Skip to main content

Posts

Showing posts from August, 2017

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የተዋሐደን ፆተኝነት

ይህ ጽሑፍ ስለ ፍትሕ ነው። አንባቢዎቼን በትህትና አስቀድሜ የምጠይቀው ነገር ቢኖር የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት መነፅሮቻችሁን አውልቃችሁ በፍትሕ መነፅራችሁ እንድታነቡኝ ነው። የተዋሐደን ፆተኝነት ስንል ምን ማለታችን ነው? ምንጮቹ ምን ምን ናቸው? ውስጣችን ያለው ይህ ፆተኝነት ምን ያህል ችግር ይፈጥራል? የተዋሐደንን ፆተኝነትን እንዴት እንቅረፈው? መግባቢያ ስለፆተኝነት ፆተኝነት ማለት በአጭሩ ‘ፆታዊ መድልዖ’ ማለት ነው። በዓለማችን እጅግ የተንሰራፋው ለወንዶች የሚያደላው ወይም አባታዊው ስርዓተ ማኅበር ነው። (እርግጥ እጅግ ጥቂት ሆኑ እንጂ እናታዊ ስርዓተ ማኅበሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕንድ አገር ሜጋላያ ስቴት ውስጥ የሚገኙት ጎሳዎች ሀብት የሚተላለፈው ከእናት ወደሴት ልጅ ነው፡፡ በዚህ ስርዓተ ማኅበር የትምህርትና መሰል ዕድሎች ከወንዶች ይልቅ ለሴቶች ይመቻቻሉ፡፡ ይህን ምሳሌ በዓለም ከተንሰራፋው አባታዊው ስርዓት አንፃር ከቁብ ሳልቆጥረው ላልፍ እችል ነበር። ነገር ግን የእነዚህ ጎሳዎች እናታዊ ስርዓት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ መድረሱ አባታዊው ስርዓትም ሆነ እናታዊዋ በማኅበራዊ ብሒል የሚገኙ እንጂ ተፈጥሮ ያከፋፈለችን ሚና አለመሆኑን ስለሚያሳይ ነው።) የአገራችን ስርዓተ ማኅበር ከጥግ እስከ ጥግ አባታዊ ነው። ይህንን ስርዓተ ማኅበር ለመቀልበስ እና ፍትሐዊ ስርዓተ ማኅበር ለመመሥረት የሚደረጉ የተደራጁም ይሁን ያልተደራጁ ንቅናቄዎችን ሴታዊነት እንላቸዋለን። (‘እንስታዊነት’ የእንግሊዝኛውን ‘Feminism’ በቀጥታ የሚተካ ቢሆንም፣ አማርኛችን ስርዓተ ፆታ (gender) ያልተጫነው ‘ሴት’ የሚል ሥነ ተፈጥሯዊ (biological) ልዩነቱን ብቻ የሚገልጽ ቃል ስላለው ‘ሴታዊነት’ የሚለውን መርጫለሁ። በዚህ ጽሑፍ ውስ...