Skip to main content

ያልተሞከረውን ሙከራ

በበፍቃዱ ኃይሉ

ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እያለሁ ፖለቲከኛ ከሆነውም ካልሆነውም ጋር በፖቲካ ጉዳዮች እንከራከር ነበር። ከክርክሮች በአንዱ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር እኔ እንደሃይማኖት የማከርረውን “ሠላማዊ ትግል አልተሞከረም” እያልኩ እንደወትሮዬ ስሟገት የደረሰልኝ ብቸኛ ሰው ፍቅረማርያም አስማማው ነበር። ፍቅረ በሙግት ሲያጣድፉኝ የነበሩትን፣ እያንዳንዳቸውን "አንተ ሰልፍ ወጥተህ ታቃለህ? ፓርቲ ተቀላቅለህ ታቃለህ?…” እያለ ቀድመው አፋችን ላይ የሚመጡልንን የሠላማዊ ትግል እንቅስቃሴ የሚባሉትን ሁሉ ሲጠይቃቸው "አይ…" በማለት ይመልሳሉ። ከዚያ ፍቅረ “ብዙ ጊዜ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም እያሉ የሚከራከሩት ምኑንም ያልሞከሩት  ናቸው" አለና ክርክሩን ቋጨልኝ።

ከዚያ ከፍቅረ ጋር ብቻችንን ስንሆን፣ "የምር የምታምንበትን  ነው የተናገርከው?" አልኩት። ግንቦት 7ን ለመቀላቀል ከብርሃኑ ተ/ያሬድ እና ከእየሩሳሌም ተስፋው ጋር ሲሄድ መያዙ ይታወቃልና።

እጅግ ሲበዛ የሚያስደንቀኝ  ትሕትና ያለው ፍቅረ፣ በተለመደ ትሕትናው ሊያስረዳኝ ሞከረ። "ለሠላማዊ ትግል ክብር አለኝ" ብሎ ነበር የጀመረው። "ቢሆንም…" በማለት ብዙ አስረድቶኛል። በተለይ መደራጀት በማይቻልበት ጥቂቶች ሠላማዊ ትግልን የመረጡ በግልጽ እየታዩ ለመኮርኮም ይመቻቻሉ አለኝ። ተለቅቄ እስክወጣ ክርክሯችን አልበረደም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን አማራጩን ከሕይወት መርሔ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ባልቀበለውም፣ ቢያንስ “የእነርሱን መረዳት አለብኝ?” በሚል ብዙ አስቤበታለሁ።

ምዕራፍ ፩ - ሦስቱ ወጣቶች በሠላማዊ መንገድ ላይ…

ለመጀመሪያ ግዜ እየሩስን በአካል የተዋወቅኳት እስር ቤት ውስጥ ነው። ‘ግራዚያኒ በትውልድ ሀገሩ የመታሰቢያ ኀውልት ሊሠራለት የማይገባ ነፍሰ–በላ ሰው ነው’ ብለው የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ እኔ በዚያ’ጋ በአጋጣሚ ሳልፍ ፖሊስ እየደበደበ ሲያፍሳቸው አየሁ። ይቺንማ ፎቶ ማንሳት አለብኝ ብዬ ሦስት ፎቶ እንዳነሳሁ እኔም አብሬ ታሰርኩ። የሰማያዊ ፓርቲ እና የባለራዕይ ወጣቶች ነበሩ ሰልፈኞቹ። ፖሊሶቹ «እንፍታቸው፣ አንፍታቸው?»፤ «የት እናሳድራቸው?» ሲባባሉ ሦስት ጣቢያ እያዞሩን አስመሹን። እኔ በወቅቱ በፍርሐት ስርድ እነሱ ሌሎቹ በጀግንነት ይዘፍኑ ነበር። ማታ ላይ ብርዱ ይሁን ፍርሐቱ ሲያንቀጠቅጠኝ እየሩስ የመጣላትን ጋቢ አለበሰችኝ።…

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እያንዳንዳቸው ከ10 ጊዜ በላይ ታስረው ተፈትተዋል። ሁሉንም እስሮቻቸውን ጥፋተኛ ተብለውት አያወቁም። የሚታሰሩት አንዳንዴ "ወረቀት በተናችሁ"፣ አንዳንዴ ደግሞ "ዕውቅና ያልተሰጠው ሰልፍ ወጣችሁ" በሚሉና በሌሎችም ተልካሻ ሰበቦች ነው።

ታስረን እያለን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየመጡ ይጠይቁን ነበር። ፍቅረ እና ብሬ አንድ ቀን ያለወትሯቸው ፊታቸው ላይ ተስፋ መቁረጥ በግልፅ በሚነበብበት ሁኔታ ሊጠይቁን መጡ። ሁለቱም ከከተማ ውጪ እንደነበሩ፣ እና ለምርጫ ዕጩ እየመለመሉ አንደከረሙ ነገሩን።

«እንዴት ነው ታዲያ?» በጉጉት ጠየቅናቸው።

«ተስፋ አስቆራጭ ነው» አሉ። «‘እኔን ዕጩ አድርጉኝ’ ብሎ ወጥሮ የያዘን ሁሉ አዲሳባ ስንደርስ ‘ይቅርብኝ፣ ይቅርብኝ’ ብሎ ይደውልልናል።»

«ምንድን ነው ችግሩ?»

