"የአማራ ሥነ ልቦና" በሚል ርዕስ ቀደም ሲል የጻፍከት አጭር የእንግሊዝኛ መጣጥፍ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል። የጽሑፉ ዋነኛ ዓላማ ስለአማርኛ ቋንቋ ዕድሜ፣ ወይም ስለአማራ ሕዝብ ኅልውና ባይሆንም፣ ብዙዎቹ አንባቢዎች ግን የተረዱት በዚያ መንገድ ነበር። ወሳኙ ቁም ነገር እኔ የጻፍኩበት ዓላማ ሳይሆን አንባቢ ጋር ሲደርስ የሰጠው ስሜት ስለሆነ ይህንን ጽሑፍ አስከትያለሁ።
በመሠረቱ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት፣ እኔ የምፈልገው ዘውግ-ዘለል የዜግነት ብሔርተኝነት (civic nationalism) ነው፡፡ ይህን ስል ግን የዘውግ ብሔርተኝነትን እና በዘውግ መደራጀትን እቃወማለሁ ማለቴ አይደለም፤ በዘውግ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች እስካሉ ድረስ ያንን በመከልከል ማስቆም ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የዘውግ ቡድኖችን እና ፍላጎቶቻቸውን አቻችሎ በአንድ ለማኖር የዜግነት ብሔርተኝነት ማበበ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በዘውግ ስለተዋቀሩ እና የመንግሥታዊ አደረጃጀቱም ይህንን (ለዜግነት መብቶች በርዕዮተዓለም መደራጀት) ምቹ ሁኔታ ስላልፈጠረለት አገሪቷ የፉክክር ቤት ሆናለች። ስለሆነም፣ ይሔ እና መሰል ጽሑፎች፣ በአገራችን የተንሰራፋው በአሁኑ ወቅት የበለጠ ተቀባይነት ያለው የዘውግ ብሔርተኝነቱ አካሔድ ቢያንስ ወደፊት ወደ ዜግነት ብሔርተኝነትን እንዲያድርግ የማደርገው ጥረት አካል እንደሆነ ይታወቅልኝ።
አሁንም ከዚህ በፊት "የተጣመመ የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ" በሚል የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጆች ላይ አስተዋልኩት ብዬ የጠቃቀስኩት የጠራ ዘር እና የዘር ሐረግ በመቁጠር ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነት አዝማሚያ “ገና አፍላ ነው” በሚባለው የአማራ ብሔርተኝነት ላይም በጉልህ ያስተዋልኩ መሆኑ የጽሑፌ ዋና መነሻ ነው፡፡ የጠራ ዘር ፍለጋ እና የዘር ቆጠራ ፍልስፍና፣ ዘውግ ወይም ብሔርተኝነት ማኅበራዊ ሥሪት መሆኑን ክዶ በደም የሚወረስ ከማስመሰሉም በተጨማሪ፣ መሠረታዊ መብቶችን ለመጣስ ሰበብ ሆኖ ሊመጣ ይችላል።
ዶ/ር አድማሱ ከበደ ‹የአማራ ብሔርተኝነት ከተለመደው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የተለየ መንስዔ ይዞ ነው የተነሳው› በማለት ሲተነትኑ፣ ‹ከአማራ ብሔራዊ መነቃቃት አስቀድመው ብሔራዊ መነቃቃት ያገኙት ሌሎች የኢትዮጵያ የዘውግ ቡድኖች እንደሌላ ስለቆጠሩት (othering) የተፈጠረ ብሔርተኝነት ነው› ብለው ጽፈዋል::
በዚህ ግንዛቤ በታሪክ አማራ ማነው? አማርኛስ የማነው? እና የአማርኛ የዝግታ ዕድገት ዛሬ አማራ ስለምንለው ሕዝብ ‹ሌላነት› የሚነግረን ነገር አለ? የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳትና መልስ በመፈለግ የአማራ ብሔራዊ (የዘውግ ማንነት) መሠረቶች ምንነት ላይ መላምት አሳልፋለሁ። ይህም የአማራ ብሔርተኝነት ከዜግነት ብሔርተኝነት ጋር በመርሕ የማይጋጭ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የውይይት ዕድል በመስጠት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እምነት አለኝ።
ስለ አማርኛ እና አማራ፤
የታሪክ እና የጥናት መዛግብት ምን ይላሉ?
የደርግ መንግሥት የብሔረሰብ ጥናት ለማስደረግ ባደራጃቸው ምሁራን ተጠንቶ፣ ዶ/ር ፍስሐ አስፋው በ2008 ያሳተሙት “የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጥ ጥናታዊ መዘክር” ስለ አማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ የሚከተለውን ይናገራል፡፡ “የአማርኛ ቋንቋ በጽሑፍ ላይ ከዋለ ስድስት መቶ ዓመታት ሆኖታል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በ14ኛው መቶ ዓመት ተቀርጾ የተገኘው የአማርኛ ጽሑፍ እጅግ ጥቂት ነው፡፡ የጽሑፉ ዓይነት ደራሲው ካልታወቀ ለነጋሢዎች የተገጠመ ቅኔ ነው፡፡ ቅኔው በዘመናት ውስጥ አንድ ቋንቋ እየተለዋወጠ ለመሔዱ ምስክር ከመሆኑ በላይ ዛሬ የማንናገረው፣ የማንጽፈውና ለመረዳት የማንችለው የሰዋሰው አካሔድና የቃላት አገባብ አለበት፡፡ አማርኛ እንደገና ለ300 ዓመታት ያህል ሳይጻፍ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በ17ተኛው መቶ ዓመት ብቅ አለ፡፡ እንደዚህ ሲወድቅ ሲነሳ ኖሮ በ19ኛው መቶ ዘመን አጤ ቴዎድሮስ የመንግሥታቸው ይፋ ቋንቋ ሲያደርጉት አማርኛ የግዕዝ ቦታን በመያዝ የመንግሥት ጉዳይ የሚከናወንበት የጽሑፍ ቋንቋ ሆኗል፡፡”
ፕሮፌሰር ስርግው ሀብለሥላሴም ‘Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270’ በተባለው መጽሐፋቸው (ገጽ 2፣ 4፣ 179 ላይ) ቋንቋው ከ13ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ “ልሳነ ንጉሥ” ይባል እንደነበር ገልጸው፣ የነገሥታቱ ዜና መዋዕል እና ሸንጎ ግን ይመዘገብ የነበረው በግዕዝ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ግዜ ግን ታሪኩ ተለውጦ የንጉሡ የሸንጎ ጸሐፌ ትዕዛዝ አለቃ ዘነብ የዐፄውን ዜና መዋዕል በአማርኛ ጽፈዋል፡፡ በተጨማሪም አለቃ ወልደማርያም የተባሉ እና ሌላ ሥማቸው ያልታወቀ አንድ ጸሐፊ የንጉሡን ታሪክ በግል ተነሳሽነት በአማርኛ በመጻፋቸው አማርኛ ይፋዊ የመንግሥት የጽሑፍ ቋንቋ ብሎም ሌሎች ጸሐፍትንም የሚቀናቸው ቋንቋ ሆነ፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት “A Social History of Ethiopia” በሚለው መጽሐፋቸው (ገጽ 317 ላይ) “[በዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን] ዋነኛው (principal) የጽሑፍ ቋንቋ - ግዕዝ በአማርኛ መተካቱን” የወቅቱ የለውጥ አብዮት አካል አድርገው ይወስዱታል፡፡ ፓንክረስት አክለውም፣ “[ዳግማዊ ቴዎድሮስ] በጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ምትክ አማርኛን ማስተዋወቁን ሳያበረታታው አይቀርም፡፡ በዚሁ ምክንያት ይመስላል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በአማርኛ እንዲተረጎሙለት ያስደረገው” ብለዋል፡፡
ዶ/ር አንበሴ ተፈራ “የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎቻቸው አጭር ቅኝት” በሚል ባሰፈሩት አጭር ጥናታዊ መጣጥፍ “ግዕዝ ከ13ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መነገር በማቆሙ ቀሰ በቀስ በሰሜን ትግርኛ፣ በማዕከላዊው ክፍል ደግሞ አማርኛ የግዕዝን ቦታ ያዙ” ብለው ጽፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ አፈታሪክ “አማርኛ የተፈጠረው የዮዲት ጉዲትን ጥቃት ሸሽተው ሸዋ ውስጥ በገቡ የሸዋ መኳንንት ነው” የሚል ነገር አለ፡፡ “ወሬሳው ካሣ” በሚል ርዕስ በ2005 የታተመ መጽሐፍ ላይ መርጌታ ግሩም ተፈራ የተባለ ጸሐፊ ትርክት እንዲህ ተጠቅሷል፣ ‹የአክሱም መግባቢያ የነበረው ግዕዝ ነው፡፡ ደብተራዎች አሁንም ድረስ ነገረ-ደብተራ የሚባል የምሥጢር መግባቢያ በየጊዜው ይፈጥራሉ፡፡ ኋላ ዮዲት ባመፀች ጊዜ፣ አክሱማውያን መኳንንት ሸሽተው ሰሜን ሸዋ አንኮበር ተሸሸጉ፡፡ እዚያም ለምሥጢራዊነት ሲባል ነገረ ደብተራን ይጠቀሙ ጀመር፡፡ ሌላው ሰፋሪም የመኳንንት ቋንቋ አገኘሁ ብሎ ይናገረው ጀመር፡፡› (ገጽ 230) ይሄንኛው አፈ ታሪክ ቢያንስ ቋንቋው በተፈጠረበት ዘመን እና ቦታ ላይ ትክክል አለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ በቋንቋው አመጣጥ ላይ የሚወራው ግን ስህተት መሆኑን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም፡፡ አለቃ ታየ ገብረማርያምም የዕድሜውን ጉዳይ ውድቅ ያድርጉታል፤ ሆኖም በሌላ ጥናት ተገልጾ እንደሁ ማረጋገጥ ያልቻልኩትን ዕድሜ ለአማርኛ ይሰጡታል - ከይኩኖአምላክ በፊት 1,640 ዓመት በፊት የነበር ነው በማለት፡፡
ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታልም፡፡ ዶ/ር አንበሴ “አማርኛ ልሳነ ንጉሥ የሆነው በ1272 ከዛጔ ሥርወ መንግሥት በኋላ ይኩኖ አምላክ ሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት መልሶ ሲያቋቁም ነበር። አማርኛ ልሳነ ጽሑፍ መሆን የጀመረው በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን ይህንንም ያደረገው ሁሉንም የግዕዝ ፈደላትን በመውሰድና 6 አዳዲስ የላንቃ ፊደላትን (ማለትም ሸ፣ ቸ፣ ኘ፣ ዠ፣ ጀ፣ ጨ) እና ኸን በመጨመር ነበር። ነገር ግን በጽሑፍ ይበልጥ መስፋፋት የጀመረው ከዐፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ሲሆን ለዚህም በተለይ አስተዋጽኦ ያደረገው ጸሐፊያቸው ደብተራ ዘነብ ነው።”
ዶ/ር አንበሴ ፕሮፌሰር ባየ ይማምን (“የአማርኛ ሰዋስው” (1986፡ ገጽ 4-5)) አጣቅሰው “አማርኛ የተወለደው በሴማውያን መሪዎችና በካማውያን (ኩሻውያን) ወታደሮች መካከል በተፈጠረው ግንኙነት ሳቢያ ቋንቋዎቻቸው በመደባለቁ ነው። ስለሆነም አማርኛ ቅይጥ ቋንቋ (pidgin) እንጂ ንጹሕ ሴማዊ አይደለም” ይላሉ፡፡ “ለምሳሌ ያህል መሠረታዊ ቃላት ሳይቀሩ ከኩሽ (ካም) የተዋሳቸው ናቸው። ምሳሌ፡- ውኃ፣ ውሻ፣ ሰንጋ፣ ወዘተ. ግሱ በዓረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ ስለሚመጣ የዓረፍተ ነገር ቅርፁም ሴማዊ አይደለም።” ዎልፍ ሌሳሉ የተባሉ የውጭ ምሁር የኢትዮጵያ ኩሽ ቋንቋዎች በሴም ቋንቋዎች ላይ ያሳረፉትን ተፅዕኖ በተነተኑበት ጥልቅ ጥናት ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ሌሳሉ እንደሚሉት “በጥቅሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች (አማርኛን ጨምሮ) ከሰሜን ኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች (ግዕዝን ጨምሮ) ይልቅ የኩሽ ቋንቋዎች ተፅዕኖ አርፎባቸዋል”፡፡ ይህንንም ተፅዕኖ በጥናቱ ሲያሳዩ ድምፀት፣ ብዜት፣ ቅድመ/ድኅረ ቅጥያ፣ ቃላት እና የግስ፣ ሥምና ተጠሪ አደራደርን ጨምሮ ሌሎችንም አማርኛን ጨምሮ (የደቡብ ኢትዮጵያ ሴም ቋንቋዎች ምድብ ውስጥ ያሉ ሌሎች ቋንቋዎችም) ላይ የኩሽ ቋንቋ ያሳረፈውን አሻራ የሚስረዱ 30 የቋንቋ ጥናት አላባትን ከአስረጅ ምሳሌዎች ጋር ዘርዝረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የዶ/ር ፍስሐ አስፋው “የጥናት መዘክር”ን ጨምሮ ሌሎችም ጥናቶች “የአማራ ታሪካዊ ጥንተ መካን በወሎ ክፍለ አገር፣ በቦረና አውራጃ ልዩ ሥሙ ‹አማራ ሳይንት› የተባለው ወረዳ እንደሆነ” ያትታሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ወረዳ የዛሬው ወይም ለዛሬው የቀረበ አማርኛ ይነገር እንደነበር የሚያስረዳ በኔ ኀሠሣ ምንም ምንጭ አላገኘሁም፡፡ እንዲያውም አለቃ ታየ “አምሃራ ወይም አማራ ማለት አራሽ ማለት ነው፡፡ ሳይንት ማለትም ባረቢኛ የእህል ማከማቻ ጎተራ ማለት ነው” ብለው ጽፈዋል፡፡ በዚያ ላይ ይህ ወረዳ ዛሬ የአማራ ትልቅ አካል የሆኑትን ‹መርሀቤቴ፣ ይፋትና አንጎት /የጁ/፣ በጌምድር (የዛሬው ጎንደር)፣ እና ጎጃምን አይጨምርም› ነበር፡፡ እንዲያውም “የአማራ ሳይንት አንድ ክፍል በ19ኛው ክፍለ ዘመን በኦሮሞዎች ተሞልቶ እንደነበር” ዶናልድ ሌቪን (ዶ/ር) “Three Faces of the Oromo Struggle” በሚለው ጥናታዊ መጣጥፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ “Amharic Speakers and the Question of Nationalities” በሚለው ‘ethiopianreview.com’ ላይ እ.ኤ.አ. በኤፕሪል 18፣1992 በታተመ አጭር ጥናታዊ መጣጥፋቸው “አማራ የሚኖሩት ብቻ ነበሩ አማራ የሚባሉት” ይላሉ፣ አማራ ሳይንትን የጠቀሱ በሚመስል መልኩ፡፡ ቀጥለውም፣ “ባልታወቀ ምክንያት፣ የአማራዎቹ ቋንቋ ከአማራ ውጪ ተሰራጨ፡፡ በተለይም ጎንደር፣ ጎጃም፣ ላስታ እና ሰሜን ሸዋ (መንዝ፣ ተጉለትና ቡልጋ በመባል የሚታወቁት) እነዚህ አካባቢዎች አማርኛ ከመልመዳቸው በፊት ሌላ ቋንቋ ነበር የሚናገሩት” በማለት ብዙ ዝርዝር ሳይሰጡ ያልፋሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በሰነድ ደረጃ፣ “በ1274 ከግብጽ ካሊፋ የተላከ ደብዳቤ የኢትዮጵያን ዐጤ “የአማራ ንጉሥ” ይለዋል፤ በ1412 በአማርኛ የተጻፈ አንድ ታሪካዊ ጽሑፍ ደግሞ “የአማራ ጅር” ይላል፡፡” (ዶ/ር ፍስሐ) ከነዚህ ሰነዶች ውጪ ከ17ኛው ክፍለዘመን በፊት “አማራ” የሚለው ቃል እንዳልተጠቀሰ የዶ/ር ፍስሐ “የጥናት መዘክር” ይጠቅሳል፡፡ በአማርኛ ቋንቋ እና በዛሬው የአማራ ሕዝብ መካከልም ቀጥተኛ አያያዥ መኖር አለመኖሩን ከዚህ የተሻለ ማስረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡
መጀመሪያ በ1914 የታተመውና ቀደም ሲል የጠቃቀስኩት የአለቃ ታየ ገብረማርያም “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፤ ባጭር የወጣ ቃል” (በ2008 በድጋሚ የታተመ) እንደሚለው “አማራ ግን ከወዴትም አልመጣም፡፡ ጥሩ የላስታ ወታደር፣ ከያይነቱ [የ]ተጠራቀመ፣ ኃይለኛ፣ ግፈኛና አድመኛ፣ ዕውቀት ያለው፣ ያልተማረ ጭፍራ ነው፡፡” በመቀጠልም አለቃ ታየ “መንግሥቱ የአማርኛ ስለሆነ አማርኛ ሠለጠነ” ይላሉ፡፡ “ልዩ ልዩ ሕዝብ ቋንቋቸውን እያጠፉ አማርኛን የሚናገሩ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ እኒህም ደምቢያዎች፣ ቋሮች፣ ጋፋቶች፣ የወሎ ኦሮሞዎች፣ የጆች ወይም ወረሴሆች ናቸው፡፡”
የአማራን ሕዝብ ባሕል እና ታሪክ በጥልቀት ያጠኑት ዶናልድ ሌቪን ‘Greater Ethiopia’ በተሰኘው ትልቅ ጥናታዊ መጽሐፋቸው፣ የኢትዮጵያን አፈጣጠር (ተፃምሮን/synthesis/) ሲያስረዱ በአማራ አንብሮ (thesis)፣ በኦሮሞ ተፃርሮ (anti-thesis) እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህን ካሳተሙ ከሁለት ዐሥርት ዓመተታት በኋላ በአጭሩ በጻፉት ‘Greater Ethiopia Reconsidered’ በሚለው መጣጥፋቸው (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን አጣቅሰው) ስለአማራ ሕዝብ ዳራ ሲጽፉ “ዛሬ አማራ የምንለው አንድ የዘውግ ቡድንን አይወክልም፤ ይልቁንም ቋንቋውን በዘመናት ሒደት የወረሱ ከብዙ የዘውግ ቡድኖች የተውጣጡ የአንድ ቋንቋ ማኅበረሰብ ነው” በማለት “አሁን በአፋን ኦሮሞ ተናጋሪነት እንደተሰባሰቡት እና ቀድሞ ራሳቸውን ቦረን፣ ጉጂ፣ ጂማ እና ወዘተ ብለው ይጠሩ እንደነበሩት ሕዝቦች” አማርኛም ተናጋሪዎቹን በአንድ ቋንቋ ማዕቀፍ አሰባስቦ የተፈጠረ እንደሆነ ጽፈዋል፡፡
ይህንን በአማርኛ ቋንቋ መሥፋፋት የተፈጠረ የአማራ ሕዝብ ታሪክዊ ማንነት ማገናዘብ የአማራ ብሔራዊ መነቃቃትን በጤናማ መንፈስ እንዲያድግ፤ እንዲሁም ከሌሎች የዘውግ ቡድኖች ጋር የሚኖረው መስተጋብርም ጤናማ እንዲሆን ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተመሳሳይ የሌሎች የዘውግ ቡድኖች ስብስቦችም ይህንን የአማራ ሕዝብ ሥነ ፍጥረት እና ሥነ ዕድገት መረዳታቸው ከአማራ ሕዝብ ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት እመርታ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
የአማራ ሕዝብ ሥነልቦና እና ግለኝነት
እ.ኤ.አ. በ2006 ዶ/ር አድማሱ ከበደ ለዶክትራል ዲግሪያቸው ያሰናዱት “The Invention of Amhara Nationalism: Ethnicity and National Identity in Ethiopia” የሚል ጥልቅ ጥናት እንደሚያስነብበን ‹አንድ ብሔር ወይም ዘውግ በብሔር የ“ተገምቢነት” ንድፈ ሐሳብ (“constructionist perspective”) መሠረት “አለ” የሚባለው አባላቱ አለ ብለው ሲያምኑ ነው ይለናል›፡፡ እንደሚታወቀው ደግሞ በኢትዮጵያ የትኛውም የዘውግ ቡድን አባላት የአማራን ያክል “ዘውጌ የለም” ብለው አልተከራከሩም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ወቅታዊ ሒደቶች እንደሚያሳዩት እና እኔም እንደማምነው፣ በአሁኑ ወቅት ብዙኃን የአማራ ክልል ነዋሪዎች “አማራ ነኝ” ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም በቀላሉ የብሔሩን ኅልውና ያረጋግጥልናል፡፡ ዶ/ር አድማሱም በመደምደሚያቸው ይህንኑ ያነሳሉ - “አሁን እንደ አማራ ብሔር አባል ተወልደው ያደጉ አዋቂዎች አሉ” በማለት፡፡ ዶ/ር አድማሱ እዚህ ድምዳሜ ከጻፉት ደግሞ ዐሥር ዓመት አልፏቸዋል፡፡
የተለያዩ ምሁራን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ) “አማራ” የሚለው ቃል ከዘውግ ይልቅ ሃይማኖትን (ክርስትያን መሆንን) ይገልጽ ነበር ያሉት ክርክር ትክክል እና አሁንም ድረስ ያልከሰመ አገላለጽ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ቢያንስ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ብቻ ቃሉ፣ በተገላቢጦሽ፣ ከሃይማኖት ይልቅ ብሔርን ለመግለጽ ውሏል ማለት ከእውነታው የራቀ ግምት አይመስለኝም፡፡
“የአማራ ሥነ ልቦና” ብዬ ለመጻፍ ስነሳ ግን ደጋፊ የጽሑፍ ማስረጃ እንደሚቸግረኝ ግልጽ ነበር፡፡ ነገር ግን የአማርኛ ቋንቋ እና የዛሬው የአማራ ሕዝብ ያለፈ ታሪክ (የተጻፈውም ያልተጻፈውም)፣ ከወቅታዊው ስርዓተ ፖለቲካ ጋር አማሮች ያላቸው መስተጋብር፣ እንዲሁም እኔ ዕድሜ ልኬን የነበርኩበት፣ ያየሁት እና የታዘብኩት (ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የዘውግ ቡድን የበለጠ የማውቀው መሆኑ) የሚሰጠኝን የምስክርነት መብት ነው ይዤ የተነሳሁት፡፡ (ይህ ድምዳሜዬ የማይስማማው በተቃራኒው መሞገት ወይም ንቆ መተው ይችላል፡፡)
በዚህም መሠረት በአገራችን በየትኛውም ክፍል ያሉትን የአማራ ተወላጆች በሙሉ (exceptions ብዙኃኑን ስለማይገልጹ ከግምት ውስጥ ባለማስገባት) የሚያመሳስላቸው ባለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለታሪኮች መኩራት እና መመካት ነው፡፡ ይህንን ማንንት የፈጠረው ታሪካዊ አመጣጣቸው እና ለማዕከላዊው መንግሥት የነበራቸው ቀረቤታ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ምናልባትም የአማራ ተወላጆች የዘውግ ማንነታቸውን የሚክዱት እና በብሔር መደራጀትን ሲገፉ የኖሩት በዚህ የወል ሥነልቦናቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ ዓይነቱ በታሪክ እና በባለታሪክነት የመኩራት የወል ሥነልቦና የሚያሳፍር ማንነት ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ተሳስተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ኩራቱም ይሁን በባለታሪክነት መመካቱ በግል ደረጃ መወሰን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
በቀዳሚው ጽሑፌ ያነሳሁት ሌላኛው ጉዳይ ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል “ግለኝነት” (individualism) ብለን የምንተረጉመው “የአማራ የወል ባሕሪ” ነው፡፡ ዶናልድ ሌቪን “Wax & Gold” በሚል ርዕስ ያሳተሙት እና የአማራን ባሕላዊ ልምዶች በጥልቀት የተነተኑበት መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ስለ አማራ የግለኝነት ባሕሪ ጽፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምዕራፉን ሲጀምር ግለኝነት የዘመናዊነት መጀመሪያ ምልክት ነው ተብሎ እንደሚታሰብ እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፣ “a deep-going process of individualization has commonly been regarded as one of features of the early stages of modernization.” ነገር ግን ይህ በድፍን “የግለኝነት” ጽንሰ ሐሳብ ትርጓሜ መወሰድ እንደሌለበት እና የአማራ ግለኝነት የሥርዓተ ማኅበሩ የሞራል መሠረት መሆኑን ለመግለጽ እንጂ አማራ በማኅበር መኖር የማይችል ነው ለማለት እንዳልሆነ ያሳስባሉ፡፡ በርግጥ እነዚህ ጥናቶች የተሠሩት ከ50 እና 40 ዓመታት በፊት በመሆኑ ብዙ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
