Pages

Thursday, December 12, 2013

#HRDay2013፤ ከሰው በታች የሆኑ ሰዎች አሉ ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን አሁንም አሉ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው፤ አምስት ኢትዮጵያውያን ሰብሰብ ብለን እራት እየበላን ነበር፡፡ አንደኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ‹‹ነጻ›› የጋዜጠኞች ማኅበራት የአንዱ ፕሬዚደንት ነው፡፡ በጨዋታችን መሐል የተናገረው ነገር ሁላችንንም አስደነገጠን፡፡ በዚህ ዘመን እንዲህ የሚያምን “ዘመነኛ” ሰው አለ እንዴ!?

ሰውዬው ያወራልን ሌሊት ወደጅብነት ስለሚለወጡ ሰዎች ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁላችንም አፍረን ስናፈገፍግ ከመሐላችን አንዱ “እንዲህ ዓይነት ነገር እውነት ነው ብለህ ታምናለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ እሱ ሆዬ በሙሉ መተማመን እኛን እንዳላዋቂ በመቁጠር ሌሊት ወደጅብነት የሚለወጡ ሰዎች እንዳሉ ያስረዳን ጀመር፡፡

ይህንን ትዝታዬን የቀሰቀሰው ትላንት ጋዜጠኛ Masresha Mammo የጻፈው ማስታወሻ ነው፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ የተለየ ስለነበር እኔ ግን ለዚህች ጽሑፌ የሚጠቅመኝን ገንጥዬ አጣቅሳለሁ፡፡ ማስረሻ እንዲህ ይላል፤

‹‹…ተወልጄ ያደግኹት ከእንጦጦ ተራራ ስር ቀጨኔ በምትባል ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ […] ቀጨኔ ላይ ያለው ማኅበረሰብ ወደአዲስ አበባ የተሰደደው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሲል አልነበረም፡፡ ቡዳ ነው የሚል ስም ስለተለጠፈበት ‹ልጆቻችንን በልተው ጨረሷቸው› በሚል ግድያው ስለበዛበት ነበር፡፡ አንድ ቀጥቃጭ አባቱ፣ ወይም ሸማኔ ወንድሙ፣ አሊያም ሸክለኛ እናቱ በዚሁ ሰበብ ሲገደሉበት፤ በምላሹ እሱም ደሙን ተወጥቶ ይሸሻል፡፡ ይሰደዳል፡፡...

‹‹ይኼ ማኅበረሰብ ለሺሕ ዓመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የጀርባ አጥንት ኾኖ ቆይቷል፡፡ በቴክኖሎጂ ላልሰለጠነችው ኢትዮጵያ ማረሻ እና ወገል ያቀርባል፣ እንዳይበርዳቸው ልብስ ይሠራላቸዋል፣ ለመመገቢያቸው የሚኾኑትን ሸክላዎች እና የዕደ ጥበብ ውጤቶች ሁሉ ይሰጣቸዋል፡፡ ያለዚህ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያን ወደኋላ ዞር ብላችኹ አስቧት፡፡ [ማኅበረሰቡ] በሚኖርባት በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ግን ስሙ ቡዳ ነው፡፡

‹‹ቡዳ ማለት ደግሞ፤ ቀን ቀን ጋቢ ለብሶ የሚኖር፣ ማታ ማታ ወደ ጅብነት የሚቀየር ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እና አመለካከት የሚመራው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውስጥ ነበር፡፡…››

ማስረሻ ‹‹ነበር›› ይበል እንጂ ዛሬም ድረስ ከዚህ ባልተለየ መንገድ የሚያምኑ ‹‹ምሁራን›› ሳይቀሩ አሉ፡፡ ልዩነቱ በዚህ ዘመን በተለይ በከተማ እንዳይገዳደሉ ሕግ ያግዳቸዋል፤ በገጠር ግን አሁንም በግልጽ አለ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሄድኩበት የገጠር አካባቢ ውስጥ ካሉ ‹‹ቡዳ›› ወይም ‹‹ባለእጅ›› ከሚባሉ ሰዎች/ቤተሰብ አባላት ጋር እንዳልገናኝ እና ‹‹ዓይናቸው እንዳልገባ›› አብረውኝ ያሉ ሰዎች ሲጠብቁኝ እና ሲያከላክሉኝ ነበር፡፡ ዛሬም እናቴን ብቻ ሳይሆን ወጣት ጓደኞቼን ሳይቀር ቡዳ የሚባል ነገር የለም ብዬ ማሳመን ይከብደኛል፡፡

ይህ ሰዎችን የማግለያ ሰበብ ነው፡፡ ሰዎችን ንዑስ-ሰው አድርጎ የመቁጠር አባዜ ነው፡፡ የሰብኣዊ መብት ዋና ፅንሰ ሐሳቡ ደግሞ ሰዎች ሁሉ ዕኩል ናቸው የሚለው ነው፡፡ ያንን የማያምኑ ሰዎች ባሉበት አገር በመንግሥት ጥረት ብቻ ሰብኣዊ መብት አይከበርም፡፡
--- 
እዚህ ጽሑፍ ላይ የተሰጡ ለማየት እዚህ ጠቅ ያድርጉ!

No comments:

Post a Comment