Skip to main content

የተዋሐደን ፆተኝነት

ይህ ጽሑፍ ስለ ፍትሕ ነው። አንባቢዎቼን በትህትና አስቀድሜ የምጠይቀው ነገር ቢኖር የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት መነፅሮቻችሁን አውልቃችሁ በፍትሕ መነፅራችሁ እንድታነቡኝ ነው።

የተዋሐደን ፆተኝነት ስንል ምን ማለታችን ነው? ምንጮቹ ምን ምን ናቸው? ውስጣችን ያለው ይህ ፆተኝነት ምን ያህል ችግር ይፈጥራል? የተዋሐደንን ፆተኝነትን እንዴት እንቅረፈው?

መግባቢያ ስለፆተኝነት

ፆተኝነት ማለት በአጭሩ ‘ፆታዊ መድልዖ’ ማለት ነው። በዓለማችን እጅግ የተንሰራፋው ለወንዶች የሚያደላው ወይም አባታዊው ስርዓተ ማኅበር ነው። (እርግጥ እጅግ ጥቂት ሆኑ እንጂ እናታዊ ስርዓተ ማኅበሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕንድ አገር ሜጋላያ ስቴት ውስጥ የሚገኙት ጎሳዎች ሀብት የሚተላለፈው ከእናት ወደሴት ልጅ ነው፡፡ በዚህ ስርዓተ ማኅበር የትምህርትና መሰል ዕድሎች ከወንዶች ይልቅ ለሴቶች ይመቻቻሉ፡፡ ይህን ምሳሌ በዓለም ከተንሰራፋው አባታዊው ስርዓት አንፃር ከቁብ ሳልቆጥረው ላልፍ እችል ነበር። ነገር ግን የእነዚህ ጎሳዎች እናታዊ ስርዓት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ መድረሱ አባታዊው ስርዓትም ሆነ እናታዊዋ በማኅበራዊ ብሒል የሚገኙ እንጂ ተፈጥሮ ያከፋፈለችን ሚና አለመሆኑን ስለሚያሳይ ነው።) የአገራችን ስርዓተ ማኅበር ከጥግ እስከ ጥግ አባታዊ ነው። ይህንን ስርዓተ ማኅበር ለመቀልበስ እና ፍትሐዊ ስርዓተ ማኅበር ለመመሥረት የሚደረጉ የተደራጁም ይሁን ያልተደራጁ ንቅናቄዎችን ሴታዊነት እንላቸዋለን። (‘እንስታዊነት’ የእንግሊዝኛውን ‘Feminism’ በቀጥታ የሚተካ ቢሆንም፣ አማርኛችን ስርዓተ ፆታ (gender) ያልተጫነው ‘ሴት’ የሚል ሥነ ተፈጥሯዊ (biological) ልዩነቱን ብቻ የሚገልጽ ቃል ስላለው ‘ሴታዊነት’ የሚለውን መርጫለሁ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሴታዊነት ማለት “ፆታዊነትን መቃወም እንዲሁም ሴቶች ከወንዶች ዕኩል መብትና ዕኩል ዕድል እንዲያገኙ መታገል” የሚል ብያኔ ይኖረዋል።)

የተዋሐደን ፆተኝነት…

ስልካችንን የኋላ ኪሳችን አስቀምጠነው ብንሰረቅ ማነው ተወቃሹ? እንዝህላልነታችን ወይስ ሌብነቱ? በመርሕ ደረጃ ሌብነት በማንኛውም ሁኔታ ነውር ነው። ይህ ምሳሌ “ነውር ማለት ሁላችንም በራሳችን ላይ እንዲደረግብን የማንፈልገው ነገር ነው” የሚል ብያኔ እንድናገኝ ይረዳናል። ስለዚህ "ቤታቸውን ከፍተው ሰውን ሌባ ያሰኛሉ" የሚለው አባባል የሌብነትን ነውር አቃልሎ ያሳያል እንጂ አያስቀረውም። ልክ እንደዚህ ሁሉ የሴት ልጅ መደፈርን ነውርነትም እንዲህ በሰበብ ሊያስተባብሉ የሚሞክሩ ብዙ ናቸው። ነገር ግን በአገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ ለሴቷ መደፈር እራሷኑ ተጠያቂ ማድረግ የተዋሐደን ፆተኝነት ማሳያ ነው። ዩጋንዳ በየካቲት 2006 አጭር ቀሚስ የሚከለክል ሕግ አውጥታ ነበር። ከዚያ ቀደም ብለው የወጣቶች ሚኒስትሩ "ጨዋነት የጎደለው አለባበስ የለበሱ ሴቶች ሲደፈሩ ከራሳቸው በቀር ማንም ተጠያቂ መሆን የለበትም" ብለው ተናግረው ነበር። ተመሳሳይ ንግግሮች በሁሉም የአፍሪካ አካባቢዎች የተለመዱ ናቸው። በአገራችንም፣ አንዲት ሴት በወንድ ጥቃት ደረሰባት የሚለው ዜና ሲሰማ ገና፥ “ምን አድርጋው?” የሚለው ምላሽ ይከተላል። ጥያቄው፣ ሴት ልጅ ምክንያታዊ ጥቃት ይገባታል ከሚል የተዋሐደን አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። ለጥቃቱ ከማዘናችን በፊት ቀድሞ የሚመጣብን ጥያቄ “ምን አድርጋው?” የሚለው ከሆነ የተዋሐደን ፆተኝነት ሥር የሰደደ ነው ማለት ነው፡፡

