Pages

Monday, February 11, 2019

ለውጡ እና የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ


አሁን እየተካሔደ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ፍኖተ ካርታ የለውም በሚል በተደጋጋሚ ተተችቷል። ይልቁንም፣ ሲሆን ሲሆን ለብዙኃን መገናኛዎች አጀንዳ በማበጀት፥ ሳይሆን ሳይሆን ደግሞ “ሚዲያዎች ምን አሉ?” የሚለውን እያሳደዱ መልስ በመስጠት የተጠመደ ለውጥ ነው የሚለው የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል። ብዙኃን መገናኛዎች በለውጡ ላይ ይህንን የሚያክል ትልቅ ተፅዕኖ እንዳላቸው ከታወቀ ዘንዳ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። ለውጡ ፍኖተ ካርታ ባይኖረውም፥ ብዙኃን መገናኛዎቹ ግን ፍኖተ ካርታ ሊኖራቸው ይገባል፤ “ምን-ለምን-ለማን ነው የሚጽፉት ወይም ለተደራሲዎቻቸው የሚያቀርቡት?” የሚለውን በነሲብ ሳይሆን በነቢብ ቢያድርጉት መልካም ነው በሚል ዓላማ ይህ ጽሑፍ እንደ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።

የብዙኃን መገናኛዎች ሚና በጥቅሉ

በመሠረቱ የብዙኃን መገናኛዎች ሚና “ትርክት ማኖር” ነው። ዜና፣ ትንታኔ፣ ምርመራ፣ ማጋለጥ… ሁሉም አንድ ዓላማ አላቸው። በትርክት መብለጥ ነው። አንድ ጥሬ ሐቅ ከብዙ አንግሎች ‘ሪፖርት’ ሊደረግና ሊተነተን ይችላል። ሰዎች ያንን ጥሬ ሐቅ እንዴት መረዳት እንዳለባቸው የሚወስኑበት ደጋግመው ከሰሙት ወይም ደግሞ ይበልጥ ካሳመናቸው ትንታኔ አንፃር ነው። ስለዚህ ሁሉም ብዙኃን መገናኛዎች ዋነኛ ዓላማቸው ሐቁን ለዜጎች ማድረስ ነው ቢባልም ቅሉ፥ ዋናው ቁም ነገር ሐቁን የሚተነትኑበት መንገድ ነው።

ለምሳሌ ያክል የአድዋ ጦርነትን ብናስታውስ፣ ለኢትዮጵያውያን የምሥራች ሲሆን፥ ለጣሊያኖች ደግሞ መርዶ ነው። የጣሊያን ብዙኃን መገናኛዎች መርዶውን ለዜጎቻቸው ያደረሱት በቁጭት ሲሆን፣ ‘የተነተኑትም ለሽንፈት የዳረገን ምንድን ነው? ለወደፊቱስ ምን ማድረግ አለብን?’ በሚል ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ቢኖራት ኖሮ ትንታኔው በተቃራኒው ታቀርብ ነበር። ስለሆነም የብዙኃን መገናኛዎች የመጨረሻ ግብ ለቆሙለት ወገን ወይም ግብ ተሥማሚውን ‘ትርክት መፍጠር’ እና ያንን ትርክት ገዢ (mainstream) ማድረግ ነው።

ብዙኃን መገናኛዎች ከለውጡ በፊት

ከለውጡ በፊት የነበሩት ብዙኃን መገናኛዎች ኹለት ዐቢይ ትርክቶችን በማኖር ሥራ ተጠምደው ነበር። አንዱ ‘ልማታዊ’ ከሚባሉት ወገን ሲሆን፥ የመንግሥትን በጎ አስተዋፅዖ በማጉላት እና ስህተቶቹን በማሳነስ የገዢውን ቡድን ተቀባይነት ለማሳደግ የሚፍጨረጨረው ትርክት አኗሪ ወገን ነው። ሌላኛው ደግሞ ‘አብዮታዊ’ ልንለው የምንችለው እና የመንግሥትን ስህተቶች በማጉላት እና በጎ አስተዋፅዖዎቹን በማንኳሰስ ገዢው ቡድን የነበረውን ተቀባይነት በማሳጣት ሕዝቡ እምቢ እንዲል የሚያደርግ ትርክት አኗሪ ወገን ነው። ኹለተኛው ወገን በጣም የተከፋፈለ ቢሆንም ገዢውን ቡድን በሚመለከትበት ዓይን ግን አንድ ሆኖ ከርሟል። ከዚህ መሐል ያሉት እምብዛም ተፅዕኖ ፈጣሪ አልነበሩም።

በኹለቱ ትርክት አኗሪዎች ፉክቻ [የውስጥ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ] ‘አብዮታዊው’ ብዙኃን መገናኛ አሸንፏል። ገዢው ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ አመኔታ በማጣቱ ‘ገዢ’ የሆነውን ትርክት ተቀብሎ፣ ይቅርታ በመጠየቅ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት እስከ መገደድ ደርሷል። አሁን የፖለቲካ ሒደቱ ተንጓሎ ግልጽ አቋሙ አልጠራም። በሽግግሽጉ ቦታ የተለዋወጡ፣ ዳር ቆመው የሚታዘቡ፣ እዚህም እዚያም የሚንቀዠቀዡ ትርክቶች እና ትርክት አኗሪዎች አሉ። አንድ የማይታበለው ነገር ግን በርካታ ብዙኃን መገናኛዎች መድረኩን እየተቀላቀሉ ነው። በርካታ ቡድኖች በርካታ ልሳኖች ይኖሯቸዋል። ከቡድን ባሻገር አንድን ዓላማ (ለምሳሌ ዴሞክራሲያዊነትን፣ ሊበራሊዝምን፣ ወግአጥባቂነትን፣ ወዘተ…) ወግነው እሱን ለማስረፅ የሚነሱም ይኖራሉ። የሆነ ሆኖ አሁን ኹለት ዐቢይ ትርክቶች ብቻ ሳይሆን በርካታ ሆነው ሊበቅሉ ይችላሉ። በገዢው ቡድን እና ተቃዋሚዎች መካከል (ከላይ ወደ ታች፣ ከታች ወደ ላይ) የነበረው የትርክት ጦርነት አሁን በአራቱም ማዕዘን ይሆናል፦ ሽቅብ ቁልቁል እና አግድም።

