በኢትዮጵያ የጋዜጦች እና መጽሔቶች አማራጭ አልባነት ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክሪያሲያዊ ስርዓት እንድትሸጋገር በማገዝ ረገድም ይሁን የነቁ እና መረጃ ያላቸው ዜጎችን በመፍጠር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዳይጫወቱ አድርጓል። ጎረቤቶቻችን እነ ኬንያ ከኛ ግማሽ በታች የሕዝብ ብዛት ኖሯቸው ከእኛ እጥፍ ድርብ የበዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በየቀኑ ለስርጭት እና ለንባብ ይበቃሉ። እኛስ ምንድነ ነው ችግራችን? (የሚከተሉት ከልምድ የታዘብኳቸው ፈተናዎች ናቸው፤ አንባቢ ላለማሰልቸት ባጭር ባጭሩ ነው የምጠቅሳቸው።)
፩ኛ፣ የንባብ ባሕል ደካማነት
ኢትዮጵያውያን የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ነን እንበል እንጂ አንባቢ ሕዝቦች አይደለንም። የተማሩ ሰዎች ቁጥር ማነስ ብቻ ሳይሆን፣ ፊደል የቆጠሩትም የአንባቢነት ልምድ የላቸውም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ብዙ ጊዜ ጋዜጦቹ እና መጽሔቶቹ የሚነበብ ብዙም አዲስ ነገር የላቸውም ቢባልም፣ እውነቱ ግን የሚነበብ ነገር ይዘው የሚመጡትም ቢሆኑ በቅጡ እየተነበቡ አለመሆናቸው ነው። ጋዜጣና መጽሔት አንባቢዎች ጥቂት ጡረተኞችና የፖለቲካ ወይም የዝነኛ ሰዎች ወሬ ፈላጊዎች ብቻ ናቸው። ስለዚህ የንባብ ባሕል አለመኖሩ የኅትመት ብዙኃን መገናኛውን ከሚያዳክሙት ፈተናዎች ቀዳሚው ነው።
፪ኛ፣ የሕግ እና አፈፃፀም አፋኝነት
ከብሮድካስት ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ እስከ ብዙኃን መገናኛ ነጻነት እና የመረጃ ማግኘት መብት አዋጅ፣ እንዲሁም የሳይበር እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጆች በአንድም በሌላም መንገድ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎችን አዳክመዋል። እነዚህ አዋጆች የተፈጥሮ ነጻነትን እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ከመገደባቸውም ባሻገር የፍርሐት ድባብ በመፍጠር ነጻ ውይይትን፣ ነጻ ሪፖርትን እና ነጻ ምርመራን የማይቻል እንዲሆን አድርገዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ በአሠራራቸው፣ በቢሮክራሲያቸው እና በእጅ አዙር ቁጥጥራቸው ወደ ኅትመት ሚዲያ ሥራ መግባትንም ይሁን ገብቶ መቆየት መቻልን ከባድ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም የመንግሥት ሕዝብ ግንኙነቶች (መንግሥት በኢትዮጵያ የአብዛኛው መረጃ ባለቤት ነው) ለነጻ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎች መረጃ ባለመስጠት ሚዲያዎቹ አዲስ ነገር አልባ እንዲሆኑ በማድረግ ዋጋ ቢስ ያደርጓቸዋል።
፫ኛ፣ የማስታወቂያ አሰጣጥ ባሕል ጉድለት
የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎች በቅጂ ሽያጫቸው ብቻ ለረዥም ጊዜ መዝለቅ አይችሉም። (በነገራችን ላይ በ1997 ምርጫ ትኩሳት ወቅት ጋዜጦች በአማካይ መቶ ሺሕ ገደማ ኅትመት እና ሥርጭት ነበራቸው። ከያኔው ጋዜጦችን የመዝጋት ዘመቻ ወዲህ ትልቁ የግል ጋዜጦች ሥርጭት 30 ሺሕ ነበር። አሁን ሀያ ሺሕም አልገቡም። በዚያ ላይ ብዙ አንባቢዎች ከመግዛት ይልቅ ተከራይቶ በገረፍ ገረድ አንብበው ሲያበቁ ለአዟሪዎች የመመለስ ልምድ አዳብረዋል።) ይሁንና ኅትመቶቹ ወጪያቸውን ለመሸፈን እና ትርፍ ለማግኘት ማስታወቂያ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ማስታወቂያ ሰጪዎች በፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመሠረተ አድልዖ ይፈፅማሉ። የመንግሥት እና የደጋፊዎቹ ሚድያዎች ያለ ችግር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ማስታወቂያ ሲያገኙ፣ የግል ኩባንያዎችም ለነርሱ ማስታወቂያ መስጠት አይፈሩም። በተቃራኒው ነጻዎቹ የኅትመት ሚዲያዎች በመንግሥት ድርጅቶች ይገለላሉ፣ በግል ኩባንያዎችም "ጣጣ ያመጡብናል" በሚል ይፈራሉ፤ የመንግሥት አፋኝነት ጦስ ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ።
ከማስታወቂያ አሰጣጥ ቅድመ ሁኔታ ባፈነገጠ መልኩ፣ በዚህ ሰበብ ብዙ ቅጂ የሚያሳትሙት ጋዜጦች እና መጽሔቶች እያሉ፣ ጥቂት ቅጂ የሚያሳትሙት እና ለመንግሥት "ችግር ያልሆኑት" ጋዜጦች በርካታ ማስታወቂያ ያገኛሉ።