«ችግሩማ ኢሕአዴግ ነው። ዕጩዎቻችንን እያስፈራሩ ራሳቸውን እንዲያገሉ እያደረጓቸው ነው። እምቢ ያሏቸውንም በየሰበብ አስባቡ እየሰረዙ ከግማሽ በላይ የሆኑትን አባሎቻችንን ሰረዙብን።»

ብርሃኑ «ከዚህ በኋላ በዚህ በኩል መጥተን የምንጠይቃችሁ አይመስለንም። ወይ በውስጥ እንገናኛለን፤» እንደሚታሰሩ ገምተዋል ብዬ ደመደምኩ። ወቅቱ ቅድመ ምርጫ እንደመሆኑ እስር ብርቅ አልነበረም።

ብርሃኑ ፖለቲካ ሲያወራ አንጀቴን ያርሰዋል። ቀረብ ብለው ሲያዋሩት የተቃዋሚውንም የኢሕአዴግንም ድክመት ያለስስት መተቸት ያውቅበታል።
ከዚያ በኋላ አልመጡም። ቆይተን መታሰራቸውን ሰማን። መጀመሪያ እንደወትሮው ዓይነት እስር መስሎን ነበር። ጉዳዩ ሌላ መሆኑ የገባን ዝርዝሩን ስንሰማ ነው። በአካል መልሰን የተገናኘነው ከማዕከላዊ ወደ ቂሊንጦ ሲዛወሩ ነው።

እኔ፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዘላለም ወርቅአገኘሁ እና ሌሎችም የነበርንበት ዞን 2 የተመደበው ፍቅረማርያም ነበር። ፍቅረማርያም የግለሰብ አጀንዳ የሌለው ሲበዛ ትሁት ወጣት ነው። የሱን ትህትና የሚፎካከር ያገኘሁት አብርሃ ደስታን ብቻ ነው። ፍቅረ የሚታገለው በሚንቀለቀል ነገር ግን ለውለታው ምላሽ በማይፈልግ የወጣትነት ስሜት ነው።

ምዕራፍ ፪ – ሦስቱ ወጣቶች በፍርድ ቤት ክርክር…
(ያልተሞከረውን ሙከራ)

ልጆቹ ትግል ላይ በቂ ልምድ ስላላቸው ሲያዙ ሌሎች እንደሚያደርጉት ወደ ክህደት አልሄዱም። «ሠላማዊ ትግል ላይ ያለን እምነት ስለተቀየረ፣ የቀድሞ ፓርቲያችንን ሰማያዊን ለቀን፣ የግንቦት ሰባትን የትጥቅ ትግል ለመቀላቀል እየሄድን ነበር» አሉ። ይኸው ክስ ሆኖ ተመሰረተባቸው።

መዝገባቸው አራት ሰዎች ይዟል።
1ኛ፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ
2ኛ፣ እየሩሳሌም ተስፋው
3ኛ፣ ፍቅረማርያም አስማማው
4ኛ፣ ደሴ ካህሳይ

ደሴ ካህሳይ ወደኤርትራ ሊያሻግራቸው የነበረው ሰው ነው። እነብርሃኑ ፍርድ ቤት «ድርጊቱን ፈፅማችኋል ወይስ አልፈፀማችሁም?» ሲላቸው የሰጡትን መልስ ነው ‘ያልተሞከረውን ሙከራ’ የምለው።

«ድርጊቱን ፈፅመናል፤ ግን ጥፋተኞች አይደለንም» አሉ።

ከዚህ በፊት በግንቦት ሰባት ተጠርጥረው ያመኑ እና በዚያው የተቀጡ እስረኞች ገጥመውኛል። ሆኖም «ድርጊቱን ፈፅመናል። ጥፋተኞች ነን» ነበር የሚሉት።

«ምን አስባችሁ ነው?» አልኩት ፍቅረን።

«ግንቦት ሰባት በእኛ እምነት አሸባሪ ቡድን አይደለም። ነፃ አውጪ ቡድን ነው። ልክ የፀረ–ሽብር አዋጁ ሠላማዊ ትግልን እያደናቀፈ ነው ይሰረዝ እንደምንለው ሁሉ፣ የግንቦት ሰባት ‘አሸባሪ ነው’ የሚለውም እንዲሰረዝ ፍ/ቤቱን በሕጋዊ አካሄድ መሞገት እንፈልጋለን» አለኝ።