ለውጥ እና ብዙኃን መገናኛዎች…

የለውጥ ወቅት የድርድር ወቅት ነው። ስለሆነም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እና ‘የፍላጎት ቡድኖች’ (interest groups) መደራደሪያ የሚሆናቸውን፣ ተከታይ የሚያፈራላቸውን እና ኃይላቸውን ማሳያ ትርክት ያንፀባርቃሉ፤ አንዳንዶቹ ያሉትን ብዙኃን መገናኛዎች ይጠቀማሉ፣ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ይዘው ይመጣሉ፣ ቀሪዎቹ የነበራቸውን ልሳን ይጠቀማሉ። ከላይ እንደገለጽኩት በተለይ በዘመናችን የፖለቲካ ድል የሚወሰነው በትርክት በመብለጥ ነው።

ገዢው ቡድን የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎችን እና ራሱ ያቋቋማቸውን የግል ብዙኃን መገናኛዎች መጠቀሙን ይቀጥላል። “የዜግነት ፖለቲካ” አራማጆቹም፣ ብሔርተኞቹም የየራሳቸው ብዙኃን መገናኛዎች አሏቸው፣ የሌላቸውም እያቋቋሙ ነው። ስለዚህ የድርድሩ ውጤት የሚወሰነው ከእነዚህ የፖለቲካ ትርክት አኗሪዎች መካከል የበለጠ ገዢ በሚሆነው ነው።

በዚህ መሐል በተለይም የማይታረቁት የብሔርተኝነት ሕልሞች እና አረዳዶች ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት ማድረጋቸው አይቀርም። ሆኖም ፍጭቶቹ ከሐሳብ ዘልቀው ሕዝቡን ወደ ጠርዝ በመግፋት ከሐሳብ ፍጭት ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊያመሯቸው እንደሚችሉ ሥጋት አለ። ይህ ደግሞ ተራ ግምት የወለደው ሥጋት ደሳይሆን ከለውጡ በፊት በነበራቸው ሚና የታየ ጉዳይ ነው።

አሁን ምን ይደረግ?

በመጀመሪያ ደረጃ ብዙኃን መገናኛዎች ያላቸውን ኃይል መረዳት አለባቸው። እንደ ሲኤንኤን እና እንደ ፎክስ ኒውስ በሐሳብ መቆራቆዝ አንድ ነገር ነው። እንደ ሬዲዮ ኮሊንስ የዘር ማጥፋት መስበክ ሌላ ነገር ነው። ስለዚህ ያሉትም ይሁኑ የሚመጡት ብዙኃን መገናኛዎች ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን እና የተጠያቂነት ኃላፊነታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሥራቸውን መሥራታቸው የሁሉም ነገር ሀሁ ነው።

የሚፈለገው ለውጥ መጥቷል እና ያለፈው ‘አብዮታዊ’ የማፍረስ እና ቅቡልነት የማሳጣት (deconstructing and delegitimizing) ትርክት አያስፈልግም እና የሚፈለገውን የፖለቲካ ስርዓት እንደ አዲስ የማነፅ እና ተቀባይነት የመገንባት (constructing and legitimizing) ሥራ ነው የሚያስፈልገው የሚሉ የብዙኃን መገናኛዎች ተዋናዮችም ሆኑ፣ የለም ለውጡ የሚፈለገውን ዓይነት አይደለም፣ ወይም ደግሞ ገና ይቀረዋል የሚሉትም ቢሆኑ በኃላፊነት ሥራዎቻቸውን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ደግሞ መጪው ጊዜ የምርጫ እንደመሆኑ መጠን፥ ያለ ደም መፋሰስ ብሎም የሕዝቡን ምርጫ ባከበረ መልኩ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ቅድሚያ እና ጥንቃቄ ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል።

ይህንን እውን ለማድረግ የብዙኃን መገናኛዎች ምክር ቤት ካሁኑ ማቋቋም ወይም ደግሞ የነበረውን ገለልተኝነቱን እና አቅሙን ማጠናከር ነው። ይህንን በማድረግ ብዙኃን መገናኛዎቹ የትርክቶቻቸው ልዩነት ሳያግዳቸው፣ የመንግሥት የፀጥታ እና የፍትሕ አካላት ጣልቃ ሳይገቡባቸው ከአውዳሚ አካሔድ ራሳቸው በራሳቸው የሚቆጣጠሩበት መንገድ ማመቻቸት ይቻላል። ይታሰብበት።

1 comment:

  1. Harrah's Cherokee Casino Resort to reopen after
    Harrah's Cherokee Casino Resort in Cherokee is 목포 출장샵 to reopen on 광주 출장마사지 Monday, May 태백 출장샵 29 after a safety review and testing revealed a 평택 출장마사지 large lead-up 제주 출장안마 to the

    ReplyDelete