Pages

Saturday, March 29, 2014

ኢሕአዴግን እንበይነው!

ሁሉንም ተቃዋሚ እንደአንድ መመልከትም ሆነ በአንድ አዕምሮ እንዲያስብ መጠበቅ የገዢው፣ የተገዢዎች፣ የተቃዋሚዎች ሁሉ የጋራ ችግር ነው። ሚሊዮን ችግሮች እና ሚሊዮን ተቃዋሚዎች ባሉበት አገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ሁሉ አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። ይሁን እንጂ ሁሉም ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን በቅጡ ያውቃሉ ብሎ ለማለትም ያስቸግራል፤ ምክንያቱም “በስመ ተቃዋሚ ሲሳሳሙ" ማየት የተለመደ ነው። ተቃዋሚዎችን በተቃውሞ አካሔዳቸው መግባባት ላይ መድረስ እንዲያቅታቸው ከሚያደርጋቸው ችግር አንዱ ኢሕአዴግን የሚበይኑበት (define የሚያደርጉበት) መንገድ መለያየቱ ወይም ግልጽነት ማጣቱ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ብያኔ ለምን ያስፈልጋል?

40 ዓመት ወደኋላ መለስ ብለን የአብዮቱን ልጆች ለመከፋፈል እና ለእርስበርስ እልቂት የዳረጋቸው ዋነኛውን፣ የሚታገሉትን አካል (ደርግን) የበየኑበት መንገድ ነው። የኢሕአፓ እና የመኢሶን ዋነኛ ልዩነት፣ የኢሕአፓና አንጃ እያለ የሚጠራቸው አባላቱ መካከል የተከሰተው የሐሳብ መሰነጣጠቅ፣ ብሎም እርስበርስ መጨራረስ ደርግን የሚበይኑበት መንገድ መለያየትን ተከትሎ የተወለደው ደርግን ለማስወገድ የመረጡት መንገድ ነው። ሁለቱ (የተቀናቃኝ ወገን ብያኔ እና የመቀናቀኛ መንገድ ምርጫ) ተሰናስለው የሚኖሩ ጉዳዮች ናቸው። በጥንቃቄ ሳይጤን የሚገበቡበት ገደል አይደለም።

ኢሕአዴግ፣ በዚህ ረገድ ራሱን ግልጽ የማድረግ ችግር የለበትም። ተቀናቃኞቹን አንዱን አሸባሪ፣ አንዱን የአሸባሪ ደጋፊ፣ ሌላውን ለዘብተኛ እያለ የሚኮረኩምበትን መንገድ አስቀምጧል። ኢሕአዴግ መሣሪያ ታጣቂ እንደመሆኑ ተቀናቃኞቹን ባይበይናቸውም ቅሉ ማሽመድመጃ መንገድ አይቸግረውም። ለተቃዋሚዎች ግን ‘ኢሕአዴግ ምንድን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሕልውና ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ወዴት እና እንዴት እየሄደ እንደሆነ የሚያውቁበት ወሳኝ ጥያቄ ነው።

የበኩር ጥያቄ፤ ኢሕአዴግ ምን ያስባል?


ኢሕአዴግ እንደማንኛውም ገዢ ፓርቲ በፖለቲካዊ ብልጫ ሥልጣን ላይ የቆየ ፓርቲ ነው? በኃይል ሥልጣን ተቆጣጥሮ የሚኖር ፓርቲ ነው? እያጭበረበረ የሚኖር ፓርቲ ነው? በኃይል ሥልጣን ተቆጣጥሮ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን ላይ የቆየ ፓርቲ ነው? ሕዝባዊ ይሁንታ ባገኘ መንገድ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ኃይሉን መከታ በማድረግ ሥልጣኑን ያለመጋራት የተቆጣጠረ ፓርቲ ነው? በኃይል ሥልጣን ተቆጣጥሮ በኃይል ሥልጣኑን እያስጠበቀ ያለ ፓርቲ ነው? ወይስ ምንድን ነው?…ብዙ ዓይነት ትርጉሞች (ሁሉም እውነት ያላቸውን) ማስቀመጥ ይቻላል። የራስንና አንድ ወጥ ትርጉም ማስቀመጥ የሚበጀው የሚከተሉትን የትግል ስልት ለማወቅ እና የሚጠብቁትንም (what to expect) ለማወቅ ነው።

