Pages

Sunday, September 17, 2017

የአራማጅነት ሀሁ…

‘አክቲቪዝም’ በአማርኛ ቁርጥ ትርጉም አልተገኘለትም። እንዲሁ በየዐውዱ "የለውጥ አራማጅነት"፣ "የመብቶች አቀንቃኝነት"፣ ወዘተ… ነው የሚባለው። የእንግሊዝኛ ቃሉን ግርድፍ ትርጉም ከወሰድን "ንቁ ተሳታፊ" ከሚለው የሰፋ ትርጉም የለውም። በኢትዮጵያ ቃሉ በተደጋጋሚ መደመጥ የጀመረውና ራሳቸውን ‘አክቲቪስት’ ብለው የሚጠሩ ሰዎች የተከሰቱት ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማደግ ጋር ተያይዞ ነው። በተለምዶ፣ ቃሉ በጥቅሉ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያደርጉ እና የሚወክሉት ድርጅት የሌላቸውን ግለሰቦች በሙሉ ለመግለጽ እየዋለ ነው። እዚህ ጽሑፍ ላይ የምጠቀምበት ገላጭ ሆኖ ያገኘሁትን "አራማጅነት" የሚለውን ቃል ነው።

አራማጅነት ምንድን ነው? 

አራማጅነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና/ወይም አካባቢያዊ ለውጦችን ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። አራማጅነት የአጭር ግዜ ፕሮጀክት ወይም ዘላቂ ንቅናቄ ሊሆን ይችላል። አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ወይም ብዙ ጉዳዮችን ያቀፈም ሊሆን ይችላል። አራማጅነት በብዙኃኑ ተቀባይነት ያለውን አንድ ጉዳይ በመንግሥት ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ወይም በመንግሥት ዕውቅና ያለውን ጉዳይ በብዙኃኑም ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ወይም በብዙኃኑም፣ በመንግሥትም ተቀባይነት እና ዕውቅና የሌለውን ጉዳይ በሁለቱም ተቀባይነት እና ዕውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። አራማጅነት በብዛት ከተገለሉ ሕዳጣን ወይም ከተጨቆኑ ብዙኃን መሐል በወጡ አራማጆች የሚደረግ የመብት/የጥበቃ ንቅናቄ ነው።

የአራማጅነት ስኬት እንደመነሻው ነው የሚለካው። አንዳንዴ የተነሳውን ሐሳብ የተደራጁ ሲቪል ማኅበረሰቦች ወይም የፖለቲካ ማኅበሮች አጀንዳዬ ብለው ሲይዙት ከአራማጆች እጅ ሊወጣ ይችላል። ሌላ ግዜ ደግሞ የተጠየቀውን መብት/ጥበቃ የሚያጎናፅፍ አዋጅ ሲወጣ ሊቆም ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ የወጣው አዋጅ እና መመሪያ አፈፃፀምን እየተከታተለ፣ የተፈለገው ማኅበራዊ የግንዛቤ ለውጥ እስኪመጣ ሊቀጥል ይችላል። እንዲሁም ቀድሞ የወጣ አዋጅ ወይም የተዘረጋ ስርዓት እስኪሻር ወይም በሌላ እስኪተካ የሚደረግ አራማጅነትም አለ። በተግባር ደረጃ የማድረግ ወይም ያለማድረግ (ሌሎችንም እንዲያደርግ ወይም እንፋያደርጉ የማግባበት) ንቅናቄ ነው።

አራማጅነት የዓለማችን ዘመናዊ ባሕል ሆኗል ማለት ይቻላል። ቃሉ በዚህ ፖለቲካዊ ይዘቱ ከተመዘገበ የመቶ ዓመት ያክል ዕድሜ ይሆነዋል። ከጊዜ ግዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ የበይነመረብ (ኢንተርኔት) ዘመን ላይ የእያንዳንዱን ጓዳ የሚያንኳኳበት ዕድል አግኝቷል።

