Skip to main content

“…ማን አለ እንዳንተ፣ ታማኝ?”



የሆነ ጊዜ የሰማኋት ቀልድ ትዝ አለችኝ፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ተወካዮች ፓርላማ ውስጥ በነበሩበት በዚያ በደጉ ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ ተወካይ የሻዕቢያ መንግሥት ላይ ሊደረግ ስለሚገባው እርምጃ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ “አሁኑኑ ገብተን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለብን፡፡ አለበለዚያ ካደሩ አይቆረጠሙም፤ እነዚያ ወያኔዎችም ያኔ ሲመሠረቱ ሳንጨፈልቃቸው ዝም ብለናቸው ነው ዛሬ አናታችን ላይ…” አሉና ያሉበት ቦታ ትዝ ሲላቸው ድንግጥ ብለው ወደአቶ መለስ መቀመጫ አማተሩ፡፡ አቶ መለስ በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ተወካዩ እንደደነገጡ “…ልጨርሰው ወይስ ትጨርሰኛለህ?” አሉ ይባላል፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወታደሮች አዲስ አበባ ደርሰው “ሲቪል” መንግሥት ከመመሥረታቸው አስቀድሞ “እኩይ” ናቸው በሚል ሲቃወማቸው የነበረ እና እስካሁንም ስክነቱ ያልተለየው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ነው፡፡ የታማኝ የአክቲቪስትነት ሪከርድ ከኮሜዲያንነቱ የሚመዘዝ ነው፡፡ በቀልዶቹ ቢጀምርም አሁን ግን በጣም ‹ሲሪዬስ› ነው፡፡ አሁን እነቪኦኤ፣ ዶቸ ቬሊ፣ ኢሳት በየቤቱ እንደሚደመጡት ከደርግ ማክተሚያ ቀደም ብሎ ብዙ ሰው በየቤቱ ‹ድምፂ ወያነ›ን በድብቅ ያደምጥ ነበር፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች አመል ነውና ያው ውሸታቸው አይጣል ነው፡፡ ታዲያ ታማኝ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቀርቦ የምሩን ሲቀልድ ‹እዚህ ቦታ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር፣ እዚያ ቦታ ደግሞ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር ደመሰስን ይላሉ፡፡ ሲደመር ግን ይሄን ያክላል፡፡ ቆይ እኔ የምለው ወያኔዎቹ የሚደመስሱት ጦር ከጠቅላላ ጦሩ በለጠ እኮ፤ ከየት እያመጡ ነው የሚደመስሱት?› ዓይነት ቀልድ ተናግሮ አላገጠባቸው፡፡ ከዚያ በድምፂ ወያነ መልስ ተሰጠው፤ “ቁጥሩን አዲስ አበባ ስንደርስ እናወራርዳለን” የሚል፡፡ ዛቻ የሽፍትነት ዘመንም አመል ነበረች፡፡

ግንቦት 20/1983 - ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲረግጥ፣ ሲ ኤን ኤን ካነጋገራቸው ሰዎች አንዱ ታማኝ በየነ ነበር፡፡ “በመሣሪያ ተከበናል፣ ምንም ሠላም የለም…” የሚል ነገር ለጋዜጠኛው ሲነግረው ይታያል፡፡ ታዲያ ታማኝ ሁኔታውን በቀልድ ሲያስታውስ “ጓደኞቼ ከውጪ ደውለው ‹ሲ ኤን ኤን› ላይ አየንህ ሲሉኝ፣ ወዲያውኑ እንግሊዝኛዬ እንዴት ነበር?” አልኳቸው ይላል፡፡

ታማኝ ከአዲሱ ስርዓት ጋር አብሮ መኖር በማይችልበት ሁኔታ የተቀያየመው፣ ካልተሳሳትኩ የወቅቱ ባለሥልጣናት፣ እነታምራት ላይኔ በተገኙበት ስታዲዬም ውስጥ በቀለደው ቀልድ ነው፡፡ እንደማስታውሰው ቀልዱ በማንነት ላይ የተመሠረተ እና ለኢሕአዴግ የማንነት ብያኔ የማይበገር ዓይነት ቀልድ ነው፡፡

ፍቃዱ ማሕተመወርቅ፣ የቀድሞዋ ዕንቁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበር፡፡ በመጽሔትና ጋዜጦች አከፋፋይነትም ይታወቃል፡፡ አሁን መጽሔቱ ተዘግቶ “በታክስ ስም” ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ይገኛል፡፡ ፍቃዱ ነጻው ፕሬስ ሲጀመር ጀምሮ ምኅዳሩን ያውቀዋል፤ እናም “እናንተ በደጉ ጊዜ ነው የመጣችሁት” እያለ ይቀልድብኛል፡፡ ያኔ (ማለትም የመጀመሪያው አንቀጼ ላይ ‹ደግ› ባልኩት፣  ለፍቃዱ ግን ‹ክፉ› ግዜ) አንድ ሰው ስርዓቱን የሚያስቀይም ንግግር ሲናገር፣ እንዳሁኑ በሕግ ሥም ፍርድ ቤት አይመላለስም፣ የደረሰበት ይጠፋና ከአራት አምስት ወር በኋላ ተመልሶ ይመጣል፡፡ እንዳይሞት እንዳይሽር ተቀጥቅጦ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ያሻሻልነው ነገር ቢኖር ፍርድ ቤት የመቅረብ ዕድል መፈጠሩ ነው ማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ያነሳሁት ታማኝ ላይ የደረሰውም እንዲህ ያለው ነገር ነው ለማለት ነው፡፡

ታማኝ ተሰደደ፡፡ ብዙዎች ሲሰደዱ አቅላቸውን ያጣሉ፡፡ የሀገር ቤት ናፍቆት መመለስ ካለመቻሉ ጋር ተደማምሮ ይሁን፣ የሄዱበት አገር ኢሕአዴግ የማይደርስባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያዩት ነጻነት ስለሚያስቀናቸው አላውቅም ብቻ ጠርዝ ይይዛሉ፡፡ ጥቂቶች ብቻ ሚዛናቸውን በጥፍራቸው ቆንጥጠው ይቆማሉ፡፡ ታማኝ ለኔ ከጥቂቶቹ አንዱ ነው፤ ያውም በረዥም ቆይታ ይህንን ማስመስከር የቻለ፡፡ ታማኝ አሁን አክቲቪዝሙን የሚሠራው ብዙ ጊዜ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እያቀረበ ነው፡፡ ቪዲዮዎቹን ዩቱዩብ ላይ ሳያቸው በክምችቱ እቀናለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ የአገር ቤት ጉዳይን እየተከታተሉ፣ ማስረጃዎችን እየሰበሰቡ የመቆየት ፅናት የገቡበትን ጉዳይ ርዝመት እና ክብደት ከመረዳት ይመነጫል፡፡

የማስረጃ ነገር ከተነሳ አይቀር፣ አሁን እነ ታማኝ ማስረጃ ዶት ኮም (masreja.com) የተባለ ድረአምባ ፈጥረዋል፡፡ ድረአምባው በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የበላይነት ፈንታ ራሳቸው ከሕግ የበላይ ሆነው ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ማስረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኔ በይቅርታ አምናለሁ፤ እስከዛሬ አዲሱ ያለፈውን እየቀጣ የመጣበት ዑደት ቢያንስ የእኛ ትውልድ ላይ ቢቆም እያልኩ እመኛለሁ፡፡

ይህንን በተመለከተ ጓደኛዬ ሶሊያና “ይቅርታ ከፍትሕ ጋር መጋጨት የለበትም” ብላ ሞግታኛለች፡፡ ልክ ነች፤ በወቅቱ የሰጠችኝን ምሳሌ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር አዋህጄ ልናገር፤ “#OromoProtests ላይ ልጇ የተገደለባት እናት የስርዓት ለውጥ ቢመጣ እና ለገዳዩ ወታደር ይቅርታ አድርጊለት ብትባል ፍትሕ ተደረገልኝ ብላ ታምናለች?” በወቅቱ፣ ሶሊም እኔም ጥያቄውን ከመጠየቅ በቀር መልስ መስጠት አልቻልንም፡፡ እርግጥ ነው ልጁ የሞተው የመጣው ለውጥ እንዲመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በምሳሌያችን መሠረት አወዛጋቢው ማስተር ፕላን ቢሰረዝ እንኳን ልጁ የለውጡ እሸት ተጋሪ ላይሆን አልፏል፡፡ ይቅርታ ለአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያስፈልግ ይሆናል፤ የቤተሰቡን አባል ወይም ወዳጁን ላጣው ግለሰብ ግን ፍትሕ ሆኖ ይሰማዋል ማለት አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ለይቅርታውም ቢሆን ማስረጃውን መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ አጥፊው ጥፋቱን እንዳይክድ፣ ይቅርታ ጠይቁኝ ባዩም በማስረጃ እንዲሞግት፡፡

ማስረጃ መሰብሰብ ሕገ-ወጥ መስሏችሁ የምትፈሩ ካላችሁ አትሳሳቱ፡፡ ሕጋዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ራሱ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል አላግባብ የተገኘ ሀብት ካለ በሚል የባለሥልጣናቱን ሀብት ምንጭ ሳይቀር የማጣራት ማንዴት አለው፡፡ ቁርጠኝነቱ ስለሌለ አልተሳካላቸውም፤ እኛ ግን ይሳካልናል፡፡ በየቀኑ ከታችኛው እርከን (ወረዳ) እስከ ላይ ድረስ የምንጠየቃቸውን ጉቦዎች፣ ባለሀብቱና ባለሥልጣናቱ (ሁለቱም አንድ ናቸው) ኢ-ርትዓዊ በሆነ መንገድ የሚያካብቱትን ሀብት፤ ከትላልቆቹ እስከ ትናንሾቹ ሹመኞች በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ፤ ትንንሽሽም፣ ትልልቅም ሠላማዊ ተቃውሞዎች በተነሱ ቁጥር በንፁሐን ዜጎች ነፍስ ላይ የሚሰነዘሩትን የኃይል እርምጃዎች የሚያጋልጡ ማስረጃዎች ባገኘን ቁጥር ለማስረጃ ዶት ኮም በመላክ ለኢትዮጵያችን የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታ ሲባል እንዲከማቹ የበኩላችንን እናድርግ፡፡ ማስረጃዎቹን መሰብሰቡ ሌላው ቢቀር አጥፊዎቹን ስለሚያስፈራቸው በደላቸውን ሊያላሉልን ይችላሉ፡፡

ቪቫ ላ ታማኝ!!!

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...