(በፍቃዱ ኃይሉ)
ይህን መጣጥፍ ያዘጋጀሁት እያስጴድ ተስፋዬ “ምክረ-ሀሳብ ለረጋ ፖለቲካዊ ስርአት” በሚል ላቀረበው ጽሑፍ መጋቢ መልስ ይሆን ዘንድ ነው። በቅድሚያ እያስጴድ ጊዜ ወስዶ እና አሰላስሎ “የተረጋጋ ስርዓተ ማኅበር ለመፍጠር እንቅፋት ሆነዋል” ያላቸውን ነጥቦች በመዘርዘር እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በመሰንዘር ውይይት ለማነሳሳት በመሞከሩ ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ። እንዲህ ዓይነት የሰከነ ውይይት እና ቆም ብሎ ለማሰላሰል የሚረዳ መጣጥፍ ማዘጋጀት በተለይ በዚህ ሁሉ ነገር በሚጣደፍበት እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሲዎች ትኩረት ባጠረበት ጊዜ አስቸጋሪ እንደሆነ እረዳለሁ። ሆኖም፣ የውይይቱ በረከት እንዳያመልጠኝ፣ እሱ በቀደደው የውይይት አጀንዳ ላይ ተመርኩዤ የኔንም ሐሳቦች እንደሚከተለው አቀርባለሁ። (ጽሑፉን በፒዲኤፍ ለማንበብ ይህንን ሊንክ ይከተሉ።)
ይህ ጽሑፍ ሦስት ዋና ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ክፍል “የእያስጴድን አንብሮ” (Eyasped’s Thesis) እኔ በተረዳሁት ልክ አሳጥሬ የማቀርብበት ነው። ሁለተኛው ክፍል አንብሮው ላይ ግምገማ የማቀርብበት ነው። ሦስተኛው ክፍል እያስጴድ ማካተት ነበረበት የምላቸውን “ተጨማሪ ሐሳቦች” የማቀርብበት ነው።
1. የእያስጴድ አንብሮ
የመጋቢ መልስ ሐሳቤን ከማቅረቤ በፊት የእያስጴድ አንብሮ (thesis) የያዛቸውን ጭብጦች፣ እኔ በተረዳሁት መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መጣጥፉ በአራት ምዕራፎች የተቀነበበ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን የተረጋጋ ስርዓት ማኖር ለምን እንደተሳነን ይተነትናል። ሁለተኛው ምዕራፍ ችግሩን የመመልከቻ መነፅር ያቀርባል። በሦስተኛው ምዕራፍ ወደ መፍትሔ የሚወስደንን ማዕቀፍ ያመላክት እና በአራተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ አዲስ አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ በመመሥረት ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ይደመድማል። (የእያስጴድን አንብሮ ጨምቄ በማቀርብበት እና በምገመግምበት ጽሑፍ ውስጥ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሞችን ለእኔ አጻጻፍ ዘዬ በተመቸ መልኩ እንደቀየርኳቸው ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ።)