በቅርቡ ይፋ የሆነ (ነገር ግን ውጤቱ ከቀደምት ጥናቶች ጋር የሚመሳሰል) ጥናት እንደሚያስረዳን፣ በኢትዮጵያ 63% የሚሆኑት ሴቶች "ባል ሚስቱን ወጥ ካሳረረች፣ ከጨቀጨቀችው፣ ሳትነግረው ዙረት ከሔደች ወይም መሰል ጥፋት ካጠፋች… ቢመታት ምንም አይደል" ብለው ያምናሉ። ባንፃሩ አሳማኝ ምክንያት ካለ ሴት ልጅ መመታት አለባት ብለው የሚያምኑት 28% የሚሆኑት ወንዶች ብቻ ናቸው። ለምን ሴቶች የገዛ ራሳቸውን ጥቃት ተገቢ ነው አሉ። ለምን ከሴቶቹ ቁጥር ያነሱ ወንዶች መምታቱ ተገቢነት ላይ ተስማሙ? መልሱ ቀላል ነው። የተዋሐደን ፆተኝነት የገዛ ጥቃታችንን በራሱ ተቀባይነት እንዳለው ነገር እንድንቀበለው ያታልለናል። ወንዶች ከሴቶች የተሻለ፣ የትምህርትና የመረጃ ዕድል ስላላቸው የሴት ልጅ ጥቃት በማንኛውም ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን መረዳታቸውንም ውጤቱ ይጠቁመናል። በዚህም ፆተኝነት በትምህርት የሚቀረፍ ነገር መሆኑን በቀላሉ ማየት ይቻላል።

የተዋሐደን ፆተኝነት ከማኅበረሰቡ የተማርነው፣ የኑሮ ዘዬያችን የተገነባበት እና በየዕለቱ የምንከተለው ነገር ግን ጨርሶ የማናስተውለው ከመሆኑ የተነሳ "ትክክለኛ" የሚመስለን ነገር ነው። ሆስፒታል ሔደን ነጭ ጋዋን የለበሰች ሴት ስትገጥመን [ነርስ እንደሆነች እርግጠኛ በመሆን] "ሲስተር" የምንላት፣ ነጭ ጋዋን የለበሰ ሲገጥመን "ዶክተር" የምንለው የተዋሐደን ፆተኝነት አስገድዶን ነው። አንድ ቀን መሳሳታችንን ብናውቅ እንኳን ደግመን መሳሳታችንን እንቀጥላለን፡፡ በተመሳሳይ የቢሮው ሥራ አስኪያጅ እንዲሁ ስናስበው ወንድ አድርገን ነው፤ ጸሐፊዋን ደግሞ ሴት። "ማናጀሩ የታል?" ስንል ወንድ እንደሆነ አንጠራጠርም። የኩሽና ሥራ በጥቅሉ የሴት ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምግብ አብሳይ ስንባል በምናባችን ሴት እንስላለን፤ የትልቅ ሆቴል ሼፍ ስናስብ ግን ወንድ ነው በምናባችን የሚመጣው፡፡ ምክንያቱም ምግብ አብሳይነትም  ቢሆን ደረጃው እያደገ ሲመጣ ለሴት እንደማይገባ የተዋሐደን ፆተኝነት ሹክ ይለናል፡፡
የፍቅር ግንኙነቶች ላይ ወንዱ ራስ፣ ሴቷ ንዑስ ናት፡፡ በታዋቂ የፍቅር ትርክቶቻችን የወንዶቹን ሥም የምናስቀድመው ያለነገር አይደለም፡፡ ሮሚዮ እና ጁልየት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይም አዳምና ሔዋን፣ አብርሃምና ሳራ ሲባል ነው እየሰማን ነው የኖርነው፡፡ ተራ ነገር ይመስላል፤ ነገር ግን አዕምሯችን ወንድና ሴትን የሚያስቀምጥበት ቅደም ተከተል አሳባቂ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ባለትዳሮችን ስንጠራ ‹ባል እና ሚስት› እንጂ ‹ሚስት እና ባል› የሚለው አማርኛ አፋችን ላይ የማይመጣልን፡፡ የተዋሐደን ፆተኝነት በይፋ የሚጋለጠው በንግግራችን ስለሆነ እንጂ በተግባርም (መብትና ዕድል በመስጠት) የምናስቀድመው ወንዱን ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ወንዱን ለቤተሰቡ እንደብቸኛ የገቢ አስገኚ ይቆጥረዋል፤ ስለዚህ የፍቅር ግንኙነቶች በወንዱ የኢኮኖሚ የበላይነት ላይ ነው የሚመሠረተው፡፡ በፍቅር ግንኙነቶች ሴቷ በትምህርት ደረጃ፣ በኢኮኖሚ አቅም፣ በቁመት… ወዘተ በልጣ ከታየች ግንኙነቱ ውስጥ የሆነ ስህተት እንዳለ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም የተዋሐደን ፆተኝነት ያስተማረን እና አምነን የተቀበልነው መብለጥ የወንዱ ድርሻ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

