Pages

Thursday, November 8, 2012

የአዲስ አበባ ከተማ እና ምርጫዋ

From Addis Ababa, Ethiopia

አዲስ አበባ 125ኛ ዓመቷን እያከበረች ነው፡፡ በከተማይቱ ልደት ሰሞን እናትና አባቷ (በመናገሻ ከተማነት የቆረቆሯት አጤ ምኒልክ እና ስሟን ያወጡለት እቴጌ ጣይቱ) ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም ላለፉት 21 ዓመታት በፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ መሪነታቸው በእጅ አዙር የዘወሯት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ እና በየመንገዱ ዳር በቆሙ ‹ቢልቦርዶች› ላይ ከከተማይቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ፎቶ ፊት ለፊት በጉልህ በተቀመጡ ምስሎቻቸው ታጅቦ ታይቷል፡፡

የክብረ በዓሉን ክንውን እንዲያዘጋጅ የኢሕአዴግ ሰዎች የሚመሯቸው ዋልታ እና ፋና ጥምር-ድቅል የሆነው ዋፋ የማስታወቂያ ድርጅት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ምናልባትም የዚሁ የፓርቲ ጥገኝነት ጉዳይ ይሆናል መለስን በግምባር ቀደምነት የከተማይቱን ቆርቋሪ አስዘንግቶ ያስጠቀሳቸው፡፡

ለነገሩ ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት ያነሳሳኝ የክብረ በዓሉን ዐብይ-ሰብ (figure) ለመሰየም አይደለም፡፡ ስለከተማይቱ እያነሳሁ ይህንን ያፈጠጠ ስህተት ሳልነቅስ ማለፍ ስላልሆነልኝ ነው፡፡ የጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ሚያዝያ ወር ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ከሀገር አቀፍ ምርጫ በሁለት ዓመት እንዲዘገይ የሆነው፣ በምርጫ 97 ከአንድ ወንበር በስተቀር ሁሉንም የከተማዋን ምክር ቤት መቀመጫዎች አሸንፎ የነበረው ቅንጅት ምክር ቤቱ ለመግባት ባለመፍቀዱ  ማሟያ ምርጫ እስኪካሄድ በተፈጠረው መዘግየት ሳቢያ ነው፡፡

ሀገሪቱ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በላይ ባላየችባቸው ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ አዲስ አበባ አምስት ከንቲባዎችን ለማየት ታድላለች፡፡ አንዴ ግዜያዊ የባለአደራ ከንቲባ ስታስተናግድ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹ተበለሻሸች›› ተብሎ - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በሚፈቅደው መሠረት - ምክር ቤቷ ፈርሶ በድጋሚ እንዲገነባ ተደርጎ ነበር፡፡ በነዚህ ጊዜያት ከተሠሩ ሕንፃዎች እና መንገዶች በተጨማሪ በተለይ ሕዝቡን ያማከለ ሥራ የሠሩት አርከበ ናቸው፡፡ አርከበ የኮንዶሚኒዬም ቤቶችን እና አርከበ ሱቆች ተብሎ በማኅበረሰቡ የተሰየሙላቸውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ቤቶች ያስጀመሩ ከንቲባ ናቸው፡፡

በዐሥር ክፍለከተሞችና ከ100 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች (አሁን ወረዳዎች) የተከፋፈለችው አዲስ አበባ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች እየዋሉ እንደሚያድሩባት ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው ከ3 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ለምርጫ ብቁ የሆኑት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን የሚጠጉት ብቻ ናቸው፡፡

በምርጫው ማን ይሳተፋል?

በሀገር አቀፉ ምርጫ 2002 የተሳተፉት/የመረጡት አዲስ አበቤዎች ብዛት ከ50 በመቶ እምብዛም የተሻገረ አልነበረም፡፡ በድኅረ ምርጫ 97 የተቀየመው ተቃዋሚ ሕዝብ ውስጥ ብዙኃኑ ለምርጫ ባለመመዝገብ፣ ወይም ከተመዘገበ በኋላ ባለመምረጥ እና የምርጫ ወረቀቱ ላይ ቅያሜውን ጽፎ ወረቀቱን በማበላሸት ተቃውሞውን መግለጽ መርጧል፡፡ በሌላ በኩል የነርሱ ድምፅ ለውጥ እንደማያመጣ በማመን ባለመምረጥ ዕድላቸውን የሚያባክኑትም ሰዎች ቁጥር እልፍ ነው፡፡

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ስለዚህ ዓመቱ የከተማ ምክር ቤት ምርጫ መገመት የምንችለው ተቃዋሚዎችን ከሚደግፈው ኅብረተሰብ ይልቅ ገዢውን የሚደግፉት የሊግ እና የፓርቲው አባላት በምርጫ ተሳትፎ ጎልተው ይታያሉ፡፡ ለዚህ ችግር የፖለቲካ ምኅዳሩን ካጠበበው ኢሕአዴግ እኩል አባላት ምልመላ እና ማኅበራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ (civic participation) እንዲያድግ ሲሠሩ ብዙም የማይስተዋሉት ተቃዋሚዎች ተወቃሾች ናቸው፡፡

