በአፍሪካ አሜሪካውያን የሲቪል መብቶች ትግል ውስጥ እና በደቡብ አፍሪካ ነባር ጥቁሮች ከመጤ አፍሪካነሮች የተነጠቁትን የዕኩል ሰውነት መብት ለማስመለስ ሲታገሉ፣ ጥቂት የማይባሉ ነጮች (ወይም አፍሪካነሮች) የትግላቸው አጋር ሁነውላቸው ነበር። ሌሎች ጥቂቶች በደሎቹን ምክንያታዊና ተገቢ ለማድረግ (to justify) ተከራክረዋል። ብዙኃኑ ግን በገለልተኝነት እና በስጋት ተመልክተውታል። ከጥቁሮቹ ታጋዮች መካከልም ከፊሎቹ ለዕኩል የሰውነት ማዕረግ ታግለዋል። ከፊሎቹ ነጮቹን ለመበቀል ታግለዋል። ዞሮ፣ ዞሮ ግን ሁሉም ነባሩን ትርክት እና ተቀባይነት የነበረውን (mainstream) አስተሳሰብ ማፈራረስ ነበራቸው። በዚህ ግዜ ነጮቹ ቀድሞ የነበራቸውን የተለየ መብት ከጥቁሮች ጋር መጋራታቸው መብታቸውን እንደመነጠቅ ቆጥረውታል። ለምሳሌ ቅድሚያ ይሰጣቸው የነበረውን አገልግሎት ከጥቁሮች ዕኩል እንዳደራረሳቸው እየተሰለፉ እንዲያገኙ መገደዳቸውን እንደመብት ነጠቃ ይቆጥሩታል።
እነዚህ ተግዳሮቶች መገፋፋት ይፈጥሩ ነበር። በዚህ ሳቢያ ከነጮቹም፣ ከጥቁሮቹም ወገን አብረን መኖር አንችልም የሚል ሰውነትን የመጠራጠር ዝንባሌ ታይቷል። በአሜሪካ እነማልኮም ኤክስ ይመሩት የነበሩት እንቅስቃሴ የነጭ የሆነውን ሁሉ መጠየፍን እንደስትራቴጂ የቆጠረ ነው። የነሱ ተቃራኒ ዕኩያ የሚባለው ኬኬኬ የሚባሉት የነጮች ጥቁር ተጠያፊ ቡድን ነው። የማልኮሜክስ ‘ኔሽን ኦቭ ኢስላም’ እና ‘ኩ ክላክስ ክላን’ አንዴ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ጥቁሮቹም ነጭ የማያዩበት የጥቁር ዓለም፣ ነጮቹም ጥቁር የማያዩበት የነጭ ዓለም ሊመሠርቱ። አንዱ ሌላኛውን ለማግለል እንደመስማማት።
በቀድሞዋ አሜሪካ ሰሜኖቹ "ነጻ አገሮች" ሲሆኑ ደቡቦቹ "ባሪያ አሳዳሪ" ነበሩ። ሶሻሊስቶቹ በወቅቱ በሰሜን የነበረውን የጭሰኝነት ሁኔታ እያዩ በሰሜን ያለው የጭቁን ሠራተኞች ሁኔታ እና በደቡብ ያለው የባሪያዎች ሁኔታ አንድ ነው እስከማለት የሚደፍሩ ነበሩ – በመደብ ጭቆና ትንተና። ነገር ግን በወቅቱ ከደቡብ ባርነት ኮብልለው ወደሰሜን ጭሰኝነት የሚፈልሱ እልፍ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሰሜን ጭሰኝነት ወደደቡብ ባርነት የኮበለሉ ሰዎች አልነበሩም።
ሌላኛው ፈታኝ ነገር ያንን ጥቁሮችን የሚያንኳስስ ስርዓት የሚደግፉ ጥቁሮች መኖራቸው ለነጭ አስተባባዮች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ነበር። ማልኮም ኤክስ በባርነት የነበሩ ጥቁሮችን በሁለት ይከፍላቸው ነበር። የቤት እና የመስክ ኔግሮዎች (house and field negroes) ብሎ። የቤት ኔግሮዎቹ ጥቁር ቢሆኑም ከጌታው የሚተርፈውን ከስር ከስር የመቋደስ ዕድሉ ነበራቸው (they were privileged)። ተመችቷቸዋል። ስለዚህ፣ አብዛኛውን ፍዳ እንደሚቀምሱት የመስክ ኔግሮዎች ስርዓቱን አይቃወሙትም፣ እንዲያውም በደሉን በሰበብ ያለባብሱለታል።
እንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ትርክት መገፋፋት ኋላ ላይ የዕኩል ሰውነት ማዕረግ ለማግኘት ይታገሉ ለነበሩት ለነማርቲን ሉተር ኪንግ ፈታኝ ነበር። በግለታሪኩ ላይ ኪንግ የሲቪል መብቶች ትግሉ አንዱ ፈተና ይህ እንደነበር ገልጿል። መጨረሻ ላይ ስኬታማ የሆነው ግን፣ የአግላዮቹ ሳይሆን የአካታቾቹ ትግል ነው። ጥቁሮቹ ዕኩል መብቱን ሲያገኙ ቀድሞ ነጮቹ ይፈሩት እንደነበረው ዓይነት ጥፋት አልደረሰም።
በደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲ ጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ነጮችንም በአባልነት ይቀበል ነበር። የነማርቲን ሉተር ኪንግ እንቅስቃሴም በርካታ ነጭ አጋሮች ነበሩት። ማልኮም ኤክስ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለሚፀፅተው ነገር ሲናገር አንዲት ታዳጊ ልጅ ጠቅሷል። ከዓመታት በፊት ማልኮም የአግላዩ ትግል ሊቀ ጳጳስ እይያለ አንዲት የ10 ዓመት ሕፃን ልጅ እቅፍ አበባ ይዛ ለጥቁሮች ትግል አጋርነቷን ለማሳየት ስትወጣ ‘ሂጅ ከዚህ፤ እኛ ከነጮች ጋር አጋርነት የለንም’ ብሎ አባሯት ነበር። ኋላ፣ እየበሰለ ሲመጣ ተፀፅቷል።
እኛ አገር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፆታን ጨምሮ፣ ከፊሉ በመደብ፣ ከፊሉ በማንነት፣ ከፊሉ በመደብ እና በማንነት ምክንያት በሚሉት መሠረት (መሠረቱን ባለሙያዎች በጥናት ሊበይኑልን ሲገባ እኛ ባላዋቂነት ጭቃ እየተለቃለቅንበት እንገኛለን፣ ለማንኛውም) ለዘመናት በገዢዎች እና በተገዢዎች መካከል (ወይም ዘመንና በሕል ባፈረጠማቸው እና ባንኳሰሳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች /ምሳሌ ወንዶች እና ሴቶች/) ለደረሱት በደሎች እና በዘለቄታው ላስከተሉት በማንነት ላይ የተመሠረተ የተጠቃሚነት ጉዳትን ለማስተካከል (undoing sustained system of repression) አንዱ የሌላው አጋር በመሆን አካታች የመብት ትግል በማድረግ ፈንታ አግላይ ትግል እያደረግን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ አማራጭ እያለን፣ ሁሉንም ተሸናፊ የሚያደርገውን አማራጭ እየተከተልን እንገኛን።
ብዙ ጊዜ አጋርነትን አለመከተል ጦስ አለው። "ችግር የለም" በሚል በክህደት (denial) የተጀመረው፣ ወደፍረጃ ወይም መጥሌ (prejudice) ያድግና ውጤቱ የእርስበርስ እልቂት ይሆናል። ለዕኩል ዕድል እና መብት የሚታገሉት ቡድኖች በአግላይ ትርክት ጠላት የሚል ሥም የሚያወጡለት ቡድን ስለሚኖረው "ተቃራኒያችን" የሚሉትን ወገን ይገፋሉ። በሌላ በኩል ያንኛው ወገንም አንዳንድ ነባር ጥቅሞቼ ሊሸረሸሩብኝ ነው፣ ከሌሎች የዕኩል ባለመብቶች ጋር ልጋራው ነው በማለት የአፀፋ ግፊት ይገፋሉ።
የአንዱ እምነት ተከታይ ይሄ በደል ነበረብኝ፣ አለብኝ፣ በዘዴ እንዲቀጥል እየተደረገብኝ ነው ሲል፤ አንዱ ብሔርተኛ በማንነቴ ምክንያት እንዲህ ዓይነት በደል ይደርስብኝ ነበር፣ አሁንም አለብኝ፣ በዚህ አካሔድ ወደፊትም በደሉ ይቀጥልብኛል ሲል፤ አንዷ ሴት በመሆኔ ብቻ ወንዶች በቀላሉ የሚያገኙትን መብትና ዕድል ተነፈግኩ ስትል፣ «እኔ አለሁልህ/ሽ» በማለት ሰው ሠራሽ የእምነት እና የማንነት ድንበሮችን መስበር ካልቻልን ለሰውነት ማዕረግ ብቁ ነን ማለት አይቻልም። ተበዳይም በአርቲፊሻል ሰበቦች ላይ ተመሥርቶ ‘አንተማ በድለኸኛል፣ ወግድልኝ’ ካለ ትግሉ የሚገባውን የሰውነት ማዕረግ ለማግኘት ሳይሆን በተራው የሌሎችን ለመግፈፍ ነው ማለት ነው። ዳር ላይ ቁሞ ችግሩን ለመፍታት የሚፍጨረጨሩትን ፀጉር እየሰነጠቁ በማብጠልጠልም ግድግዳው አይፈርስም። የሚከፋፍለን ግድግዳ ፈርሶ፥ የሚያቀራርበን ድልድይ የሚሠራው እያንዳንዳችን ሌሎች በሚያደርጉት ትግል ውስጥ አጋርነታችንን በተግባር መግለጽ ስንችል ነው።
መጤ ሃይማኖት፣ ከመጤ ሃይማኖት በመምረጥ፣ (ግን በመሠረቱ ለገዢዎቹ ዋናው ሃይማኖቱ ሳይሆን በሥመ ሥዩመ–ፈጣሪነት የገዢነት ዕድል እና ተገዢ የማግኘት ጥረት ነው።) በወንዜ ማንነት ላይ በመመሥረት አገር ሲገዙ የነበሩ ሰዎች በነበሩበት አገር ውስጥ ያንን የሚያስተባብሉ (justify-ers) መኖራቸው አይገርምም። ይልቁን ከዚያ የአስተሳሰብ እስራት ወጥቶ ሰው ሆኖ መገኘት ነው ቁም ነገሩ።
ከገዢዎች እስራት ነጻ ከመውጣት በፊት ከገዛ ኋላ ቀር አስተሳሰባችን ነጻ መውጣት ይኖርብናል። መሬት የረገጠ ለውጥ ሊያመጡ እውነተኛውን ሥራ እየሠሩ ላሉት አጋር መሆን ካቃተን፣ ቢያንስ አደናቃፊ ላለመሆን መጣር ነው።
Comments
Post a Comment