በአማራጭ ፓርቲዎች መካከል እና ለዴሞክራሲያዊነት  በሚደረጉ ነጻ (የአራማጆች እና የሲቪል ማኅበረሰብ) ትግሎች ምን ዓይነት መሆን አለባቸው የሚለውን መወሰን የሚቻለው የሚታገሉለትን ነገር በማወቅ (ለምሳሌ ለዴሞክራሲ በዴሞክራሲያዊ መንገድ) ከሚለው በተጨማሪ ተቀናቃኝ አካላትን በሚገባ በማወቅና በመበየንም ጭምር ነው። የኢሕአዴግን ማንነትም በቅጡ መበየን የሚያስፈልገው አላስፈላጊ ጊዜ፣ ገንዘብና ጥረት ላለማባከን እና የጠበቁትን ውጤት ለማግኘት ነው።

‘ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በኃይል ተቆጣጥሮ በኃይል እያስጠበቀ ያለ ድርጅት ነው’ ብለን ካልን ሠላማዊ ትግል የሚባለው ሁሉ ትርጉም ላይኖረው ይችላል። ግን ይህንን ለማለት የሚያስችል በቂ መረጃ አለ ወይ? ኢሕአዴግ ብረት ታጣቂውን ደርግ ለመገርሰስ ከኃይል ውጪ አማራጭ ነበረው? የሥልጣን ባለቤት ከሆነ በኋላ ሥልጣኑን ያላስረከበው በፓርቲው እምቢተኝነት [ብቻ] ነው ወይስ የተቀናቃኞቹም እጅ (ድክመት) አለበት? ኢሕአዴግን ከኃይል መለስ ባለ ነገር ከሥልጣን ለማውረድ የሚያስችሉት በሮች ሁሉ ተዘግተዋል? ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አባላት ያሉትን ፓርቲ ‘ጠላት’ ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል ሁኔታ አለ? ይህ መሰሉ ድምዳሜ እና ፍረጃ በታሪክ ከተሠሩ ስህተቶች አንፃር ምን ያክል የተማረ/የታረመ ነው?

‘ኢሕአዴግ በኃይል ያገኘውን ሥልጣን በሕዝባዊ ይሁንታ (እንበል ምርጫ) ቀጥሎበታል’ ካልን ደግሞ ለስርዓት ለውጥ የሚደረጉ ትግሎች ፍፁም ሠላማዊና ግልጽ መሆን ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይህም እልፍ ጥያቄዎችን ይወልዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ እውን የሥልጣን ርክክብ ማድረግ ይቻላል? ከምርጫ ውጪ የሥልጣን ሽግግር የሚመጣባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ? ኢሕአዴግ ሕዝባዊ ይሁንታ ካለው ትግሉ (ለውጡ) ለምንድን ነው? በሠላማዊ መንገድ የሚመጣው ለውጥ ምን ዓይነት ነው?… ወዘተ።

እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች እንደምሳሌነት ብንወስድም፣ ሌሎችም ጥያቄዎች በተለያዩ ብያኔዎች ላይ ተመሥርቶ ማውጣት ይቻላል። በምሳሌው ውስጥ የተካተቱትን ሁለት ብያኔዎች ተንተርሶም፥ ሁለቱን ብያኔዎች የሚሰጡ አካላት አብረው ሊሠሩባቸው የሚችሏቸው እና የማይችሏቸውን ጉዳዮች አብጠርጥሮ ማውጣትም ያስፈልጋል እንጂ በብያኔ ተለያይተናልና አብረን የምንሠራበት መንገድ የለም ማለት ላይሆን ይችላል። ይህን ባለማወቅ የሚደረግ ትግል ግን መነሻውንም፣ መድረሻውንም የማያውቅ ተራ ጥላቻ የሚመራው ጉዞ ነው።

መበየን ቀላልም፣ ከባድም፤ ትንሽም፣ ብዙም ነው

ኢሕአዴግን የተለያዩ አካላት የተለያየ ብያኔ ይሰጡታል። ኢሕአዴግ ኢትዮጵያዊ (ብሔራዊ) ስሜት የለውም ከሚሉት ጀምሮ ለኢትዮጵያ የመጨረሻው የመድኅን ስጦታ ነው እስከሚሉት ጽንፎች ድረስ የሚደርስ ብያኔዎች አሉት።

እኔ በግሌ ኢሕአዴግ በተለያዩ ሒደቶች ውስጥ የተለያየ ምልከታዎችን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያጎለበተ የመጣ ቡድን ነው ብዬ አምናለሁ። ፕሮፌሰር ክላፋም እንዳሉት፥ ‘ሕወሓት በብሔር ዓይን ኢትዮጵያን እየተመለከተ መጥቶ ገዢ ሆነ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያን ወክሎ (በኢትዮጵያዊ ዓይን) ኤርትራን ጦርነት ገጠመ፤ ይህም ሁለተኛ ዕይታ ሰጠው’። ምናልባት እዚህ’ጋ መጨመር ቢያስፈልግ ሕወሓት (የጠቅላላው ኢሕአዴግ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ እንደመሆኑ) ከምርጫ 97 በኋላ ኢትዮጵያዊ (ኅብረብሔራዊ) ስሜት ማዳበር ባይችል እንኳን ያለሱ ብዙ እርምጃ መጓዝ እንደማይችል ተረድቷል።

ስለዚህ ኢሕአዴግ በሦስት ደረጃዎች ውስጥ አልፎ እዚህ ደርሷል ባይ ነኝ፤ ሁሉንም ነገር በዘውግ-ብሔር ዓይን የሚመለከትበትና የሚተረጉምበት ደረጃ (አንድ)፣ ኢትዮጵያዊ ኅብረብሔርተኝነትን ለአጀንዳ ማስፈፀሚያነት (ለምሳሌ ለጦር መቀስቀሻነት) የሚያውልበት ደረጃ (ሁለት)፣ እና ያለኢትዮጵያዊ ኅብረብሔራዊ ስሜት እና መሰል እርምጃዎች (ምሳሌ የባንዲራ ቀን) መራመድ እንደማይችል የተረዳበት ደረጃ (ሦስት) ናቸው። ይሁን እንጂ የዘውግብሔርተኝነትን እና ሕብረብሔርተኝነትን ሚዛን የሚያስጠብቅበት ግልጽ አካሔድ የለውም፤ ይልቁንም እንደ ሕዝባዊው ስሜት አነፋፈስ ተስማምቶ ለመንፈስ ብቻ እየተፍጨረጨረ ነው።

ኢሕአዴግን ከላይ ልበይነው የሞከርኩት በኢተዮጵያዊነት ስሜቱ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ሥልጣን ላይ ያለውን አመለካከትም በአካሔዱ ለመተርጎም ብሞክርም በርግጠኝነት ልበይነው አልቻልኩም። ኢሕአዴግ ከስኒ ማዕበል በላይ አቅም የሌላቸውን ተቃዋሚዎች ይቀበላል። ከዚያ በላይ ያሉትን ግን በቀና ልቦና እንደሚቀበል አላሳየም፤ ሆኖም በሙሉ አቅም ተፈትኗል ማለትም አይቻልም። የደኅንነት፣ የኮሙኒኬሽን እና የመከላከያውን ቁልፍ ሚናዎች በሕወሓት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ እንዲሁም ኢኮኖሚው በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር ስር ማድረጉም ሥልጣኑን በሠላማዊ መንገድ ለመልቀቅ ያለውን ዝግጁነት አጠራጣሪ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ እስከመጨረሻው ድረስ ተገፍቶ ያልተሞከረ በመሆኑ ለሠላማዊ ትግል በር ተዘግቷል ሊባል በማይቻል መወላወል ውስጥ አስቁሞናል።

ብያኔ ቸኩለው የሚገቡበት ጉዳይ አይደለም። ርዕሱን ከብዙ ገጾች ማየት ያስፈልጋል። ነገር ግን ያለብያኔ ቋሚ አቅጣጫ መያዝ አይቻልም፤ ባይሆን ብያኔንም አቅጣጫንም በየጊዜው መከለስ ያዋጣል።

No comments:

Post a Comment