፬ኛ፣ የሙያ እና ሥነ ምግባር ጉድለት
በዚህ ጉዳይ ነጻ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎች እርስ በርስ ጣት ይቀሳሰራሉ። መንግሥትን (ገዢውን ቡድን) የሚተቹት፣ የሚያወድሱትን ወይም ከመንግሥት "የሚያነካካውን" ዜና ከመሥራት የሚቆጠቡትን "ነጋዴ"፣ "ገንዘብ አታሚዎች" ይሏቸዋል። በተቃራኒው እነዛኞቹ የመንግሥት ተቺዎቹን "የአስተያየት ተቺዎች" ('opinion merchants') ይሏቸዋል። ጣት ከመቀሳሰር ውጪ ወደ ራሳቸው የመመልከት እና የአንባቢውን ፍላጎት የማሟላት ልምድ ከሁለቱም ወገን የለም ማለት ይቻላል። የብዙኃን መገናኛዎች ሚና መረጃ መስጠት፣ ማስተማር እና ማዝናናት ቢሆንም እነዚህን ወይም ከነዚህ አንዱን በምን ዓይነት ብቃት ለሕዝቡ እያቀረብን ነው ብለው ባለመጠየቃቸው ምክንያት ያለው ውሱን አንባቢም ቢሆን ከጋዜጣ እና መጽሔቶች ሸመታ ራሳቸውን አግልለዋል። ስለዚህ አንባቢዎች የኅትመት ሚዲያዎቹን "የእነዚህ" እና "የእነዚያ" ሙያዊ እና የሥነ ምግባር ነጻነታቸውን ባለመጠበቃቸው እና ገለልተኝነታቸውን ባለማረጋገጣቸው ምክንያት "እነ እከሌ ምን አሉ?" ከማለት ውጪ ፋይዳ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል።
፭ኛ፣ የማተሚያ ቤቶች እጥረት
አሁን ያሉት አብዛኛዎቹ ጋዜጦች የሚታተሙት በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነው። በሱ አቅም ጋዜጣ ማተም የሚችሉት ሌሎችም የመንግሥት ማተሚያ ቤቶች ናቸው። ብዙዎቹ የግል ማተሚያ ቤቶች የገበያ እጥረት ስለሌለባቸው ጋዜጦችን በማተም "የፖለቲካ ጣጣ" ማስከተል አይፈልጉም። የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ከዚህ በፊት ማተሚያ ቤት ለማቆም ያደረገው ሙከራ በመንግሥት ተደናቅፎበታል፤ በዚህ ሁኔታ አንዳንዴ የእሁድ እትሙን ማክሰኞ ይዞ ለመውጣት ይገደዳል። ሌሎችም ሙከራዎች አልተሳኩም። ስለዚህ በብቸኝነት (monopoly) የያዘው ብርሃንና ሰላም ሲያሻው የሚያትምላቸውን ያማርጣል፣ ሲያሻው ሳንሱር አድርጎ (ፍትሕ ጋዜጣን በ2004 እንዳቃጠለው) እርምጃ ይወስዳል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዋጋ በየጊዜው ይጨምራል። ከአንዳንድ ባንኮች የበለጠ (ዘንድሮ ለምሳሌ 203 ሚሊዮን ብር) የሚያተርፈው ብርሃንና ሰላም ለኅትመት ሚዲያው ማተሚያ ቤቶች ፈተና መሆናቸውን ማሳያ ምሳሌ ነው።
፮ኛ፣ የሥርጭት ሥራው ኋላ ቀርነት
ጋዜጦችን የማሠራጨት እና የመቸርቸሩ ሥራ በጣም ኋላ ቀር ከመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባቸዋል። አከፋፋዮች 'ኔትዎርካቸው' በጣም ጠባብ ከመሆኑም በላይ ኅትመቶቹ ምን መያዝ እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው መናገር ይዳዳቸዋል። በዚያ ላይ ብዙ አዟሪዎች ከገበያ ወጥተዋል። ከ1997 በፊት በርካታ ጋዜጦች በየቀኑ ይወጡ ስለነበር ብዙ አዟሪዎችም የሥራ ዘርፍ አድርገውት ነበር። አሁን በየቀኑ የሚታተሙ ነጻ ጋዜጣዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ብዙዎቹ ሥራ ቀይረዋል። ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉት ቁጥራቸው በጣም ቀንሷል። ይህም የጋዜጣና መጽሔት ሥርጭትን በጣም ቀንሶታል።
ይሁን እንጂ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎችን እየፈተኑ ያሉት እነዚህ ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ የማኅበራዊ ሚድያዎች መምጣትም ቀላል ፈተና አይደለም። ቢሆንም ግን ማኅበራዊ ሚድያዎች ክስተትና ኹነት ማራገብ እንጂ ወጥ እና የተሟላ መረጃ ማቅረብ ላይ ብቁ አይደሉም። በዚያ ላይ ተዳራሽነታቸው ገና ጨቅላ ነው። ስለዚህ ሙሉ ፈተና አልሆኑም።
የሆነ ሆኖ ሁሉም ፈተናዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከመንግሥት አፋኝነት [ታሪክ] ጋር የተያያዙ ናቸው። በመሆኑም የሚድያ ሕግጋትን የሚከልሱ ሰዎች የመንግሥት አፈና በሕግ፣ በአሠራር፣ በነጻ ገበያ አፈና፣ በተዘዋዋሪ ማስፈራሪያ እና ቁጥጥር እንደሚከሰት አውቀው፣ መንግሥትን ማቀቢያ፣ ብዙኃን መገናኛዎችን ደግሞ ነጻ ማውጫ ዘዴዎችን መቀየስ አለባቸው። ሌላው ዕዳው ገብስ ነው።
Comments
Post a Comment