Skip to main content

ይቅርታ ለማን፣ ምሕረት ከማን?


ከቅርብ ግዜ ወዲህ ፌስቡክ የወቅቱን ጨቋኝ ሕወሓትን ጥሎ የቀድሞዎቹን ጨቋኞች እነ ምኒልክን አንስቷል፡፡ ነገርዬው ሲተቹት በመሣሪያ መልስ ከሚሰጥ አካል ጋር ከመታገል፣ በሕይወት ከሌሉት ወይም ቀጥተኛ ተወካይ የሌላቸው ላይ መዘባበት ይሻላል በሚል ይሁን ወይም የጥያቄው አሳሳቢነት ስር ሰዶ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፡፡ በታሪካዊ ጭቆናዎች ትርክቶች ውስጥ ‹አንዱ በማፍረስ፣ አንዱ በመካብ፣ ሌላው ደግሞ በመገላገል› ሁሉም የያቅሙን የሞት ሽረት እያደረገ ነው፡፡

እነ አብይ አቶምሳ ‹‹የታሪክ ኢ-ፍትሐዊነት ላይ መተማመኛ ላይ ሳንደርስ ወደፊት ንቅንቅ የለም› ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ ትላንትና ዛሬ ደግሞ የኔም ወዳጆች በያዝ ለቀቅ የከረመውን ‹‹የይቅርታ ጉዳይ›› ቀለል አርገውም ቢሆን አንስተውታል፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ‹‹የአባት ሀብት ወይም ዕዳ ለልጅ እንደሚተላለፍ ሁሉ የአባት ትውልድ በደል ለልጅ ትውልድ ይተላለፋልና፣ የበዳይ አባት ልጅ ትውልድ የተበዳይ አባት ልጅ ትውልድን ይቅር ቢል ምን አለበት?›› የሚመስል አማራጭ የመፍትሔ ጥያቄ ጠቁሟል፡፡ ማሕሌት ፋንታሁን ደግሞ ‹‹ነገሩን የተበዳይ ቦታ ሆኜ ብሆን ብዬ ሳስበው ከዚህ ትውልድም ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ›› የሚል ጭብጥ ያለው የራሷን የይቅርታ መልዕክት አስነብባናለች፡፡

በኔ አመለካከት የጓደኖቼ ሐሳብ ለውይይቱ ጥሩ መንገድ ቢጠርግም፣ ይቅርታ መጠየቅ እና ምሕረት ማግኘት በአገራችን የብሔር ጭቆና ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ግለሰቦች ‹‹ይቅር ለእግዜር›› የሚፈታ አይመስለኝም፡፡ በጭቆናው ጥልቀት እና አተረጓጎም ላይ እንኳን ገና መግባባት ላይ አልደረስንም፡፡ ስለሆነም እነዚህን መጠየቅ ይቀድማል ባይ ነኝ፤
  • ይቅርታ የሚጠያየቁት አካላት (የሚጠይቀው እና የሚጠየቀው) እነማን ናቸው?
  • ይቅርታ የሚጠየቅበት በደልስ የትኛው ነው?
  • ይቅርታ የሚጠየቀውስ እንዴት ነው?
  • ይቅርታው ያለካሣ ምሕረት ያገኛል ወይ?
  • ምሕረት የሚያስገኘው የካሣ ዓይነትስ ምንድን ነው?
‹አቢሲኒያውያን (በተለይ አማራ እንዲሁም ትግራይ) በተለይ ላለፉት 130 ዓመታት በተለይ በኦሮሞ ሕዝብ (እና እንዲሁም በደቡብ ሕዝቦች ላይ) ‹‹ኢትዮጵያውነትን የመጫን›› (ወይም በሌሎች አነጋገር በኢትዮጵያ ክልል አጥሮ በማስገባት እና በጉልበት በማስገበር) ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውን፣ እምነታቸውን እና ጠቅላላ ማንነታቸውን የሚያጠፋ (ወይም በአማራነት የሚተካ - amharanize የሚያደርግ) በደል /ጭቆና/ አድርሰውባቸዋል› የሚለው ከሞላ ጎደል ጉዳዩን የሚገልጸው ቢሆንም በተለያዩ አካላት ግን የተለያየ አተረጓጎምና የቃላት አጠቃቀምም ጭምር ይኖረዋል፡፡

ብዙ የአማራ ልሒቃን የነበረው የማስገበር ሒደት አገር የማስፋት ነው እንጂ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ለማጥፋት የተደረገ ነገር የለም፡፡ የአማራውም የኦሮሞውም ገበሬ በነገሥታቱ ዕኩል ሲገብር፣ ሲዘረፍ እና ሲበደል ነው የኖረው ይላሉ፡፡ የኦሮሞ ልሒቃንም በበኩላቸው በሕዝባችን ላይ የደረሰው ‹የቅኝ አገዛዝ እንጂ ተራ ጭቆና አይደለም› ከሚሉት (ሌንጮ ለታ) አንስቶ ‹የነዳግማዊ ምኒልክ የማስገበር እርምጃ ነበር፤ አገር በዚያ መንገድ ነው የሚገነባው ቢሆንም የኦሮሞን ማንነት ግን ማጥፋቱ ፍትሐዊ አልነበረም… አሁንም ሒደቱ አልቆመም፡፡› እስከሚሉት (አቶ ቡልቻ ደመቅሳ) እንዲሁም ‹በኦሮሚያ የማንነት ጭቆናዎች ቢኖሩም የመደብ ጭቆናውን ያክል የከፋ አልነበረም፤ የኦሮሞ ባላባቶችም የኦሮሞ ሕዝብን በድለዋል› እስከሚሉት (ዶ/ር መረራ ጉዲና) እና ሌሎችም በከፊል የሚገናኙ እና በተለይ በአማራጭ መፍትሔዎቻቸው የሚለያዩ ማለትም ‹መገንጠል ነው መፍትሔው› በሚሉና ‹የለም ከሌሎች ጋር አብሮ በዕኩልነት ራስን ማስተዳደር› ይሻላል የሚሉ የተለያዩ አተረጓጎሞች አሉበት፡፡