«እና በዚህ መንገድ ተከራክራችሁ እና ረትታችሁ ነፃ እንወጣለን የሚል እምነት አላችሁ?» የኔ ጥያቄ ነበር።

«ጉዳዩ በዚህ ክርክር ነፃ መውጣት አለመውጣት አይደለም። እኛ የምናደርገው ክርክር አንደኛ መንግሥት ሠላማዊ ትግሉን ሆነ ብሎ ሠላማዊ ወዳልሆነው ሜዳ እየገፋው እንደሆነና ለዚህ መከሰስም ካለበት ራሱ መንግሥት መከሰስ እንዳለበት፤ ሁለተኛ ግንቦት ሰባት የገዢው ፓርቲ እንጂ የሕዝብ ጠላት አለመሆኑን ለማሳየት መሞከር ነው ዓላማችን» አለኝ። ይህንን ስናወራ የነበረው እዚያው ቂሊንጦ እያለሁ ነበር። አሁን ተከላክለው ነፃ እንዲወጡ በ14ኛው የፌ/ወ/ችሎት ተበይኖባቸው የመከላከያ ምስክሮችን ለማስደመጥ ለመጋቢት 22, 2008 ተቀጥረዋል።

«እህ ምን አሰባችሁ?» በማለት የእስር ጓዶቼን ልጠይቃቸው ቂሊንጦ የሄድኩ ጊዜ ፍቅረን ጠየቅኩት።

ፍቅረ «ማንኛውንም በሠላማዊ ትግል የተሰማራ ሰው በሙሉ ከቻልክ ለኛ እንዲመሰክርልን ጥሪ እንድታደርግልን እንፈልጋለን» አለኝ። «እንዴ?» አልኩኝ ድንግጥ ብዬ። «ይሄማ እንዴት ሊሆን ይችላል። በሠላማዊ ትግል ውስጥ ያለ ሰው እኮ የናንተ ተቃዋሚ ነው። የተሳሳተ መንገድ ነው የሚከተሉት እያለ እንዴት ምስክር ይሁኑን ትላለህ?» አልኩት።

የሰጠኝ መልስ ባጭሩ እንዲህ የሚል ነው።

«እኛ የምንፈልገው ሠላማዊ ታጋዮች በሠላማዊ ትግል ውስጥ የገጠማቸውን ፈተና ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱልን ብቻ ነው። ይህ መንግሥት ሠላማዊ ትግል እንዲያበቃለት መንግሥት ራሱ መንስኤ እየሆነ እንደሆነ ያሳይልናል። ቀሪውን ማስረዳት የኛ ድርሻ ነው።»

ፍቅረ በተጨማሪም ስርዓቱ ራሱ ለነሱ ውሳኔ እያደረገ ያለውን ኢ–ሕገመንግሥታዊ ዘመቻ አንድ ባንድ የሚሞግቱበት ስትራቴጂ እንዳላቸው ነገረኝ። ነገርዬው ፈረንጆቹ ‘ጁዲሻል አክቲቪዝም’ የሚሉት ሕግን መሠረት ያደረገ አክቲቪዝም ዓይነት መሆኑ ነው። እኔ በግሌ ወጣቶቹ የትግል ስትራቴጂ መቀየራቸውን አልወደድኩላቸውም ነበር። እስር ክፉ አጋጣሚ ቢሆንም፣ አጋጣሚውን ወደዕድል በመቀየር፣ ውጤቱ እንደጠበቁት ቢሆንም ባይሆንም  በሠላማዊ የትግል ስትራቴጂ (በጁዲሻል አክቲቪዝም) ራሳቸውን ለማስፈታት (ወይም አጭር ፍርድ ለመቀበል) ሳይሆን መንግሥትን ለሞገት በመወሰናቸው ደስ ብሎኛል።

በእኔ እምነት ከሠላማዊ ትግሉ ወጥቶ የኃይሉን መቀላቀል ለኢሕአዴግ እጅ መስጠት ነው። እስከዛሬ ደክመው እጅ የሰጡትን ሁሉ እየጠቀሰ የሚያሳጣው ኢሕአዴግ ነበር። አሁን ግን በነብርሃኑ ተ/ያሬድ መዝገብ የተከሰሱት ወጣቶች ‘ለዚህ ያበቃኸን አንተው ነህ’ እያሉ ኢሕአዴግን ይከሳሉ።

***
ብርሃኑ፣ እየሩስ፣ ፍቅረ እና ደሴ ከታሰሩ እነሆ ልክ አንድ ዓመታቸው ዛሬ።

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...