የወሲብ ግንኙነታችን ሳይቀር ለወንዱና ሴቷ የተለያየ ነገር እንደሆነ አስመስሎ የተዋሐደን ፆተኝነት ይነግረናል። ጥንዶች ፍቅር ሲሰሩ ወንዱ ‘አድራጊ’ ሲሆን፣ ሴቷ ‘ተደራጊ’ ነች ተብላ ነው የምትታሰበው። በዚህ አይወሰንም፣ ድርጊቱ ለእሱ ጀብዱ ሲሆን፣ ለሷ ግን እንደብልግና ይቆጠራል። በአንድ ቀን ትውውቅ አንድ ወንድ ከሴት ጋር ቢያድር እሱ በጀብድ ሲደነቅ፣ እሷ በአመንዝራነት ትወቀሳለች። ሴት ስትሰደብ ‘ሸርሙጣ’ ተብላ ከሆነ፣ ወንዱ ግን ‘የሸርሙጣ ልጅ’ ነው የሚባለው። አድሎው በስድብ ሳይቀር ይንፀባረቃል። ‘እናትህ እንዲህ ትሁን’ የሚለው ስድብ የሚሆነው በሴቷ ዙሪያ ስለሚያጠነጥን ነው። ብቻውን የሚኖር ወንድ ላጤ ይባላል፤ ላጤ የሚለው ቃል ውስጥ ‹አንድ ብቻ› ከመሆን በስተቀር የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ሴት ግን ብቻዋን ስትኖር ‘ጋለሞታ’ ነው የምትባለው፤ መንፈሱ ሴት ካለወንድ ዋጋ የላትም የሚል ነው። ‘ጋለሞታ’ የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሲተረጉመው እንዲህ ነው፣ “1. ዕድሜዋ ለትዳር ደርሶ ያላገባችና ብቻዋን የምትኖር ሴት፡፡ 2. ባል አግብታ የሞተባትና ብቻዋን የምትኖር ሴት፡፡ 3. ሸርሙጣ፣ አመንዝራ ሴት፡፡ 4. ባል ፈታ ብቻዋን የምትኖር ሴት፡፡”

የሃይማኖት አመለካከቶች

በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ሰዎች የክርስትና እና እስልምና እምነቶች ተከታይ ናቸው፡፡ የሕዝቡ ባሕልም በሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም እምነቶች ወንድን የበላይ፣ ሴትን የበታች አድርገው ይስላሉ፡፡ ጉዳዩ ከሥነ ፍጥረት ይጀምራል፡፡ በሁለቱም እምነቶች አምላክ ወንዱን ከፈጠረ በኋላ ሴቲቱን ከወንዱ አካል ስባሪ ነው የፈጠራት፡፡

በክርስትና ለሰው ልጅ ከገነት መባረር ተወቃሽዋ ሴት ናት፡፡ ለዚህም “በፀነስሽ ግዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፡፡ ፈቃድሽም ወደባልሽ ይሆናል፡፡ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ይላል (ዘ ፍጥረት 3/16)፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አንቀፆች አሉ። "ቅዱስ" መጽሐፎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገሮች መጻፋቸው ያስደነግጣል። ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓያቆብ "ይህ የሙሴ ሕግ ሴትን ከፈጠረ አምላክ የመጣ ሊሆን አይችልም" ያለው። ነገር ግን መሰል አንቀፆች ያሉት በኦሪት ብቻ ሳይሆን በአዲስ ኪዳንም ጭምር ነው፤ ወደቆሮንቶስ ሰዎች 1ኛ፣ ምዕራፍ 11፣ ቁጥር 3 ‹የሴት ራስ ወንድ ነው› ይላል፡፡ ብሉይ ኪዳን የዘር ሐረግ ሲቆጥር የወንዶቹን ነበር የሚቆጥረው፤ ሐዲስ ኪዳን ላይ ደግሞ የሕዝቦች ብዛት ሲጠቀስ የሴቶችን እና የሕፃናትን ቁጥር አይጨምርም፡፡

በእስልምና ሥሟ ቁራን ላይ የተጠቀሰችው ብቸኛዋ ሴት መሪየም ናት፡፡ በተጨማሪም (የሴቶች ምዕራፍ እየተባለ በሚጠራው) ምዕራፍ 4፣ ቁጥር 11 ላይ “አላህ በልጆቻችሁ (ውርስ በሚከተለው)፣ ያዛችኋል፣ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ቢጤ አለው” በማለት በቁጥር አንድ ወንድ የሁለት ሴቶች ዋጋ እንዳለው ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡ በተመሳሳይ፣ ምዕራፍ 2 (አል-በቀራህ) ቁጥር 282 ላይም ለምስክርነት ከአንድ ወንድ ጋር ዕኩል የሚቆጠሩት ሁለት ሴቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡

እምነቶቻችን ከልጅነታችን እስከ እውቀታችን ድረስ ሲሰበኩልን ያደግን እንደመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበልባቸው እዚህ የደረሱ እንደመሆኑ መጠን ውስጣችን የተዋሐዱ አስተሳሰቦችን የመቅረፅ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ሥነ ጽሑፍ፣ ጥበብ እና ሚዲያ

“ድንበር ስታቋርጥ የተገኘች በሕግ ትቀጣለች” የሚል ማሳሰቢያ ብትመለከቱ ለወንዱም ተግባራዊ የሚሆን ይመስላችኋል? “ድንበር ሲያቋርጥ የተገኘ በሕግ ይቀጣል” የሚል ቢሆንስ? ይህ የተዋሐደን ፆተኝነት ውጤት ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ‹ሰው› የሚለውን በተባእታዊ ፆታ ሲገልጹት በውስጠ ታዋቂነት ሴቷ መኖሯ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ በእንስታዊ ፆታ ብንገልጸው ግን የሚሠራው ለሴቷ ብቻ ነው፡፡ በጉልህ ስንመለከተው ችግር ያለው አይመስልም ምክንያቱም ሴቷን ንዑስ የማድረጉን ነገር የተዋሐደን ፆተኝነት እንደ “ትክክል” (normal) እንድናየው አለማምዶናል፡፡

ብዙ ቃላቶቻችን እና ተረትና ምሣሌዎቻችን ፆተኝነት የተዋሐዳቸው ናቸው፡፡ እኛ ግን ሳናስተውል በየዕለቱ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ይህም ማለት አስተሳሰቦቹን በማኅበረሰባችን እናፀናባቸዋለን፤ ለቀጣዩ ትውልድም እናወርሰዋለን፡፡

የጥንት እና መካከለኛው ዘመን ፈላስፎችም ስለሰው ልጅ ሲጽፉ ሴትን እየገደፉ ነው፡፡ ጆን ሎክ ’ሁሉም ሰዎች የተወለዱት ዕኩል ነጻ ሁነው ነው’ (“All men are born equally free”) ብሎ ከጻፈ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ እነቶማስ ጀፈርሰን የአሜሪካንን “ሁሉም ሰዎች ዕኩል ነው የተፈጠሩት” የሚል መሪ ሐረግ ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ በመክተት የወንዶች (በርግጥ ያውም የነጭ ወንዶች ነው) መንግሥት መሥርተዋል፡፡ ምንም እንኳን በእንግሊዝኛው ‘man’ የሚለው እና በአማርኛ ‘ሰው’ የሚለው ለወንዱም፣ ለሴቷም የወል መጠሪያ መስሎ ቢታይም፣ ሴቷን እንዴት ሊገድፍ እንደሚችል ከላይ የጠቀስነው ጥሩ ማሳያ ይመስላል፡፡

ቮልቴር የፈረንሳይ አብዮትን ያነሳሳ ጸሐፊ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የቮልቴር ፍትሐዊነት ሴት ጋር ሲደርስ ይቆም ነበር፡፡ ‹ካንዲድ› የተሰኘው የተውኔት ሥራው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ይባላል፡፡ ቮልቴር ሴትን አሳንሶ ከማየቱ የተነሳ በጣም የሚወዳትን ሚስቱን ሲያቆላምጣት “ሴት ከመሆኗ በቀር እንከን የሌለባት ሰው” እያለ ነበር፡፡ የዓለምን ልማዳዊ አስተሳሰብ የፈተኑ ፈላስፎች ሳይቀሩ በዚህ ጉዳይ ወድቀው ተገኝተዋል። ዕውቁ ፈረንሳዊ ፈላስፋ ዣን ዣክ ሩሶ “የሴቶች ተግባር መሆን ያለበት ባሎቻቸውን ማስደሰት፣ ማፍቀር፣ ማገልገልና መጥቀም እንዲሁም ሕፃናትን ማስተማር፣ መንከባከብና ማሳደግ ነው። ሴቶች የሚማሩት ትምህርትም በዚህ ዓላማ መቀረፅ አለበት" ብሏል። ይህንን የሚያስተጋቡ ዛሬም አሉ። የሴትን ተፈጥሯዊ የመውለድ ፀጋ ለባርነቷ እንዲዳርጋት የሚከራከሩት የተዋሐደን ፆተኝነት ቢጋርዳቸው እንጂ ከክፋት አይመስለኝም።

የታይም መጽሔት ከዓመታት በፊት ‹ፓሪስ ሒልተን፣ ሊንድሴይ ሎሃን እና ብሪትኒ ስፒርስ› የዱርዬ ባሕሪ አሳዩ ተብሎ ትልቅ አጀንዳ በሆነበት ግዜ ‹Girls gone bad› (ሴቶች መረን ወጡ) የሚል አስተያየት አትሟል፡፡ ሦስት ዝነኛ ወንዶች በየፊናቸው ጋጠ ወጥነት የተሞላበት ድርጊት ቢያደርጉ (ያደርጉማል) ግን ‹ወንዶች ሁሉ ተበላሹ› የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ይወጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በቅርቡ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስኮትላንዷ ቀዳማይ ሚኒስትር ጋር ኒኮላ ስቱርጂዮን ጋር ያደረጉትን ስብሰባ በሽፋን ገጹ ይዞ የወጣው ‹ዴይሊ ሜይል› የተባለ ጋዜጣ እንደትልቅ ጉዳይ ያወራው አጭር ቀሚስ ለብሰው እግራቸው መታየቱን ነበር (‘Never mind Brexit, who won Legs-it’)፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥ የወንድ መራሔ መንግሥታት ስብሰባ ላይ አለባበሳቸው የሽፋን ገጽ ዜና ሆኖ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ (ከተዋሐደን ፆተኝነት አንፃር “የወንዶቹ አለባበስ ኖርማል ስለሆነ ነው” የሚል አስተያየት ሰጪ እንደማይጠፋ እገምታለሁ፡፡)

