አንድ የቆየ ቀልድ አስታውሳለሁ፡፡ ኒው ዮርክ ውስጥ አንዲትን ሕፃን ልጅ ውሻ ሲያባርራት ያየ አንድ ሰው ውሻዋን በያዘው አጠገቡ ባገኘው ዱላ መትቶ ይገድልና ልጅቷን ያድናታል፡፡ ይህንን ይመለከት የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ወደሰውየው ይቀርብና ‹‹እሺ፤ ጀግናው አሜሪካዊ - እስኪ የልጅቷን ሕይወት እንዴት እንዳተረፍክ ንገረኝ?›› ሰውየው ‹‹ኧረ እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም›› አለ፡፡ ‹‹እሺ፤ ጀግናው የኒው ዮርክ ሰው..›› ብሎ ጋዜጠኛው ሊቀጥል ሲል÷ ሰውየው ‹‹ኧረ የኒው ዮርክም ሰው አይደለሁ፤ ለጉብኝት ነው የመጣሁት›› ይለዋል፡፡ ጋዜጠኛው ፈገግ ብሎ ‹‹ታዲያ የምን አገር ሰው ነህ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ሰውዬው ‹‹የሳውዲ አረቢያ›› ሲል ይመልሳል፡፡ በማግስቱ የኒው ዮርክ ጋዜጦች ‹‹አንድ አክራሪ ኢስላሚስት በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ውሻ ቀጥቅጦ ገደለ›› የሚል ዜና ይዘው ወጡ፡፡ ጆርጅ ቡሽ በዘመናቸው ከሰሯቸው ስህተቶች በሙሉ የከፋ ሊባል የሚችለው በሽብርተኞች ላይ ባወጁት ዘመቻ ‹‹ሽብርተኛ›› ማለት ‹‹ሙስሊም›› ማለት እንዲመስል ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህንን ለማስተባበል መንግስታቸው ቢደክምም ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎች የተወናበደ አመለካከት አፍርተው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ብስጭት ሃይማኖታዊ ሕልውናቸውን ለማዳን የፈለጉ የሚመስሉ ምስኪኖች አልቃይዳን ለመደገፍ ተገድደዋል፡፡ አሜሪካ የምታደርገው ማናቸውም ነገር በሌላው ዓለም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ሉላዊነት (globalization) ባመዛኙ አሜሪካዊነት (americanization) መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ሐቅ ነው፡፡ የአሜሪካ ተጽዕኖ ለሁሉም የዓለም አገራት ይዳረሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ይሄ ተጽዕኖ ይንፀባረቅ ይሆናል የሚለው ስጋት ለብዙዎቻችን ልብ የሚያርድ ጉዳይ ነው፡፡
Passionate about the ideas of liberty and dignity, and of course prosperity too.