የአማራን ሕዝብ ግለኝነት ዝንባሌ በልጆች ሥም አወጣጥ ረገድ የተነተኑት ፕሮፌሰር ሳይመን ሜሲንግ የተባሉ ምሁር ደግሞ፣ “Individualistic Patterns in Amhara Onomastics” በሚል ርዕስ ባሳተሙት አጭር ጥናታቸው ላይ የአማራ ሥም አወጣጥ የሕዝቡን ግለኝነት እንዴት እንደሚያሳይ፣ በተለይም በአባታዊ ስርዓተ ማኅበር ውስጥ ለእናቶች የሚሰጠውን ነጻነት እና ፈረንጆች የቤተሰብ ሥም የሚሉትን አለመጠቀሙ የሰጠውን በቤተሰብ ደረጃ የሚንፀባረቅ ነጻነት (independence) በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ የዘረዘርኳቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ለደረስኩበት መላምት በቂ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ የአማራን ሕዝብ ታሪክ በቅጡ ማወቅ እና መረዳት ግን ለብሔራዊ መነቃቃቱ በትክክለኛ አቅጣጫ መያዝ ወሳኝ ቁም ነገር የሆነውን መሆኑ አጠያያቂ አይመስለኝም፡፡ የአማራን ሕዝብ የወል ሥነልቦናውን፣ ወግ እና ልማዱን መረዳትም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በአንድ እና ሁለት መጣጥፎች ብቻ የሚቋጭ ሳይሆን፣ ጫፍ አልባ ውይይት የሚጠይቅ ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡
የአማራ ብሔርተኝነት
ከላይ የተዘረዘረው የአማርኛ ቋንቋ እና በዚያውም የዛሬው የአማራ ሕዝብ አመጣጥ ታሪክ ሲነገር “አማራን የስርዓተ ማኅበሩ ግንድ፣ ሌሎች የዘውግ ቡድኖችን ደግሞ ቅርንጫፍ ለማድረግ ነው እንዲህ የሚለው ታሪክ የተፈጠረው” በማለት የሚያጣጥሉት የሌላ ዘውግ ብሔርተኞች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ትልቁ ተቃውሞ የሚነሳው ከአማራ ተወላጆች መሆኑ በአንድ በኩል የአማራ ብሔርተኝነት እያደገ መሆኑን ሲያመላክት፣ በሌላ በኩል የአማራ ብሔርተኞች በአማራ ታሪክ ላይ በቂ ውይይት እንዳላደረጉ ያሳብቃል፡፡ ይህም፣ የዚህን እና የቀደመውን መጣጥፍ አስፈላጊነት ያረጋግጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ዶ/ር አድማሱ ከበደ የአማራ ብሔርተኝነት ከሌሎች ዋና ዋና የኢትዮጵያ የዘውግ ቡድኖች ብሔራዊ መነቃቃት ዘግይቶ መጀመሩን ይጠቁማሉ፡፡ የትግራይ ብሔራዊ መነቃቃት አንጋፋው እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፣ የኦሮሞ ብሔራዊ መነቃቃትም ቢያንስ ግማሽ ምዕተ ዓመት ቆይቷል፡፡
ብዙ የአማራ ተወላጆች ራሳቸውን ከዘውግ ማንነት በላይ ኢትዮጵያዊ (“supra-ethnic Ethiopianist”) አድርገው እንደሚቆጥሩ በብዙ ጥናቶች ተጠቅሷል፡፡ እንዲያውም ጋዜጠኛ መኮንን ሚካኤል፣ እ.ኤ.አ. በ2008 በሠራው “Who is Amhara?” በሚል ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ የአማራን ብሔራዊ መነቃቃት የበላይነት ስሜት (“consciousness of superiority”) ሲል ይገልጸዋል፡፡ አማርኛ የትምህርት ቋንቋ ከሆነ በኋላ ያለውን ሁኔታ ሲገልጽ፣ “አማርኛ ሌሎችን የመዋጫ (assimilation) ባሕል ሆነ፤ ነገር ግን በተጨማሪም በተናጋሪዎቹ ላይ የበላይነት ስሜት አፈራ፡፡ ይህ በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአደባባይ ባሕል ሆኖ በግልጽ ተስተውሏል፡፡ አማራ[ነት] የምሁሩ ልኂቅ ባሕል ሆኗል” ይላል፡፡ ነገር ግን የዛን ጊዜው የአማራ መነቃቃት ከአሁኑ ጋር ተመሳሳይ አይመስለኝም፡፡