አራማጆች ለጋዜጦች በመጻፍ፣ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን፣ ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ የአዳራሽ ስብሰባዎችን እና ንግግሮችን በማካሔድ፣ በኪነ (ሥነ) ጥበብ ሥራዎች በመግለጽ፣ ብዙኃንን ያሳተፈ የእግር መንገድ ዘመቻ በማድረግ፣ ለቀናት ያክል ድንኳን በመደኮን፣ በሰላማዊ ሰልፎች፣ በአድማዎች፣ በማዕቀቦች፣ ያልተፈለገውን ተግባር (ወይም ሌላ አትኩሮትን የሚስብ) የለት ተለት ተግባርን በማስተጓጎል፣ ወዘተ… የሚዲያ፣ የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የፖለቲካ፣ የአካባቢያዊ እና ሌሎችም ተፅዕኖዎችን በመፍጠር ጉዳዩ መጀመሪያ ትኩረት እንዲስብ፣ ቀጥሎ ወደ ተግባራዊ ለውጥ ጉዞ እንዲጀመር የሚያስገድዱ ንቅናቄዎችን ይፈጥራሉ።

የኢትዮጵያውያን አራማጆች የተለመዱ ስህተቶች

በአገራችን አራማጅነት ከሆነው ይልቅ ያልሆነው ነው እንደአራማጅነት የሚቆጠረው ማለት ይቻላል። ለዚህ ምክንያት ሊሆን የሚችሉት የዳበረ የፖለቲካ ባሕል አለመኖሩ፣ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር እና ተዳራሽነት ውሱን መሆኑ፣ የሐሳብ ነጻነት አለመከበሩ እና የመሳሰሉት ናቸው። የሚከተሉት ነጥቦች ዋና ዋናዎቹን ችግሮች ነቅሰው ያወጣሉ ብዬ እገምታለሁ።

1ኛ፣ ትኩረት አልባነት፦ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን አራማጆች በሁሉም ጉዳይ ላይ መሳተፍ ስለሚፈልጉ በአንዱም ላይ ጉልህ አሻራ ማሳረፍ ሳይችሉ እንዲሁ እንደባከኑ ይቀራሉ።

2ኛ፣ ተደራሲውን አለመለየት፦ ብዙ የኢትዮጵያውያን አራማጆች የሚያራምዱት ጉዳይ የሚመለከተውን አካል እንዲደርስ እና አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያመጣ ከመጣር ይልቅ ለመሰሎቻቸው  ብቻ በማቅረብ በርስበርስ ሙገሳ እና ውዳሴ ውስጥ ቀልጠው ይቀራሉ።

3ኛ፣ የቃላት አጠቃቀም ጉድለት፦ የኢትዮጵያውያን አራማጆች ትልቁ የተለመደ ችግር ለውጥ እንዲያመጣ የሚፈልጉትን አካል በመዝለፍ ቢጤያቸውን ለማስደሰት መጣር ነው። ይህ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ መፍትሔ አያስገኝለትም። ለውጥ እንዲያመጣ የሚፈልጉትን አካል ሰብኣዊ ክብር እና መብቶች ሳይደፈጥጡ በጋራ ለችግሮች መፍትሔ ለመፍጠር የመጋበዝ ልምድ በአገራችን አልተለመደም።

4ኛ፣ መሬት አለመርገጥ፦ የአገራችን አራማጆች ምናባውያን ወይም፣ ወይ በጋዜጣ አልያም በኢንተርኔት ብቻ ተወስነው መቅረታቸው የተለመደ ችግራቸው ነው። ተግባራዊነት፣ እንዲሁም መሬት የረገጠ አራማጅነት ጉዳዩን በርግጥም አንድ ደረጃ ወደፊት ያራምደዋል።

5ኛ፣ ሙያን ከዓላማ አለመለየት፦ በተለይ ፖለቲከኝነት እና ጋዜጠኝነት ከአራማጅነት ጋር ሲምታቱ ይስተዋላል። አራማጅነት ወደ ፖለቲከኝነት፣ ወይም ጋዜጠኛ ወደ አራማጅ ፖለቲከኝነት ሊሸጋገሩ ይችላሉ። ነገር ግን አራማጆች ተገቢ ያልሆነን ነባራዊ እውነታ ለመለወጥ የሚታገሉ ሲሆኑ፣ ፖለቲከኞች ግን የሚወክሉትን ሕዝብ ፍላጎት ያስፈፅማሉ፣ ጋዜጠኞችም ነባራዊውን እውነታ ሪፖርት ያደርጋሉ እንጂ የራሳቸውን ፍላጎት ሊያስፈፅሙበት፣ ወይም የሚመኙትን ሊነግሩት አይችሉም። ነገር ግን አራማጆች ከጋዜጠኞች እና ከፖለቲከኞች ጋር ተመጋጋቢ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ። አራማጅነት ከሌሎች ሙያዎችም ጋር የሚኖረው ግንኙነት በዚህ መልኩ ስለማይታይ እስካሁን ያለው ሒደት ላይ በአገራችን ስለሙያዎቹ ብዙ የተሳሳተ ገጽታ እየፈጠረ ነው። አራማጅ እንደፖለቲከኛ ለፖለቲካ ስልት ብሎ መርሑ ላይ አይደራደርም፤ ወይም እንደ ጋዜጠኛ መረጃ ብቻ ሰጥቶ አቋሙን አይሸሽግም።

6ኛ፣ መንታ ምደባ (ለመርሕ አለመታመን)፦ የብዙ ኢትዮጵያውያን አራማጅነት የተለመደ ስህተት ሁለት ተመሳሳይ ድርጊቶችን በሁለት የተለያዩ (የጠላትና የወዳጅ) ዓይን መመልከት እና መዳኘት ነው። የአራማጅነት መርሑ "ለወዳጅ" የሚሻርበት፣ "ለጠላት" ደግሞ የሚከርበት አካሔድ እጅግ የተለመደ ነገር ግን ጎጂ ስህተት ነው።

እነዚህ ስህተቶች ለአራማጆቹ ጊዜያዊ ፈንጠዝያ የሚያድሉ ቢሆንም፣ ዘላቂ ለውጥ ግን ማምጣት አይችሉም። ስለዚህ መታረም አለባቸው።

የአራማጅነት ፈተናዎች

የአራማጅነት መንገዱ ጨርቅ አይደለም። አራማጅነት ለዓላማ ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት ነው ሊባል ይችላል። አራማጆች ከተራ ፍረጃ ቀዬን ለቆ እስከ መሰደድ፣ ከእስር እስከ መገደል የሚያደርስ ጦስ ይዞ ሊመጣ ይችላል። በዓለማችን በየዓመቱ ከመቶ በላይ አራማጆች ይገደላሉ። በአገራችንም አራማጅነት በእሳት እንደመጫወት ነው። ነገር ግን ብዙዎቹ አራማጆች ዓላማቸውን ብቻ ሳይሆን የተጋረጠባቸውንም አደጋ ያውቃሉ። የልባቸው ጉትጎታ እረፍት አልሰጥ ስለሚላቸው ነው አደጋውን የሚጋፈጡት።

አንዳንድ አራማጆች ማንነታቸውን ደብቀው አደጋውን ለመቀነስ ይሞክራሉ። ራሳቸውን ደብቀው ስኬታማ አራማጅነት ያካሔዱ አራማጆች ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ ስኬታማ አራማጆች ግን ለዓላማቸው አደጋውን ለመጋፈጥ ራሳቸውን ይፋ ያደረጉ ሰዎች ናቸው። ምክንያቱም አራማጅነት ስብዕና ይፈልጋል። ይህ ስብዕና ለለውጡ ፈላጊዎች መልካም አርኣያ መሆን የሚችል መሆን አለበት፣ ለለውጡ ተቋቋሚዎች ደግሞ አደጋ እንደማያመጣ (ፈረንጆች win-win እንደሚሉት ዓይነት መሆኑን) ማሳመን የሚችል መሆን አለበት። በዚያ ላይ አራማጆች ለሚሠሩት ሥራ ከነ ውጤቱ ተጠያቂ ለመሆን የተዘጋጁ መሆናቸው፣ ሌላኛውን አካል ለለውጡ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆኑ ያስረዳላቸዋል። ነገር ግን ስኬት አራማጆች ማንነታቸውን እንዳይደብቁ የሚያስፈልጋቸው ብቸኛ ምክንያት አይደለም። አራማጆች ለአደጋ በተጋለጡ ግዜ ዕውቅናቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጥበቃ ያደርግላቸዋል።

