የሰው ልጆች ሰው ለመሆን ማለቂያ የሌለው አብዮታዊ ጉዞ ውስጥ ናቸው፡፡ እንደመታደል ሆኖ፣ የሰው ልጆች የላቀ እና እየላቀ የመጣ አእምሮ ባለቤት በመሆናቸው ምድርን እንደግል ንብረታቸው፣ ራሳቸውንም ተለይቶ እንደተመረጠ ፍጡር እየቆጠሩ፣ ምድርን ለራሳቸው ምቾት እያሾሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የሰው ልጆች በሠለጠኑ ቁጥር ርሕራሔያቸው እየጨመረ፣ አውሬነታቸው እየቀነሰ መጥቷል። የራሳቸውን ነጻነት የሚያከብሩትን ያክል የሌሎችንም ለማክበር እየተጉ መጥተዋል። የሰው ልጆች ዛሬ ከራሳቸው አልፈው ስለአካባቢያቸው ብዝኃ ሕይወት እስከመጨነቅ ደርሰዋል። የሰው ልጆች ረዥም ጉዞ ገና አላለቀም። የሰው ልጆች ሰው የመሆን ጉዞ የት ተጀመረ? በየት በኩል አለፈ? ዛሬ የት ደረሰ? ነገስ ወዴት ይጓዝ ይሆን? የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የሰው መሆንን ጉዞ በወፍ በረር በመቃኘት የሰውነትን ዓላማ መገመት ነው። ቶማስ ፍሬድማን ሉላዊነት 3ኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጽፏል። የመጀመሪያው ደረጃ የአገረ-መንግሥታት እርስበርስ መተሳሰር ነው። ሁለተኛው ደረጃ የንግድ ኩባንያዎች ብዙ አገራት ላይ መሥራት መቻልና እርስ በርስ ግንኙነት ነው። የመጨረሻውና ሦስተኛው ደረጃ የሰዎች ድንበር ዘለል የአንድ ለአንድ ግንኙነት፣ የትብብር እና የውድድር ዕድል መጨመሩ እና መጠናከሩ ነው። እውነትም ዛሬ ሉላዊ ዜጋ (global citizen) መሆን ከመቼውም ግዜ በላይ ቀሏል። ይህ ክስተት የሰው መሆን ጉዞ አቅጣጫ ድንበር የለሽ የዓለም ዜጋ መሆን መሆኑን ይጠቁመን ይሆን? በዓለማችን አሁን ላይ በአንድ ወቅት 7 ሺሕ ገደማ ቋንቋዎች ነበሩ። በአጥኚዎች ትንበያ መሠረት ከነዚህ ውስጥ በመጪዎቹ መቶ ዓመታት ውስጥ የሚቀሩት መቶዎቹ ብቻ ቢሆኑ ነው። በተረፈ ቀሪዎቹ ወይ ተናጋሪ በማጣት፣ ወይ ከሌላ ጋር ተዳቅለው አዲ...
Passionate about the ideas of liberty and dignity, and of course prosperity too.