“ብሔሮች በአዋጅ አይፈጠሩም" በማለት የአማራ ብሔርተኝነት ብዙዎች እንደሚያስቡት በመንግሥት ሕዝቡ ላይ ስለተጫነ ብቻ አልተፈጠረም በማለት የሚከራከሩት ዶ/ር አድማሱ ከበደ ጥናታቸው “የአማራ ብሔርተኝነት ከዘውገኝነት የርስበርስ ትስስር ተረቶች፣ ትውስታዎች እና ትዕምርቶች አንፃር ሳይሆን በሌሎች ዘውግ ፖለቲከኞች መገለል (Othering) ሳቢያ የተፈጠረ ግብረ ምላሽ ነው” የሚለውን ቁም ነገር ያስጨብጣል። ብዙ ታሪካዊ የዘውግ ብሔርተኝነቶች የሚፈጠሩት የመገንጠል ወይም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር ሲመሠረቱ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ግን በመገለል የመጣ ራስን የመከላከል ፍላጎት መፈጠሩ ልዩ ያደርገዋል።
በርግጥም የኢትዮጵያ የዘውግ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያን ታሪካዊ ችግር “በብሔር ጭቆና” ሲመድቡት “ጨቋኝ” በማለት የሚያስቀምጡት “የአማርኛ ተናጋሪ ገዢ ልኂቃንን” መሆኑ ብዙም አያከራክርም፡፡ አልፎ ተርፎም የአማራን ሕዝብ በሙሉ ጠቅልሎ የጨቋኝ ወገን (“ነፍጠኛ”) እንደሆነ እና ያለፉት ስርዓት ናፋቂ (“አድኀሪ”) አድርጎ የመመልከት የተለመደ አካሔድ አለ፡፡ ይህን ነው ዶ/ር አድማሱ “የአማራ ብሔርተኝነት የተቋቋመበት የመገለል (othering) ስሜት” የሚሉት፡፡ እንደ እርሳቸው ‹በተለይ የኢሕአዴጉ ኦሕዴድ እና ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብ ወዳጅ ለመምሰል ባደረጉት ፉክክር አማራን ማላላት (Amhara bashing) አንዱ መሣሪያቸው መስሎ ታይቷል›፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ይህንን አስተሳሰብ ለመከላከል ከተቋቋመ - በእኔ እምነት - ከላይ በማስረጃ ለመተረክ ከሞከርኩት የአማራ ታሪክ በላይ መከላከያ የለም፡፡
ጋዜጠኛ መኮንንም ይሁኑ ዶ/ር አድማሱ ስለ አማራ ብሔራዊ መነቃቃት አስፈላጊነት ከተነገሩ ንግግሮች መካከል የሚጠቅሱት አሁን የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በወኅኒ የሚገኙት የአንዳርጋቸው ፅጌን ጽሑፍ በማንሳት ነው፡፡ ጋዜጠኛ መኮንን የጠቀሱት የአቶ አንዳርጋቸው ጽሑፍ (በኔ ትርጉም) “ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዘውግ ፖለቲካ ነው፡፡ ከፍተኛ የዘውገኝነት ስሜት ያላቸው የዘውግ ቡድኖችና የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ… በዚህም እንደ አማራ በዘውግ ያልተደራጁ የዘውግ ቡድኖች በመሐል ቤት ይጎዳሉ… አማራው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ማድረግ አለበት? ብቸኛው መውጫ መንገድ በዘውግ መደራጀት ነው” የሚል ነው፡፡ ይህ ሙግት (አማራጭ ሊኖረው ቢችልም) እንዳለ ይኑርና የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናንሳ፣ የአማራ ብሔራዊ ድርጅቶች ለምን ጥልቅ ሕዝባዊ ዕውቅና አጡ? (ብአዴንን መውሰድ ይቻላል፤) የአማራ ብሔራዊ ድርጅቶች ለምን በቀላሉ ይፈርሳሉ/ይዳከማሉ? (መአሕድን መውሰድ ይቻላል፤) ብዙ የአማራ ተወላጆች “አማራው በዘውግ መደራጀት ያስፈልገዋል” ካሉ በኋላ ዘውግ-ዘለል ወይም ኅብረ-ብሔራዊ የፖለቲካ ስብስብ የሚመሠርቱት ወይም አባል የሚሆኑት ለምንድን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ከአማራ ታሪክ፣ ወግና ልማድ አንፃርስ እንዴት ነው የሚታዩት?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የመጣጥፌ ዓላማ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጫፍ አልባ ውይይት ማነሳሳት ነው፡፡

Comments
Post a Comment