የአራማጅነት ደረጃዎች

ብዙ አራማጆች ወደ አራማጅነት የሚገቡት ሳያስቡበት በአጋጣሚ ነው። አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ባለማድረጋቸው በደመነፍስ ሲወራጩ ከማየት በቀር ወደ ውጤታቸው በተገቢው ፍጥነት ሲገሰግሱ አይታዩም። እንዲያውም በማይጠቅሟቸው ተግባሮች ብዙ ኃይላቸውን ያባክናሉ። በተለይም፣ ገና በሁለት እግራቸው መቆም ሳይችሉ (ምን እንደሚፈልጉ እና እንዴት እንደሚያገኙት ሳያውቁ) ለተግባር እንቅስቃሴ በመነሳት ባጭሩ ሲቀጩ ማየት የተለመደ ነው። አራማጅነትን ማንም ከእናቱ ማሕፀን የተማረ የለም። ወደፊት አራማጅ እሆናለሁ በሚል ትምህርት ቤት የሚገቡለትም ነገር አይደለም። አራማጅነት በሕይወት መንገድ ላይ የሚገጥም ዓላማ ነው። ብዙዎቹ አራማጆች የገቡበትን ጉዳይ እና እንዴት ማስኬድ እንዳለባቸው የሚማሩት ከገቡበት በኋላ ነው። ስኬታማዎቹ አራማጆች የጀመሩትን ዓላማ ከግብ የሚያደርሱበትን ትምህርት በሒደት ነው የሚቀስሙት። ዋናው ቁም ነገር ለዓላማው የሚታገሉለትን መርሕ ማግኘትና ለመርሑ ሁሌም ታማኝ ሆኖ መቆየት ነው። ቀጥሎ የምዘረዝራቸው ስኬታማ አራማጅ ለመሆን ይረዳሉ ብዬ የማስባቸው ደረጃዎች ናቸው። እያነበባችሁ ስትሔዱ እግረ መንገዳችሁን የአራማጅነታችሁን አካሔድ ገምግሙበት። በዝርዝሩ የጎደለ የምትሉት ካለ ጨምሩበት።

ቅድመ ዝግጅት

1) ችግሩን መለየት፦ አንዳንዴ ችግር የሚመስለን የችግሩ ውጤት ሊሆን ይችላል። ሌላ ግዜ ደግሞ ችግር የመሰለን ከራሳችን የግንዛቤ እጥረት የመነጨ ስጋት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የሕይወት ዓላማ ብለን የምንይዘው አራማጅነት የተሳሳተ ችግር (ወይም ችግር ላልሆነ ነገር) የሚባክን ግዜ፣ ገንዘብና ኃይል ሊሆን ይችላልና ትልቅ ጥንቃቄ ይሻል። ችግሩን በአግባቡ ሳንለይ የምንፈልገው መፍትሔ ሁሉ ከንቱ ስለሚሆን ይህ ደረጃ ከሁሉም የበለጠ ትኩረት ይፈልጋል። ስለዚህ የመጀመሪያው መጀመሪያ “የምንታገልለት ችግር ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ እርግጠኛ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል።

2) የመፍትሔ አማራጮችን መዘርዘር፦ ችግሩን ማወቅ የመፍትሔውን ግማሽ ማወቅ ነው ይባላል፤ አባባሉ እውነት ቢኖረውም የተጋነነ ነው። በተለይ በማኅበራዊ ሳይንስ፣ አንድ ችግር እልፍ አማራጭ መፍትሔዎች ይኖሩታል። እያንዳንዱ መፍትሔ የራሱ ጥቅምና ጉዳት ይኖረዋል። ይህን አመዛዝኖ የመፍትሔ አማራጮችን መለየት ቀላል ሥራ አይደለም። ሆኖም ግን ከባድ ነው ተብሎ የሚዘለልም ነገር አይደለም። ስለዚህ በተቻለ መጠን ያሉትን የመፍትሔ አማራጮች መለየት፣ የመፍትሔዎቹን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን፣ መፍትሔውን ተግባራዊ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ የሚፈጀው ግዜ እና ጉልበት፣ ወዘተ… ማጥናት ያስፈልጋል።

3) የተሻለውን መፍትሔ መምረጥ፦ ከተዘረዘሩት መፍትሔች መካከል በዋና ዋናዎቹ መመዘኛ የተሻሉ የሚባሉትን በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ቀጣዩ ሥራ ነው። እንዳስፈላጊነቱ የመፍትሔ አማራጮቹን በማዳቀል የተሻለ አዲስ ዓይነት መፍትሔ ማፍለቅ እንደሚቻል ደጋግሞ መፈተሽ ያስፈልጋል። በመጨረሻም ሁነኛ የሚሉትን መፍትሔ መርጦ መያዝ እና ለተግባራዊነቱ የሚሆን ስትራቴጂ ወደ መንደፍ መሸጋገር ነው።

4) ፍኖተ መፍትሔ ማስቀመጥ፦ ችግሩ ተለይቷል። የተሻለው መፍትሔም ታውቋል። ቀጣዩ ወደ መፍትሔው የሚያደርሰውን መንገድ መለየት ነው። ወደ መንገዱ ለመድረስም ከላይ ተራ ቁጥር ሁለት እና ሦስት የጠቀስናቸውን ዘዴዎች መከተል ይጠቅማል። ወደ ግባችን የሚያደርሱን ምን ምን ዓይነት አማራጭ መንገዶች አሉ? የትኞቹ መንገዶች (ከግዜ፣ ከገንዘብ እና ከሰው ኃይል… አንፃር) አነስተኛ ወጪ ይጠይቃሉ? የትኛው መንገድ ተግባራዊ፣ የትኛው ምናባዊ ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ አዋጪውን ወደ ግብ የሚያደርሰንን ስልት ይዘን መንገዱን መጀመር እንችላለን።

(እነዚህን [ችግሩን ከመለየት እስከ ፍኖተ መፍትሔ መቅረፅ ድረስ ያሉ] ሒደቶችን ስናካሒድ በግል ዕውቀታችን ብቻ መታመን የለብንም። ይህ አስተሳሰብ ስህተት ላይ ይጥለናል። በጉዳዩ ላይ ሌሎች ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች ያላቸውን አስተያየት፣ የምርምር ሥራዎች የሚናገሩትን፣ የጉዳዩን ታሪካዊ መሠረት፣ ተያያዥ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን፣ ዓለማቀፍ ድንጋጌዎችና መርሖዎችን እንዲሁም ሌሎችንም በማገላበጥ ቅድመ ዝግጅቱን ማድረግ ስህተት ላለመሥራትም ይሁን የችግሩን ጥልቀት ተረድቶ ለመዘጋጀት እንዲሁም ጉልበት በከንቱ ላለማባከን ይረዳል።)

