ምናልባት አቶ ዐብይ አሕመድ፣ አቶ ለማ መገርሳና ጥቂት የለውጥ ፊቶች በምርጫ ክልላቸው በብልጫ ያሸንፉ ይሆናል። ነገር ግን በሌሎቹ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሕዝቡ ላይ ግፍ ሲያደርሱ የነበሩ የኦሕዴድ ካድሬዎች ለሕዝቡ ጥቅም ሲታሰሩ ሲፈቱ የከረሙትን የኦፌኮ አባላትን አያሸንፉም። ከኦሮምያ ውጪም ተመሳሳይ ሁኔታ ይኖራል። ኢሕአዴግ ይህን ፈታኝ ሁኔታ በተለመደው የማዋከብ፣ የማሳደድ እና የማሰር ስልት ለመጋፈጥ የሞከረ ዕለት ደግሞ የተካበው ተስፋ ሁሉ ይናዳል። ጫወታው ፈረሰ፤ ዳቦው ተቆረሰ!
በአንድ ወቅት ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር ቃለ ምልልስ ሳደርግ፣ "ኢትዮጵያን የሚያተራምሳት ዴሞክራሲ ማጣት አይደለም፤ የዴሞክራሲ ተስፋ ማጣት ነው" ብሎኝ ነበር። እውነትም የዛሬውን አገራዊ መረጋጋት ስንመለከተው በተስፋ ላይ የቆመ መረጋጋት ነው። የዚህ ተስፋ መፍረስ፣ የሚያፈርሰው ብዙ ነገር ነው።
በሥልጣን መጫወት፣ በእሳት መጫወት!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐቀኛ የለውጥ ፍላጎት ካላቸው፣ 'ይህ በኔ ዘመን አይከሰትም' ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ይህ ግን የሰውን ራስ ወዳድ ተፈጥሮ እንዲሁም የሥልጣንን አባላጊነት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ብዙዎቹ የዓለማችን አምባገነኖች በአንድ ወቅት ሐቀኛ የለውጥ አርበኞች ነበሩ። አንዴ የሥልጣን መደላደል ከፈጠሩ በኋላ ግን በምናባቸው በሚፈጥሩት "የለውጡ ጠባቂነት" ሚናቸው ተሸፍነው ከቀዳሚዎቻቸው የበለጠ ጉዳት ያደርሳሉ። ብዙዎቹ የለውጥ አርበኞች የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ በሚል ሰበብ አስባብ ለረዥም ግዜ ሥልጣን ላይ ይከርማሉ፣ የሚያምኗቸውን ሰዎች ብቻ መርጠው ቁልፍ ቦታ ላይ ይሾማሉ፣ የለውጥ ሒደታቸውን የተቃወሙትን 'አድኀሪያን' በፈርጣማ ጡንቻዎቻቸው ይጨፈልቃሉ፣ በመጨረሻም 'ለውጥ' የሚሉት የራሳቸውን ሥልጣን ተቆናጦ መቆየት ብቻ እስኪመስል ድረስ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናሉ - በአጭሩ አምባገነን ይሆናሉ። ከለውጥ አምጪነት፣ መለወጥ ያለበት አካል ወደ መሆን ይሸጋገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለውጪያዊ መረጋጋት እና ለውስጣዊ መስማማት ግዜ ባገኙ ቁጥር፣ ሰው ናቸውና በሥልጣን የመበላሸት ዕድላቸውም ሰፊ ነው የሚሆነው። የሥልጣን መደላደል "ከእኔ ወዲያ ላሳር" ወደሚል ትምክህት ይመራቸዋል። ስለዚህ ከላይ "አሁን ያለው የተዝናና ሁኔታ" ያልኩት በእርሳቸው ይሁንታ ብቻ የመጣው መልካም ጊዜ ለፈተና ግዜ አይፀናም። ሹመኞች በጭንቅ ግዜ የማይገቡት ቃል የለም። ዕውቁ ፖለቲከኛ አንዷ-ዓለም አራጌ "we are victims of broken promises" ('እኛ የተከዱ ቃልኪዳኖች ሰለባ ነን') ያለው በጭንቅ ግዜ የተገቡ ቃል ኪዳኖች፣ በመረጋጋት ግዜ ስለሚዘነጉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለገቧቸው ቃልኪዳኖች ማስተማመኛ አስቸኳይ ሕጋዊ ዋስትና ይስጡ። የሚሻሩት ዐዋጆች አሁኑኑ ይሻሩ፣ የሚሻሻሉት ዐዋጆች አሁኑኑ ይሻሻሉ፣ የሚጨመሩት ድንጋጌዎች አሁኑኑ ይጨመሩ… የተቋማት ገለልተኝነት ሥራ መሠረቶች አሁኑኑ ይጣሉ… ለቀጣዩ ምርጫ ያለው መሰናዶ በሕግ እና ተቋማዊ አግባብ በአስቸኳይ ይፈፀሙ። የፖለቲካ ዕርቅ ጥሪዎች በነቢብ ሳይሆን በገቢር ይደረጉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ነገሮች በማለዳ ማድረግ ከቻሉ ብዙዎቹ ለውጥ-ፈላጊ የዓለማችን ሰዎች ከወደቁበት ገደል ይተርፋሉ። ሥማቸውም "ከአብዮት ከዳተኞች" ተርታ ሳይሆን፣ ምናልባትም ከዘመን ባንዴ ብቻ ከተከሰቱት "ከጨቋኞች መሐል የወጡ የነጻነት ፋና ወጊዎች" - ከእነ ፍሬድሪክ ደ ክላርክ ተርታ ይመደባሉ። ምርጫው የእርሳቸው ነው፤ ራስን ከራስ ማዳን ወይም በሥልጣን መጫወት።
Comments
Post a Comment