‘የቤክዴል ፈተና’ የሚባል ፊልሞች ላይ የሚደረግ የሴታዊነት ፈተና አለ፡፡ መለኪያው ቀላል ነው፡፡ ፊልሙ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሴት ገጸ ባሕሪዎች ወንድ በሌለበት ትዕይንት ላይ ቀርበው ከወንድ ውጪ ሌላ ወሬ ካላወሩ ፊልሙ ፈተናውን ይወድቃል፡፡ ይህንን ፈተና የምንወዳቸው ፊልሞች ሁሉ ይወድቃሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ደራሲዎች የእውነታውን ዓለም ስለሚያንፀባርቁ [ብቻ] አይደለም፤ የተዋሐደን ፆተኝነት ሴቶች ከወንዶች ውጪ አጀንዳ የላቸውም ብለው እንዲያስቡ ስለሚያስገድዳቸው እና በዚያው መሠረት ገጸ ባሕሪዎቻቸውን ስለሚስሉ ነው፡፡ የአገራችን ፊልሞች የፆታ መድልዖን ለማውገዝ ገጸ ባሕሪ ሲፈጥሩ አይታዩም፡፡ ይልቁንም የፆታ መድልዖውን የሚና ክፍፍል እንደሆነ ለማሳመር ሲውተረተሩ እንጂ፡፡

የአገራችን ጋዜጠኞች እና ጸሐፍት መጽሐፍም ይሆን መጣጥፍ ሲጽፉ ሴት አንባቢ ያላቸው አይመስሉም፡፡ “አንባቢ ሆይ፣ ከዚህ በመቀጠል የምጽፍልህ ታሪክ…” ዓይነት ይዘት ያለው ትረካ ይከተላሉ፡፡ ይህ ግን ድንገት የበቀለ አይደለም፡፡ የጥንት ሊቃውንት ሲጽፉ ያነበናል ብለው የሚያስቡት ወንዱን ብቻ ስለነበር፣ ለተባእት አንባቢ ነበር የሚጽፉት፡፡ የጥንት አዋጆች አገር የወንዱ እንደሆነ ነበር የሚናገሩት፡፡ ዐፄ ዮሐንስ (አራተኛ) አገርን በእናት፣ በሚስት፣ በሴት ልጅ ሲመስሉ እያናገሩ ያሉት ወንዱን መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የአድዋ ጦርነትን ሲያውጁ “ያለህን ይዘህ ተከተለኝ” ሲሉ ለወንዱ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ ሴቷ ምንም እንኳን ከዘማቹም ከደጀኑም ወገን ብትኖርም በአዋጅ ለመጠራት ቁብ አትበቃም ነበር፡፡ ይህ ዘመን ተሻግሮም አልቀረም፡፡ ዛሬ፣ ዛሬ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲያወጡ እና የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ ገዢው ፓርቲ ያደረሰብህን በደል እኔ አቀልልሃለሁ” በማለት ነው፡፡ አገርን የተባእቱ ብቻ ማድረግ የተዋሐደን ፆተኝነት ክፉ ስጦታ ነው፡፡

የአባት ውርስ

የአባታዊው ስርዓተ ማኅበር ክብርን ከአባት ወደ ወንድ ልጅ ነው የሚያወርሰው፡፡ በቅርብ ግዜ በአዋጅ እስከሚቀየር ድረስ አባት እና እናት ያፈሩት ሀብት እና ንብረት ሕጋዊ ወራሽ ወንድ ልጅ ነበር፡፡ ሴት አማራጭ ሲጠፋ ነው አባቷን የምትወርሰው፡፡ በፖለቲካውም፣ የአባቱን ንግሥና ለመውረስ የሚበቃው ወንድ ልጅ ነው፡፡ የልጅ እያሱ የዳግማዊ ምኒልክን መንበር ለመውረስ (ልጅ እያለች የልጅ ልጅ) መታጨቱ፣ የአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ባለ ሙሉ ሥልጣን የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንደራሴነት ሴት ለቦታው አትመጥንም ከሚለው እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ 10 ዓመት ኢትዮጵያን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የመራው የደርግ ኮሚቴ አንዲት ሴት እንኳ አባል አልነበረውም። ሕወሓት አማፂ ቡድን እያለ "የፌሚኒዝም ዝንባሌ የታየባቸው" አባላቱ ላይ ክስ ያቀርብ ነበር። አሁንም ድረስ በውሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ የሚገኙት ሴቶች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው። የመንግሥታት ስርዓቶቻችንን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁሉም ለሴት ዕድል አለመስጠታቸው አንዱ ነው።)