በፓርቲዎች በኩል የገዢው ፓርቲ ተሳታፊነት ላይ ጥያቄ የማይኖር ሲሆን፣ እንዳለፈው የከተማይቱ ምክር ቤት ምርጫ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ያሸንፋል ወይስ ተቃዋሚዎች ያጅቡታል የሚለው ጥያቄ ይከተላል፡፡

የምርጫ ቦርድ የምርጫውን 21 ክንውኖች ለማርቀቅ ከ75 ፓርቲዎች ጋር እንደተመካከረ መናገር፣ ተቃዋሚዎች በዚህ ምርጫ እንደሚሳተፉ አንድ አመላካች ነው፡፡ ትልቁ የተቃዋሚዎች ስብስብ ግንባር የሆነው መድረክን ጨምሮ 34 ፓርቲዎችም ተሰባስበው እየመከሩ መሆኑ ተቃዋሚዎች ለተሳትፎ መዘጋጀታቸውን ሌላው አመላካች ነው፡፡

ለምክር የተሰባሰቡት ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር በሚፈልጉባቸው ነጥቦች ዙሪያ አብረው እየሠሩ መሆኑን መናገራቸውም ኢሕአዴግ መድረክን በሚወቅስበት ቋንቋ የምርጫ ሥነ ምግባሩን ሰነድ ካልፈረሙ አልደራደርም ብሎ ድርቅ ካለ - ምርጫው የተቃዋሚ ድርቅ ይመታው ይሆናል የሚል ስጋት እየገባኝ ነው፡፡

በዚህ ስጋት ዙሪያ (በግል መገናኛ ብዙኃን) ተጠይቀው መልስ የሰጡት የመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ሰዎች ሲሆኑ ሁለቱም በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ነገር ግን ‹‹ለአጃቢነት›› ብቻ ሳይሆን ለተወዳዳሪነት የሚያበቃ ምኅዳር መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በግሌ ኢሕአዴግ በዚህ ወቅት ምኅዳሩን ከዚህ በላይ ሊያሰፋ ይችላል ብሎ የሚያስጠብቅ ምንም ተስፋ አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በቃላቸው ከፀኑ በመጨረሻ ሰዐትም ቢሆን ውድድሩን ረግጠው በመውጣት ኢሕአዴግ ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን ያሸነፈበትን ያለፈውን የከተማ ምክር ቤት ምርጫ ታሪክ እንዲደግም ያደርጉታል የሚለው ስጋቴ አይሏል፡፡

ምርጫውን ማን ያሸንፋል?

ተቃዋሚዎች ባለው ምኅዳር ተወዳድረን ዕድላችንን እንሞክራለን የሚሉ ቢሆን እንኳን የበጀት እጥረታቸው በቂ ቅስቀሳ ከማድረግ ስለሚገድባቸው - አንድ፣ የኢሕአዴግ ቤት ለቤት ቅስቀሳ /በነገራችን ላይ የቤት ለቤት ቅስቀሳው በ‹‹ገለልተኛ›› ምርጫ አስፈፃሚዎች አማካይነት ‹‹ነዋሪዎች የፈለጉትን እንዲመርጡ ብቻ›› የሚቀሰቅሱ ቢሆኑም ነዋሪዎች ሰዎቹን (ቀስቃሾቹን) በኢሕአዴግ-ዘመም እንቅስቃሴያቸው ስለሚያውቋቸው የኢሕአዴግ ቤት ለቤት ቅስቀሳ እንደሆነ ነው የሚቆጥሩት - እናም በቤት ለቤት ቅስቀሳው/ እና የአንድ ለአምስት ጠርናፊ እና አስጠርናፊ ስትራቴጂዎች ኢሕአዴግ የመራጮችን ልብ አንድም በፍርሐት አሊያም በፕሮፓጋንዳ ብዛት ስለሚሸንፍ - ሁለት ምክንያቶች የአሸናፊነቱን ነገር /ከግማሽ በላይ መቀመጫ ወንበሮችን የማግኘቱ ነገር/ ከኢሕአዴግ ውጪ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ሁለት ጉዳዮች ለተቃዋሚዎች እስከመጨረሻው ድረስ እንዲታገሉ ምክንያት ይሆኗቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት አዲስ አበቤዎች በኢሕአዴግ ላይ ያላቸው ቅያሜ ጥልቀት ነው፡፡ የቅያሜው ምንጭ ከተለያዩ ፖለቲካዊ አፈናዎች እስከ ኑሮ ውድነት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የኑሮ ውድነት በከተማዎች ውስጥ የገነነ እንደሆነ ኢሕአዴግም ሳይቀር ያምናል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ በአብዛኘው በቅጥር የሚተዳደር ደሞዝተኛ መሆኑ ደግሞ ወር ጠብቆ የሚያገኛት ምንዳ ከኑሮ ውድነት የመረረውን ገፈት እንዲቀምስ አስገድዶታል፡፡ በዚያ ላይ በስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2004 ሪፖርት ላይ እንደታየው ከ25 በመቶ በላይ ሥራ አጦች በመኖራቸው ሩብ ያክሉ የከተማ ሕዝብ በአየር ላይ እንዲንሳፈፍ ተገዷል፡፡ ይህ ምሬት የሚወልዳቸው ነዋሪዎች በኢሕአዴግ መማረራቸው ብቻ ተቃዋሚዎችን ባያውቋቸውም ወይም ባያምኗቸውም እንዲመርጧቸው እና ኢሕአዴግን በምርጫ ካርድ እንዲቀጡት ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ምሬቱ ቢኖርም ምርጫው ይጭበረበራል የሚለውን ስጋት የሚሽር ነው፡፡ በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የበላይ ታዛቢነት የሚካሄድ ምርጫ መሆኑን የሚጠቅሱት ተስፈኞች ምንም እንኳን የፖለቲከኝነታቸውን ድርሻ ያገናዘበ ባይመስልም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሃይማኖተኛ መሆናቸው በይፋ መነገሩ በማጭበርበር ድርጊቶች ላይ ሀገር አቀፍ መሻሽል እንዲጠብቁ ብዙዎችን አስገድዷል፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር መኖሩ ብቻውንም ቢሆን የተሻለ ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚካሄድና እንደማይካሄድ ለማወቅ እስከመጨረሻው በመሳተፍ መሞከር የግድ ያስፈልጋል፡፡