ይቅርታ የመጠያየቅ አጀንዳ ሲመጣ በላይኛው አንቀጽ መሠረት አማራ በዳይ፣ ኦሮሞ ተበዳይ ለማለት የሚያስችሉ በርካታ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልገናል፡፡ የአማራ ባላባቶች (ወይም አማርኛ ተናጋሪዎች ማለትም ይቻላል - ምክንያቱም በተለይ የሸዋ ኦሮሞዎች የሚገባቸውን ያክል እንኳን ባይሆን በሥልጣኑ ውስጥ ቦታ ነበራቸው) በማስፋፋት፣ በነፍጠኝነት (ማለትም በኦሮሞ አካባቢዎች በነፍጥ ኃይል በመስፈር እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ጭሰኛ በማድረግ) ለሠሩት በደል አማራ በጥቅሉ ተጠያቂ መሆን ይችላል ወይ? በወቅቱ ‹‹የጨዋው ልጅ አምስት መቶም አንሞላ›› የሚሉ ባላባቶች በነበሩበት ዘመን ብዙኃኑ የአማራ ተወላጅስ ቢሆን በጭሰኝነት እየገበረ የሚኖር ተጨቋኝ አልነበረም ወይ? ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ መብት አራማጆች የሚያነሱት ወሳኝ መሟገቻ ‹የአማራ ብዙኃን ቢያንስ ማንነቱ አደጋ ላይ አልወደቀም፣ ይልቁንም ተስፋፍቶለት አሁንም ድረስ ስር ለሰደደው ተጠቃሚነት አብቅቶታል› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ብዙኃኑ ተበዳይ በነበረበት ስርዓት ውስጥ በቋንቋ የሚመስሉት ሰዎች በደል በማድረሳቸው የእነርሱን በደል ተንተርሶ ይቅርታ መጠየቅ አለበት የሚለው ውኃ የማያነሳ መከራከሪያ ሊሆን ይችላል - አንዳንዶች ግን ‹‹ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ሲባል ምን አለበት?›› ባዮች ናቸው፡፡

‹ይቅርታ ይጠየቅ - ጠያቂም አይጎዳም፣ ምሕረት አድራጊም አይከስርም› ቢባል ደግሞ ማነው የሚጠየቀው - በጥቅሉ የኦሮሞ ሕዝብ (እና ሌሎችም የደቡብ አካባቢዎች መኖራቸው እንዳይዘነጋ) ቢባል ማነው የሚጠይቅው - የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ ወካይ ፓርቲ (አለው?)፣ ክልላዊ መንግሥቱ (የያኔውን መንግሥት የመወከል ቅቡልነት አለው?) በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡ ይቅርታ የሚጠየቅበት በደልስ የትኛው ነው፣ የመስፋፋቱ ነው? በጭሰኝነትና ማስገበሩ ነው? ‹‹በቅኝ አገዛዙ ነው››? ወይስ አገር በቀሉን ስርዓት (እንበል ‹‹ገዳ››ን) በመተካቱ ነው?

ይቅርታው ተሳክቶ ተጠያየቁ እንበልና ከዚያ በኋላ የሚመጣው ምንድን ነው? ሁሉም ባለበት ይረጋል ወይስ እንደአዲስ ዕቅድ ማውጣት እንጀምራለን፡፡ ለደረሰው በደልስ ካሣው ምንድን ነው?

ሕወሓት ሕገመንግሥቱ በራሱ በደሉን ሽሮ ወደአዲስ ምዕራፍ ተሸጋግረናል ባይ ነው፡፡ በሕገመንግሥቱ የተገኘው ነገር የብሔር ፌዴራሊዝሙ ነው፡፡ ፌዴራሊዝሙ ተበዳይ ብሔረሰቦች ያለፈው በደላቸው ባይካሥም እንደአዲስ ግን ራሳቸውን በራሳቸው መገንባት የሚችሉበትን ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሎ ታምኗል፡፡ ሆኖም አሁንም የብሔር ጭቆናው ቀጥሏል ብለው የሚያምኑ ልሒቃን አሉ፡፡ በተለይ የኦሮምኛ ቋንቋ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት፤ ራስን በራስ የማስተዳደሩ ሚናም በእውነተኛ የኦሮሚያ ወኪሎች እንጂ በእጅ አዙር በሚገዙ ወኪሎች መሆን የለበትም የሚሉ (ይህ እንደተመልካቹ የሚለያይ እውነት ይሆናል) እና ከዚያም ባለፈ ደግሞ የተቀማነው ‹‹ነጻነት›› (ወይም ራስን የቻለ አገርነት) ካልተመለሰ ጭቆናው ቀጥሏል የሚሉም አሉ፡፡ ካሣው እንደየልሒቁ ይለያያል ማለት ነው፡፡ ምሕረቱም ምሕረት ላይሆን ይችላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...