አካሔድ

5) ማንቃት፦ የአክቲቪዝም ዋነኛው ሥራው የመወሰን መብት ያላቸውን ብዙኃንን፣ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ልኂቃንን፣ ፖሊሲ አውጪ ፖለቲከኞችን፣ ገንዘብ መዳቢ ባለሀብቶችን እና ሌሎችንም ስለ ችግሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ነው። መቼም፣ ምንም ያክል ብዙ ግዜ የተሠራ ቢሆንም እንኳ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ብዙዎች እንደሆኑ ራስን ደጋግሞ ማስታወስ ያስፈልጋል። ብዙ አራማጆች ስለአንድ ጉዳይ ደጋግመው ከማሰባቸው እና ከመነጋገራቸው የተነሳ ሁሉም ሰው በቂ ግንዛቤ ያለው ይመስላቸዋል። ግን ይህ እሳቤ ብዙ ግዜ የተሳሳተ ነው። የሐሳብ ተዳራሽነታቸውን በየጊዜው ላልደረሰው ማስፋት፣ ለደረሰው ደጋግሞ በተለያዩ መንገዶች ማቅረብ ያስፈልጋል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ በዘመቻዎች፣ በሚዲያ፣ በመጽሐፍት፣ በኪነ(ሥነ)ጥበብ ሥራዎች፣ በውይይቶች፣ በማስታወቂያዎች ወዘተ… መልኩ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

6) ማደራጀት፦ ከግንዛቤ ማስጨበጡ ሥራ ጎን ለጎን መሠራት ያለበት ሥራ ማደራጀት ነው። የተደራጀ የሰው ኃይል የሌለበት አራማጅነት ግቡን መምታት አይችልም። የግንዛቤ ማስጨበጡ ኃላፊነት ከግለሰቦች ወደ ቡድኖች፣ ከቡድኖች ወደብዙኃኑ መሸጋገር አለበት። ስለሆነም ብዙኃኑን ግብ ያደረጉ፣ ፖሊሲ አውጪዎችን ግብ ያደረጉ፣ ልኂቃንን ወይም ሁሉንም ግብ ያደረጉ መደበኛና ኢመደበኛ ድርጅቶች መፈጠር አለባቸው። የተደራጀ በቂ የሰው ኃይል መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ ነው ወደተግባር መግባት የሚያስፈልገው።

7) መተግበር፦ የአደባባይ ሰልፎች፣ የገበያ እቀባ፣ አለመተባበር፣ ማደናቀፍ፣… አብዛኛዎቹ የሕዝባዊ እኝቢተኝነት እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች የመጨረሻ እርምጃዎች ናቸው። ይህንን ለመጀመር መጀመሪያ የነቃ፣ ከዚያ የተደራጀ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። አለበለዚያ የተጠሩ አድማዎች፣ እቀባዎች፣ እምቢተኝነቶች፣ ወዘተ… በቀላሉ ሊከሽፉ ስለሚችሉ አራማጅነቱን ወደኋላ ሊያንፏቅቁት ይችላሉ። ሌሎችን ተስፋ ያስቆርጣሉ፣ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ እና የሞራል ኪሳራቸውም ከፍተኛ ነው። በበቂ ሁኔታ የነቃና የተደራጀ ኃይል ሲያደርጋቸው ግን ግብ የመምታት ዕድላቸው ሰፊ ነው የሚሆነው።

ድኅረ ውጤት

8) ምዘና፦ አራማጆች የሚፈልጉት ለውጥ መምጣቱን የሚያስረግጥ ግልጽ መሥመር ብዙ ግዜ አይኖርም። ምናልባት የሆነ አዋጅ በጥረታቸው ሊወጣ ይችላል፤ ነገር ግን ወሳኙ ቁም ነገር አፈፃፀሙ ነው። ምናልባት በጥረታቸው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሔድ ይችላል፤ ነገር ግን ዴሞክራሲ በምርጫዎች መካከል ባለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ነው የሚለካው። ምናልባት መንግሥት ሊለውጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው በስርዓተ ማኅበሩ ለውጥ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መነሻ ነጥባቸውን ከመድረሻቸው አመዛዝነው፣ ወይ አራማጅነቱን ያቆሙታል ወይ ከልሰው ቀሪውን ክፍተት ለመሙላት ይቀጥሉታል፤ ወይም ደግሞ በአዲስ መልክ እንደገና ይጀምሩታል።

No comments:

Post a Comment