Pages

Wednesday, June 20, 2018

የተዘነጋው የኮንሶ እስረኞች ጉዳይ ("እኛስ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ?")

ፎቶው ላይ ከግራ ወደቀኝ የሚታዩት፤ የኮንሶ መሪ ካላ ገዛኸኝ እና ወንድማቸው

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሕዝባዊ አመፆች በተቀጣጠሉበት ወቅት፣ በሕዝብ ብዛት ትንሿ ኮንሶም ከዐሥር ወራት ላላነሰ ጊዜ ሕዝባዊ ተቃውሞ ታደርግ ነበር። በወቅቱ የመብት ተሟጋቾች አመፁ አገር ዐቀፍ እንደሆነ ለማስረዳት እንደምሳሌ የኮንሶን ጉዳይ ደጋግመው ይጠቅሱት ነበር። በወቅቱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሠላማዊ ተቃውሞዎችን በኃይል በመበተን፣ ብዙዎችን ወደ እስር ቤት አጉረዋል። ከነዚህ እስረኞች ውስጥ የኮንሶ የጎሳ መሪ የሆኑት ካላ ገዛኸኝ ወልደዳዊት ካዮቴ ይገኙበታል። ('ካላ' በጎሳ መሪነት የሚገኝ የጎሳ ሐረግ ማዕረግ ነው።)

ካላ ገዛኸኝ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በሲቪል ምሕንድስና ተመርቀዋል። የጎሳ መሪነቱን ከአባታቸው የወረሱት በጥቅምት 2006 በባሕላዊው ወግ መሠረት ከአባታቸው ነበር። የጎሳ መሪው በኮንሶ ማኅበረሰብ ልማድ መሠረት ልማዳዊ ዳኝነት፣ ግልግል እና ሌሎችም ማኅበራዊ አስተዳደር ይሰጣል። ይሁን እንጂ የአሁኑ የጎሳ መሪ ካላ ገዛኸኝ ሠላማዊ ሕዝባዊ ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት ከሌሎች የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት ጋር ለእስር ከተዳረጉ እና ከማኅበራዊ ኃላፊነታቸው ከተገለሉ አንድ ዓመት ከ10 ወራት አለፏቸው። ካላ ገዛኸኝ በተከሰሱበት መዝገብ ብቻ 43 ሰዎች ተከስሰዋል። ያነጋገርኳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ግን የጠቅላላ እስረኞቹ ቁጥር 467 ነው። እነዚህ ሕዝባዊ ጥያቄ ያነሱ የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት በጊዶሌ ማረሚያ ቤት፣ ኮንሶ ፖሊስ ጣቢያ እና አርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ታስረው ይገኛሉ። ካላ ገዛኸኝ እና ሌሎችም 180 ገደማ ሰዎች የታሰሩት በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ነው። 

ከእስር ውጪ ከመንግሥት የሥራ ገበታቸው ተባርረው (እና ከግንቦት 2008 ጀምሮ) ቤተሰባቸው የኅልውና አደጋ ላይ የወደቀባቸው ከ250 በላይ የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት እንዳሉ ዝርዝሩን እና አቤቱታ ያቀረቡበትን ደብዳቤ ተመልክቻለሁ። 

የኮንሶ ጥያቄ ምንድን ነው?

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ኮንሶ ተጠሪነቷ ለደቡብ ክልላዊ መንግሥት የነበረች ልዩ ወረዳ ነበረች። ይሁን እንጂ ከመጋቢት 2003 ጀምሮ ልዩ ወረዳነቷ ቀርቶ፣ ተጠሪነቷም ለዞን ሆኗል። ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት 'በሰገን አካባቢ ሕዝቦች' አስተዳደር ሥር 'እንደተጨፈለቁ' የነገሩኝ ሲሆን፣ ይህም የራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ከመጣሱም በላይ ከተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች የመገለል ጦስ እንዳመጣባቸው አጫውተውኛል። ይህንንም በመቃወም በ2008፣ የ81ሺሕ ሰዎች ፊርማ በማሰባሰብ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ በመወከል ጥያቄያቸውን ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሁም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል። ሆኖም ያገኙት መልስ የለም። ይልቁንም የፀጥታ ኃይሎች 12ቱን የኮሚቴ አባላት ሊያስሯቸው ሲሞክሩ ሕዝቡ ሆ ብሎ ወጥቶ በማስቆም፣ የኮሚቴ አባላቱ እንዳይታሰሩ በሚል ውክልናቸውን አንስቷል። 

ኮሚቴዎቹ ቢነሱም ተቃውሞዎቹ ግን የቀጠሉ በመሆኑ በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አሰፋ አብዩ ተወካዮቻችሁን ላናግር በማለታቸው 23 ሰዎች ተወክለው አነጋግረዋቸዋል። ወትሮም ጥያቄያቸውን ማስተናገድ የነበረበት ሌላ አካል በመሆኑ የፌደራል ፖሊስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካላ ገዛኸኝን ጨምሮ ሁሉንም ለቃቅሞ ለእስር ዳርጓቸዋል። በእስሩ ወቅት የጎሳ መሪውን እና ልማዱን በሚያዋርድ መልኩ ካልሞተ በቀር ከክንዱ የማይወልቀውን ከዝሆን ጥርስ እና ከአውራሪስ ቀንድ የተሠራ የቃልኪዳን አምባር ፖሊሶች መሰባበራቸውን በምሬት ነግረውኛል።

ክሱ ምን ይላል?

የታሰሩት ሰዎች ከ400 በላይ ቢሆኑም ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉት ግን የተወሰኑት ብቻ እንደሆኑ ተነግሮኛል። ፍርድ ቤት ከሚቀርቡት ታሳሪዎች መካከል የነካላ ገዛኸኝ መዝገብ (እዚህ ሙሉውን ማየት ይቻላል) ላይ እንደሚነበበው ከሆነ ክሱ የፖለቲካ ነው። "የወረዳው ሕዝብ በመንግሥት ላይ በአመፅና በአድማ ካልተሰለፈ ይህ ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ ምላሽ አያገኝም" በማለት ቅስቀሳ አድርገዋል በሚል ታስረው እስካሁን ፍርድ አላገኙም። እንደሌሎች ፖለቲካ እስረኞችም ክሳቸው አልተቋረጠላቸውም። አሁን ቀጣዩ ቀጠሯቸው በመጪው ሰኞ ሰኔ 18/2010 ነው። 

ለምን አልተፈቱም?

የኮንሶ እስረኞች ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተቃውሟቸው ምክንያት ተለቃቅመው እንደታሰሩት ዜጎች ሁሉ የፖለቲካ እስረኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ከኮንሶ እስረኞች መካከል እስካሁን አንድም ሰው አልተፈታም። በዚህም "እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ?" የሚል ቁጭት ተሰምቷቸዋል። ከ350 ሺሕ በላይ ነዋሪ ባላቸው 42 የኮንሶ ቀበሌዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች ይህንን አቤት ለማለት ተሰብስበው አኔቱታዎቻቸውን ለክልሉ መንግሥትም፣ ለፌዴራሉ መንግሥትም አቅርበው ነበር። ይሁን እንጂ ማንም መልስ አልሰጣቸውም። ይልቁንም አሁንም በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እየተዋከቡ ነው። ከሽማግሌዎቹ መካከል አንድ ሰው ባለፈው ሳምንት ሲታሰር ሌሎችም ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው። 

አሁን ዜጎች የፀጥታ ኃይሎች ማዋከብ በመቅረቱ መፍራት ባቆሙበት ሰዐት፣ የኮንሶ ሰዎች ግን አሁንም ከእስር ስጋት ጋር ተፋጥጠዋል። ይህንን እጅግ በጣም አሳጥሬ የጻፍኩትን መረጃ የሰጡኝ ሰዎች ሥማቸውን መጥቀስ ይፈቅዱልኝ እንደሆነ ስጠይቃቸው፣ "እኛ አካባቢ ያለው ሁኔታ እንደ አዲስ አበባ አይደለም። ለኛ ጥሩ አይደለም" ብለውኛል። 

ለኮንሶ ብሔረሰብ ዜጎቻችን የሚደርስላቸው ማን ይሆን? [እባካችሁ ይህንን መረጃ እንዲሰራጭ በማገዝ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ የኮንሶ ዜጎቻችንን ከእስር እንዲፈታ የበኩሎን አስተዋፅዖ ያድርጉ።]

1 comment:

  1. The horrendous misery that Ethiopians are experiencing in Konso as elsewhere is the work of traitor Tigres and their prisoners of war who have colluded with the enemy to impose a divisive constitution,

    This, so called federal constitution be be shredded, its authors tried and a new constitution that has the approval of the nation should be drafted.

    ReplyDelete