ሌላው ቀርቶ ሥም አወጣጥ ላይ የአባት እና የወንድ አያት ሥምን የሚከተል መሆኑ በአባት መጠራትን አኩሪ ያስመስለዋል፤ ‹የሴት ልጅ› የሚለው ሐረግ ስድብ የሆነውም ያለነገር አይደለም፡፡ የተዋሐደን ፆተኝነት ወንድነትን እንደታላቅነት ከአያት ላባት፣ ካባት ለልጅ እያወረሰን ስለመጣ ነው፡፡ አሁን ጥያቄው፣ ‘እኛስ ለልጆቻችን ምንድን ነው የምናወርሳቸው?’ የሚለው ነው፡፡

ምን ይበጃል?

ስር የሰደደ ባሕላችንን፣ እምነታችንን፣ ቋንቋ እና ልማዳዊ አሠራራችንን ፍትሐዊ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም፤ በአንድ ትውልድ የሚጠናቀቅም ነገር አይሆንም፡፡ ያውም ደግሞ ጉዳዩ ብዙ ተቃዋሚ አለው፡፡ ምክንያቱም አባታዊው ስርዓተ ማኅበር የመቀልበሱን ሒደት የሚቋቋምበት ልማድን የማፅኛ መከራከሪያዎች አሉት፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ስርዓተ ማኅበሩ በፍትሐዊ ስርዓተ ማኅበር መተካት አለበት የሚሉ ሁሉ የበኩላቸውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፣

1. ሴቶችን እና ወንዶችን የምንመለከትበት መንታ ምድብ (double standard) እንዳለን ነገር ግን በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሴቶች ከወንዶች ዕኩል መታየት እንዳለባቸው አምኖ መቀበል እና እያንዳንዷን የሕይወት እርምጃ መመርመር፣

2. የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እና ደራሲዎች ከሥራዎቻቸው ውስጥ ፆተኝነትን ለማስወገድ መትጋት፣ በትረካቸው ለተባእት በመተረክ ፈንታ ለብዙኃን (ወይም እንደተቀናቃኝ አማራጭ ለእንስት) ማድረግ፣ ሴታዊነትን የሚያራምዱ ሥራዎችን በማዘጋጀት የባሕል አብዮቱን መምራት፣

3. ዝነኞች እና ሕዝባዊ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዎች ራሳቸውን የሴታዊነት አራማጅ እንዲያደርጉ ንቅናቄ ማድረግ፣ በተገኘው አጋጣሚ ፆተኝነትን የሚዋጉ መልዕክቶች እንዲያስተላልፉ ማድረግ፣

4.  የሴታዊነት አራማጅ የሕትመት ውጤቶችን ማዘጋጀት፣ በተለያዩ ጦማሮች የአደባባይ ፆተኝነትን መተቸት እና ለጥበብ ሥራዎች የፆተኝነት እና ከፆተኝነት የፀዳ ምድብ ማውጣት፣ ወዘተረፈ።