ውጤቱ ምን ያመጣል?

እስካሁን ባለው አያያዝ /ተቃዋሚዎች አስማታዊ ጥበብ ተጠቅመው መነቃቃት ካልፈጠሩ በቀር/ አብዛኛዎቹ ወንበሮች ወደኢሕአዴግ እንደሚሄዱ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ምርጫው በፍትሐዊ መንገድ ተካሂዶ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች የምክር ቤት ወንበር ካገኙ ብዙ የተቆረጡ ተስፋዎች መልሰው ይቀጠላሉ፡፡

ለምሳሌ፣ ለ2007ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ አዲስ መነቃቃት ይፈጠራል፣ በተጨማሪም አዲስ አበባ በፖለቲካዊ ሚና እና በኢኮኖሚያዊ አቅሟ የስበት ማዕከል (center of gravity) እንደመሆኗ በከተማይቱ የሚመጣው ለውጥ በሀገሪቱ ለውጥ ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ አገሪቱ በኢሕአዴግ አፍላ የሥልጣን ዘመናት አይታ የነበረውን ዓይነት የዴሞክራሲ ጭላንጭል ዳግም ማየት ትችል ይሆናል፡፡

ነገር ግን ያልተጠበቀው ሆኖ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን በጥምረትም ቢሆን ቢያሸንፉ፣ ያለምንም ጥርጥር ምርጫ 2007 በተቃዋሚዎች የበላይነት ሊጠናቀቅ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጪው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጋር መስማማት ካልቻሉ ስልጣናቸውን እና ደጋፊያቸው የሆነውን የተወካዮች ምክርቤት ተጠቅመው አፈራርሰውት ሌላ ምርጫ ሊያካሂዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን አሳሳቢ አይደለም፣ ምክንያቱም የማይሆነው ከሆነ በኋላ የሚታሰብበት ጉዳይ ነውና!

አሁን ወደነባራዊው እውነታ እንመለስና ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ተወዳዳሪ እጩዎችን ሲያቀርቡ ሊያስቡበት የሚገባውን ትልቅ ቁም ነገር እናንሳ - አዲስ አበቤዎችን መመልመል፡፡ አዲስ አበባ ወልዳ ባሳደገቻቸው ልጆቿ መመራት አለባት ብዬ አምናለሁ፤ ከኔ ጎን የሚቆሙ ሌሎችም በርካቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ፓርቲዎች እጩዎቻቸው የአዲስ አበባን ነገረ ሁኔታ በቅጡ የሚረዱ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ያደጉ (ወይም ለበርካታ ዓመታት የኖሩባትን) ዕጩዎች እንዲመለምሉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

ጽሑፌን ከመደምደሜ በፊት የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መቀመጫ እና የ19 ዓለም አገራት ከተሞች እህት ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ - ብዙ ማዕረግ ይገባታል፡፡ እነዚህን ወግ ማዕረጎች ለማየት ከጉያዋ የወጡ፣ የሚቆረቆሩላት፣ ለውጥ ሊያመጡ የሚፈልጉ እና የሚችሉ አስተዳዳሪዎች ለመምረጥ ፍትሐዊ ዕድል ሊሰጣት እና እርሷም ልትጠቀምበት ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment