መቶ ዐሥራ
ሰባት ዓመት ወደኋላ፤ መጀመሪያ (ከዚህም ዓመታት በፊት) አውሮጳውያን ኃያላን በበርሊን ያደረጉት ‹‹አፍሪቃን የመቀራመት›› ስምምነት
ይቀድማል፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ሲወስዱ፣ ጣሊያንም ኢትዮጵያ (እና ሶማሊያ…) ደርሰዋት ነበር፡፡ የመጀመሪያው የጣሊያን ጦር በባሕርምላሽ
(የአሁኗ ኤርትራ) በኩል ሲመጣ የወቅቱ የባሕርምላሽ ገዢ የነበሩት የራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) ሠራዊት የጣሊያንን ሠራዊት
ዶጋሊ ላይ በተደረገ ፍልሚያ ከ500 ወታደር 100 ብቻ በሕይወት አስቀርቶ መለሰው፡፡ ያኔ የጣሊያን ፓርላማ ተሰበሰበ፤ ተሰብስቦም
አላበቃ በ332 ለ40 አብላጫ ድምፅ ወደኢትዮጵያ ተጨማሪ (5000ሺ ወታደር የያዘ) ሠራዊት ለመላክ ወሰነ፡፡
ከዚያ በኋላ
ነው የውጫሌ ውል የተከተለው፡፡ ለጠነከረ ወዳጅነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት በምኒልክ እና በጣልያን መልእክተኛ መካከል የተፈረመው
የውጫሌ ውል ደግሞ አማርኛውና ጣልያንኛው አንድ ዓይነት ትርጉም ይኑረው ቢልም አንቀጽ 17 ‹‹ኢትዮጵያ የጣልያን ሞግዚት›› እንድትሆን
በተዘዋዋሪ የሚያታልል ነበር፡፡ ትርጉሙ ሲነቃበት ዐጤ ምኒልክ ውድቅ ከማድረግ አልተመለሱም፡፡ እንግዲህ የአድዋ ጦርነት መነሻ የሚባለው
ይህ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ የበርሊን ስምምነት ሽልማት መሆኗ ግን መሠረቱ ነው፡፡
ጦርነቱ ሲጀመር
አገር ዘመተ፡፡ 80,000 ኢትዮጵያውያን ለጦርነቱ ሲወጡ ከነዚህ ውስጥ ቆመህ ጠብቀኝ ጠብመንጃ የታጠቁት ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ሌላው
ጦርና ጋሻውን እየሰበቀ ወጣ፡፡ በጣሊያን በኩል ደግሞ 18,000 ወታደሮች ተሰለፉ፡፡ የአገር ፍቅር፣ የጀግንነት እና የአትንኩኝ
ባይነቱ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ጀግኖች ተጋደሉ፤ በዕለቱ ጦርነት ማብቂያ ላይ የጣልያን ሠራዊት በአውሮጳውያን የቅኝ ገዢነት ታሪክ ታይቶ
የማይታወቅ እልቂት አስተናገደ፡፡ እስከ 7,000 የሚገመቱ የጣሊያን ወታደሮች ሞቱ፣ 3000 ያህል ተማረኩ፤ በኢትዮጵያ ወገንም
4,000 የሚጠጉ ተሰዉ፣ የቆሰሉት ደግሞ ከ10,000 በላይ ነበሩ፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ሆነ፡፡
የድሉ ዜና
እንደተሰማ የጣልያን ጋዜጦች የጣልያንን ሠራዊት ‹‹ውኃ፣ ውኃ›› ያሰኘችውን የእቴጌ ጣይቱን ፎቶ በሽፋን ገጻቸው ላይ ይዘው ሲወጡ፣
የጣልያን ሕዝብ ደግሞ ውርደቱን ለማውገዝ ‹‹ሆ…›› ብሎ አደባባይ ወጣ፡፡ የ‹‹ኃያል አገራቸው በምስኪን አገር መሸነፍ›› ያንገበገባቸው
ጣልያናውያን በሮም ከፍተኛ ነውጥ ከሰቱ፤ ፖሊስ ነውጡን ለመበተን ቢተጋም ተቃውሞው ግን በአድዋ ድል ሳምንት የወቅቱን የጣሊያን
ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒን ከስልጣን አስለቅቋል፡፡
የአብሮነት ዕድል
የአድዋ ድልን
ለመመስከር ከበቁ ሰዎች መካከል አንድ እንግሊዛዊ ኮሎኔል የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ ‹‹መግነጢሳዊ ምስጢር›› ነው
ብሎታል፡፡ የዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን የማፈራረስ እና አንዲት ኢትዮጵያ የመመስረት ሕልም፣ በዚህም በዚያም በሚያምፁ አገረ-ገዢዎች
ሳቢያ አልተሳካም ነበር፡፡ ዐፄ ዮሐንስም ያንን የዐፄ ቴዎድሮስ ሕልም በራሳቸው መንገድ ለማሟላት ተፍጨርጭረው፣ ነገር ግን ዘመናቸውን
በሙሉ በጦርነት እንደዋተቱ ተሰውተው አልፈዋል፤ ዐፄ ምኒልክንም የዚሁ ዕጣፈንታ ሰለባ ከመሆን ያተረፋቸው የአድዋ ጦርነት እና ድል
ነው፡፡
የአድዋ ጦርነት
ሠራዊት ሁለት ሦስተኛ ያዋጡት ዐጤ ምኒልክ ናቸው፡፡ ቀሪውን ግን የሸፈነው የየአካባቢው ነገሥታት እና ገዢዎች ሠራዊት ነው፡፡ በወቅቱ
ከዐፄ ምኒልክ ጋር ስምምነት ላይ ያልደረሱ (ወይም ማዕከላዊ መንግሥታቸውን ያልተቀበሉ) በርካታ አገረገዢዎች ሳይቀሩ ከጎናቸው ተሰልፈው
ልዩነታቸው በአገር ውስጥ ጉዳይ እንጂ ከአገር ውጪ በሚመጣ ጉዳይ አንድነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ከጦርነቱ መልስም የምኒልክ ማዕከላዊ
መንግሥት በመጠናከሩ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቅርፅ ለመያዝ የሚያበቃ አቅም እና ጥንካሬ አፈራች፡፡
ዐጤ ምኒልክ
ከአድዋ መልስ በመጠኑ የተረጋጋ፣ የተባበረ እና ሰላማዊ አገር መምራት በመቻላቸው አሁንም ድረስ የዘለቁ በርካታ ‹‹የመጀመሪያ››
ነገሮችን ለመመስረት የቻሉት ድሉ ባመጣው ዕድል ነው፡፡
የመታወቅ ዕድል
‹‹የሃይማኖት
ጠላቶቿን ሽሽት በሯን ዘግታ ለአንድ ሺሕ ዓመታት ተኝታ የውጪውን ዓለም ረስታ፣ የውጪው ዓለምም ረሳት›› የተባለቸው ኢትዮጵያ ስሟ
በድጋሚ እንዲታወቅ አድዋ ዕድል ሆነላት፡፡ የአድዋ ድል የአውሮጳን የዓለም መሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ውስጥ የጣለ ገጠመኝ ነው፡፡
የዓለምን ታሪክ በሁለት ከፍለን ብንመለከተው፣ አውሮጳውያን ወደላይ እየገሰገሱ የመጡት እስከአድዋ ዘመን ሆኖ ልክ ከዚያ በኋላ ቀስ
በቀስ ለአሜሪካ አስረክበው ቁጭ እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡
የጣልያኖችን
ሽንፈት የሰሙት አሜሪካኖች በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣቸው ላይ ብቻ ያሰፈሯቸውን ዐብይ ርዕሶች እናስታውስ “Italy’s Terrible Defeat,” “Italy is Awe-Struck,” “Italy
Like Pandemonium,” እና “Italy’s Wrathful Mobs.” የጣልያን ሽንፈት፣ የጣልያን ውርደት ይላሉ እንጂ ባለአገሯ
ኢትዮጵያ፣ አገሯን ተከላክላ ማሸነፏ ኢትዮጵያን ርዕስ ላይ አላስቀመጣትም ነበር፡፡
ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ፡፡ የዓለም መንግሥታት
በሙሉ ከምኒልክ መንግሥትጋ የተለያዩ ስምነቶችን ለማድረግ ይጣደፉ ጀመር፡፡ ብዙ የአውሮጳ መንግሥታት ቆንስላቸውን በኢትዮጵያ መሠረቱ፣
ከዚሁጋ ተያይዞ ዘመናዊ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂዎች እና ዘመናዊ አስተዳደርም ቀስ በቀስ እየተስፋፋ መጣ፡፡
የአድዋ ድል፣ ኋላ ለመጣው የማይጨው ድል እና በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ
ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ ለነበራት ስመ ገናናነት ፈር ቀዳጅ ነው፡፡
የነጻነትና እኩልነት ዕድል
ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ ፍጡራን አለመሆናቸውንና ራሳቸውን በራሳቸው
መምራት እንደሚችሉ በዓለም ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመሰከሩት በአድዋ ድል ነው፡፡ የአድዋ ድል ዜና ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዙ ለነበሩ
አፍሪካውያን ከ‹‹እንቢተኝነት›› ጀርባ ‹‹ነጻነት›› እንዳለ እንዲገባቸው አድርጓል፡፡ አውሮጳውያን አሁንም ድረስ አፍሪካን ከተኛችበት
እንደቀሰቀሷት ያምናሉ፡፡ እነርሱ ባያነቁን ኖሮ ተኝተን የ‹‹ጃንግል›› ኑሯችንን ብቻ እንደምንገፋ ይጽፋሉ፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን
እንዲሁ ነው የምናስበው፣ አፍሪካውያንን ባናነቃቸው ኖሮ ያለምንም ቅሬታ እየተገዙ ይኖሩ ነበር፤ ምናልባት ቢነቁ እንኳን ‹‹ማንነታቸው››
አሁን ከጠፋው በላይ ሙሉ ለሙሉ ከከሰመ በኋላ ነበር፡፡
Comments
Post a Comment