Comments

  1. ይሄንን ፅሑ ሳነበው ልክ ሌሎች የሴቶችን የእኩልነት ጥያቄ ደግፈው የሚጻፉ ነገር የራሳቸውን አላማ ለማሳኪያ የሚጠቀሙበት ወይም የሴቶች እንቅስቃሴ በብዙሃኑ ተቃውሞ እንዲገጥመው እያደረጉ እንዳሉ ፅሁፎች እየተናደድኩኝ ነው የጨረስኩት። ምን ይበጃል ብለህ ያስቀመጥካቸው ነጥቦች እኔም ምስማማባቸው ነው በርግጥ ። ያናደዱኝ እና ያልተስማማሁባቸው ነጥቦች
    1- ምክንያት ላይ ሳይሆን ውጤት ላይ ያተኮረ ሐተታ ነው የቀረበው
    ፆተኝነታችንን ለማሳየት የተጠቀምቅባቸው ምሳሌዎች ማህበረሰቡን ለመውቀስ ነው እንጂ ያ እንዲሆን ያደረገውን ነገር ለማሳየት ፈፅሞ ማይጠቅም ነው። ለምሳሌ “ ሆስፒታል ሔደን ነጭ ጋዋን የለበሰች ሴት ስትገጥመን [ነርስ እንደሆነች እርግጠኛ በመሆን] "ሲስተር" የምንላት፣ ነጭ ጋዋን የለበሰ ሲገጥመን "ዶክተር" የምንለው የተዋሐደን ፆተኝነት አስገድዶን ነው“ ብለሃል። ይሄን አስተሳሰብ የፈጠረው መሬት ላይ ያለው እውነታ እንጂ ፆተኝነታችን አይደለም። እዚህ ላይ ሊያንገበግበን እና ልናተኩርበት የሚገባው ምን ያክሉ ሴቶች እየፈለጉ ነገር ግን እኩል ዕድል ሥላልተሰጣቸው እዚህ ቦታ ላይ ሳይደርሱ ቀሩ ሚለው ነው እንጂ ከ 50% በላይ ትክክል የመሆን ዕድል ባለው ነገር ሰዎች አመለካከታቸው ያንን እውነታ ይዞ ቢቀረፅ ፆተኞች ልንላቸው አይገባ። በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች ያስቀመጥቃቸው ምሳሌዎች እኔ እንደዚህ ነው ምረዳው። እውነታ ይሄ ሆኖ ሳለ ሰዎችን በግድ እንዲህ አታስቡ ብሎ መውቀስ ተገቢ አይደለም። እውነታውን ከቀየርን በኋል ግን ይሄን አመለካከቱ ይዞ ሚገኝ ሰው ካለ ወይም ሴት ይሄን መሆን አትችልም የሚል አመለካከት ያለውን ሰውን ነው ፆተኛ ብለን ልንገልፀው የሚገባን።
    2-ሴት ልጅ መብት እንጂ ግዴታም እንዳለባት አያሳይም
    ስለመደፈር ያነሳኸውን እንደምሳሌ ብንወስድ እኔ ስለደፋሪው በምንም መልኩ ፈፅሞ አልከራከርም መቶ ፐርሰትን ጥፋተኛ ነው መቀጣት አለበት ። ማንም ሰው ሌላ ሰውን ያለፍላጎቱ አስገድዶ ፍላጎቱን እንዲፈፅም የማድረግ መብት የለውም ይልቁንም ሴትን አስገድዶ መድፈር ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው። ነገር ግን ይህን የሚያደርግ ሰው ፈፅሞ እንዲጠፋ ማረግ እስካልቻልን ድረስ ሴቷም ለእንደዚህ አይነት ነገር ከሚያጋልጧት ቦትዎች ፣ ሰዎች፣ ሁኔታዎች እራሷ እንድትጠብቅም ልንነግራት ይገባል። የሌለ ሀሳባዊ ዓለም እየሳልን ማቅረብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ነገር ግን ይህን ስል በምንም መልኩ ሴትን ለደፈር ይሄ እንደምክንያት ቀርቦ መከራከሪያ ሊሆንለት አይገባም። ሁላችንም በሕይወት ሥንኖር ፈተና ሚሆኑን የተለያዩ ነገሮች አሉ እነዛን ፈተናዎች ምናልፍበት እና እራሳችንን ምንጠብቅበት ጥበብ ያስፈልገናል። ስለዚህ ለሴቷ ይህን እውነታ ልንነግራት ይገባል። በተጨማሪ ሴት ልጅ እንደ አንድ የማህረሰብ አባል ሚጠበቁባት ግዴታዎችም አሉ።
    3-መሰረታዊ ያልሆኑ ወይም ኢምንት ሚባሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል
    የወንዶቹን ሥም አስቀድሞ መጥራት በእውነቱ አሁን ይሄን ያክል ትልቅ ጉዳይ ነው። መፍትሄ ሊሆን የሚችለው እንግዲህ ለቀሩት ዘመናት የሴቷን ማስቀደም ነው :) ወይም በየተራ መጥራት። እኔ እንደ አንድ ለመብቷ እንደምትታገል ሴት የምረዳው ይሄ ሃሳብ ትግሉን አቃሎ እንደሚያሳይ ነው። ትልቅ ሥራ የሚጠበቅበት መሰረታዊ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ጉልበትም ጊዜም ሊያባክን አይገባውም። መሆን የምፈልገውን ነገር እንዳልሆን በሴትነቴ ብቻ ብዙ ተፅኖ የሚያደርጉብኝ፣ ሕልሜን እነሱ በመጠኑት ልክ አርገው ሊያሳዩኝ የሚሞክሩ አስተሳሰቦችና ሁኔታዎች እየታገልኩኝ እንደዚህ አይነት ነገሮች ጉዳየም አርጌ አላየውም (ጉዳይም የሚደረጉም አይደሉም)። እንደዚህ አይነት እርባና ቢስ ነገሮችን ከሴቶች የ እኩልነት ጥያቄ ጋር አያይዘን ማንሳታችን እንቅስቃሴውን ሰዎች አቅለው እና በንቀት እንዲያዩት ያረጋል እንጂ ምንም ጥቅም የለውም። ዋና የሴቶች ጥያቄ በስርአት ማስተላለፍ ብንችል አሁን የምናያቸውን ተቃዋሚዎች እና በፍረሃት የሚመለከቱቱን ሰዎች የእንቅስቃሴው አካል ማድረግ እንችል ነበር።
    4- ሌሎች
    አሁን ያለው የማህበረሰቡ አመለካከት የተመሰረተበት በፊት የነበሩ የኑሮ ሁኔታዎች ላይ ነው። ድሮ በነበረው አኗኗር ይመቻል ያሉትን ሥርአት ሰርተዋል ጥያቄአችን ድሮ ለምን እንዲህ ሆነ ሳይሆን ዛሬ ነገሮችና ሁኔታዎች ስለተቀየሩ የ ሴቶችን ኑሮ እና ሚና በዛ ልክ በተሰፋው አስተሳሰብ አይቀረፅ ነው። ወንዱ እንደብቻ የገቢ አስገኚ ተደርጎ ቢቆጠር ከሴት ይልቅ ወንዶች አድነው አርሰው ቤተሰባቸውን ይመግቡ ነበር ይህ ሀቅ ነው። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ሴቶች በሁሉም መስክ ከወንድ እኩል ድርሻ መውሰድ ስለሚችሉ ያ አስተሳሰብ ይቀየር ነው ጥያቄው። ኑራችንም ይህን መሰረት አርጎ ይዋቀር ነው። ማለት የፈለኩት ምንድነው የዱሮውን መውቀስ ላይ ሳይሆን ዛሬን መቀየር ላይ ነው ትኩረታችን መሆን ያለበት።

    የተፈጥሮ ልዩነቶችን መቀበል አለብን፣ የተያዘው የመበት ትግል እንጂ ልቅነትን መስበክ አይደለም። ሴቶች ከወንዶች በተፈጥሮ ምንለይባቸውን ነገሮችን መቀበል አለብን ይሄ ልዩነታችን ፀጋ ነው ያለበለዚያማ ሴት እና ወንድ ሆነን መፈጠር ባላስፈለገ ነበር። ወሲባዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ለሴቶች የተለዩ የሚመስሉ መስመሮች የተሰመሩ ያነሳሃቸው ነገሮች አሉ ። እኔ እንደምረዳው በተፈጥሮ ምክንያት ከወንዱ ይልቅ ሴቷ ላይ የሚከተለው ውጤት ከባድ ስለሆነ ነው። ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃ ተከትሎም ልጅ መውለድ እንዳትችል የሚያደርጋት ሁኔታ፣ ከሚወሰዱ መድሃኒት የተነሳ የሚመጡ ሌሎች ችግሮች ፣ ወዘተ ይሄ ሁሉ ነገር እያለ ሴቷም እንደፈለገች ትሁን ብሎ መስበክ ጉዳቱ እንጂ ጥቅም የለውም። የሴቶች እንቅስቃሴም አላማው ይሄ አይመስልኝም። ሃይማኖትን የተመለከቱ ያነሳሃቸው ነጥቦች አንተ ባላህ የአረዳድ ልክ ነው ያቀረብከው ብዙም ማለት አልፈልግም።
    ባጠቃላይ የሴቶችን የመብት ጥያቄ ደግፈህ መፃፍህ በራሱ የሚበረታታ ነው። ቢሆንም የተፃፈው ፅሁፍ ወጤቱ አንተ ባሰብከው መልኩ ደጋፊ ሣይሆን ታቃዋሚ ሚያበዛ ነው። መቼም አንተም እንደምታስተውለው ብዙዎች ፌሚኒዝም የሚፈሩት ና በአይነ ቁራኛ የሚያዩት ዋናውን አላማ በደንብ ከማቅረብ ይልቅ በኛ ግላዊ የሃይማኖት፣የኑሮ መርህ ወዘተ ለውሰን ስለምናቀርበው ነው። ስለዚህ አንተ ፅሁፍህ መግቢያ ላይ እንደተማፀንከው እኔም እባካችሁ ስለፌሚኒዝም ስትፅፉ የራሳችሁን የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የፖለቲካ አቋም ደባልቃቹ አትፃፉ ብዬ ተማፅኖየን አቀራብለሁ።

    ReplyDelete
  2. የተከበርሽ አኖኒመስ፣
    ረዘም ያለ ጊዜ ወስደሽ አስተያየት በመስጠትሽ ተደስቻለሁ። ሆኖም አስተያየቶችሽ ውኃ የሚያነሱ ሆነው እንዳላገኘኋቸው አልሸሽግሽም።

    በፆተኝነት የሰጠኋቸው ነገሮች የእውነታው አንፀባራቂ አይደሉም። ለብዙኃኑ ይሠራል ማለት ለሁሉም ይሠራል ማለት ስላልሆነ። ፆተኝነት ፆታዊ መድሎ የፈጠረው ስርዓተ ማኅበር መገለጫ ነው። ያንን ነው ለማሳየት የሞከርኩት። ምንጩን ስትጠቅስ ተሳስተህ ውጤቱን ነው የገለፅከው የሚለው ትችት ስለሃይማኖት በጻፍኩት ላይ ቢሆን ኖሮ ሚዛን የድፋ ነበር። ነገር ግን የሃይማኖቶች ጉዳይ ፆተኝነትን ተቋማዊ ማድረጋቸው ነው ለዚህ ትውልድ የፆተኝነት ምንጭ የሚያሰኛቸው።

    ኢምንት ነገሮች ላይ ያተኮርኩት ፈረንጆቹ እንደሚሉት "ዘ ዴቭል ኢዝ ኢን ዘ ዲቴይል" ብዬ ነው። ትችቴ በያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ሳይቀር እንድንጠነቀቅ ነው። ጥቃቅኗ ተጠራቅማ ነውና ትልቁን የምተወፈጥረው።

    የተፈጥሮ ልዩነቶችን አልተቃረንኩም። ነገር ግን ተፈጥሮም እንከን አልባ ናት ብዬ አላምንም። ማረም በምንችለው እና በምንፈልገው ልክ እናርማታለን።

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...