Pages

Tuesday, January 17, 2012

የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ

From Addis Ababa, Ethiopia
ፈረንጅ የሚለው ቃል÷foreign ከሚለው እንግሊዝኛ ቃል የመጣ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም አባቶቻችን foreign የሚለውን እንግሊዝኛ ፈረንጅ ብለው ሳያነቡት አይቀርም፡፡ በዚህ ዓይነት ፈረንጅ ማለት ኢትዮጵያዊ ያልሆነን ሰው ይወክላል ማለት ነው፡፡ እኔ ግን በርዕሴ ፈረንጅ ብዬ የጠቀስኩት ነጮችን መሆኑን ተገንዘቡልኝ፡፡

የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ መኖሩን ሳናውቅ ስር ሰዶ ከርሟል፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ቅርጫፉን የዘረጋው አሁን ቢሆንም÷ ከጥንት የተጀመረ አምልኮ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናትን በመመርመር መረዳት ይቻላል፡፡

የፈረንጅ አምልኮ ድሮ
የፈረንጅ አምልኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣባን ክርስትና እና እስልምና ወደኢትዮጵያ በገቡበት ዘመን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይሄ ብዙዎችን የሚያናድድ አስተሳሰብ ቢሆንም÷ እኔን ግን ከማሳመን አላለፈም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል እምነቶችንና ስልጣኔዎችን ደምስሰው ባዕዳን ሃይማኖቶችንና ስልጣኔዎችን የተቀበሉት በነዚያ ጊዜያት ነው፡፡

የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ዱካ ሳይተው የኮበለለበት ምስጢር ከዚህ የባዕድ ስልጣኔ ወረራ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ እንደመላምት የምጠቅሰው÷ ክርስትያናዊ፣ አይሁዳዊ (ዮዲት) እና እስላማዊ (ግራኝ መሐመድን) የመሳሰሉ ኃያላን ግዛታቸውንና እምነታቸውን ለማስፋፋት ሲንቀሳቀሱ የቀድሞውንና የተቃራኒውን እምነት ከነስልጣኔው የመደምሰስ ስልት ይጠቀሙ የነበረ መሆኑን በማስታወስ ነው፡፡ እንግዲህ በ4ኛው ክፍለዘመን ክርስትና ከመግባቱ በፊት የነበረውን ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ በመደምሰሱ መጠ’የቅ የሚኖርበት ክርስትና ነው ለማለት እንችላለን፡፡

በቅርብ ጊዜ ተመዝግበው ከተቀመጡ የታሪክ ድርሳናት መካከል የምወዳቸው አጤ ምኒልክ (ዳግማዊ) ራሳቸው የዚህ አምልኮ ሰለባ ሊሆኑ እየዳዳቸው እንደነበር የጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› ያሰፈራት ንግግር ትነግረናለች፡፡ በርግጥ እምዬ ምኒልክ ከኛ ትውልድ በተሻለ የፈረንጆችን የሥራ ችሎታ እንደሚያደንቁ እንጂ እንደማያመልኩ ንግግራቸው ይናገራል፡፡ ሚያዝያ 1፤ 1889 የሲኒማ ‹ፕሮጀክተር› አስመጥተው ከመኳንንቶቻቸውጋ የኢየሱስን ታሪክ በፊልም በተመለከቱ ጊዜ÷ ‹‹…እነኚህ ፈረንጆች እኮ የማይሠሩት ነገር የለም፡፡ ሁሉንም ነገር ሲሰሩ የሰው ነፍስ ብቻ መሥራት አልቻሉም፡፡›› ብለው ተናገሩ፡፡ (ገጽ 337)

እዚህ አካባቢ ሙግቴ ተጣምሞ ጠንካራ ሠራተኝነትን ማድነቅ እያወገዝኩ ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ እኔ እያወገዝኩ ያለሁት ጠንካራ ሠራተኝነትን ከፈረንጅነትጋ ተቃራኒውን ደግሞ ከኛጋ ማቆራኘቱን መሆኑን ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ እኒህ አባባሎችና አስተሳሰቦች ተጠራቅመው በዘመናችን ሰዎች ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ ቀጥለን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የፈረንጅ አምልኮ ዘንድሮ
በዚህ ዘመን ደግሞ ምንም ይሁን ምን የፈረንጅ ከሆነ ጥሩ ነው፤ እንዲያውም ጥሩ ከሆነ የፈረንጅ ነው፡፡ የፈረንጅ ዶሮ፣ የፈረንጅ ቀጠሮ፣ የፈረንጅ ላም፣ የፈረንጅ ጥድ፣ የፈረንጅ ዳቦ፤ ሁሉም ከ‹ሐበሻ› ተብዬዎቹ ‹‹የተሻሉ›› ናቸው ስለተባለ ነው ስያሜውም የተሰጣቸው፡፡ በርግጥ የፈረንጅ ተመራማሪዎች በማዳቀልም ይሁን በተሻሻለ አሠራር ያመረቷቸውን ነገሮች ማሞካሸት ነውር የለውም፡፡ ችገሩ፣ ቃላቶቻችን ጥሩ ነገርን መሥራት የሚችሉ ወይም ጥሩ ነገሮች በሙሉ የፈረንጅ ናቸው የሚል አንድምታ ያላቸው መሆኑ ላይ ነው፡፡ የኔ ፍራቻ በሃገራችን ተዳቅሎ የተመረተው ‹‹ቁንጮ ጤፍ››÷ ‹‹የፈረንጅ ጤፍ›› ሲባል ላለመስማት ነው - እስካሁን ካልተባለ!

የዚህ ዘመን የፈረንጅ አምልኮ ብዙ መልክ አለው፡፡ የአንድን ነገር ትልቅነት ለማመልከት የፈረንጅ ቅባት መቀባት አስፈላጊ ይመስላል፡፡ ትምህርት ቤቱ ፈረንጆች ናቸው የሚያስተምሩበት፣ ፕሮጀክቱን ፈረንጆች ናቸው ያጠኑት፣ ፖሊሲውን ፈረንጆች ይጠቀሙበታል፣ ባሏ ፈረንጅ ነው፣ ከፈረንጅ አገር ነው የመጣው እና ወዘተርፈ፡፡

ፈረንጅ እያልን የምንጠራቸው ማሕበረሰቦች በርግጥም ‹‹በዘመናዊነት እና በስልጣኔ ስለሚበልጡን›› ከነርሱ መማር እና አርአያነታቸውን መከተሉ ጉዳት የለውም፡፡ ጉዳት የሚኖረው እነሱ ከኔ የተሻሉ ናቸው፤ ለችግሮቼ መፍትሄ ማበጀት የሚችሉትም እነሱ ናቸው የሚል የጥገኝነትና የአምልኮ መደምደሚያ ላይ መድረስ ነው፡፡ የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ ይባላልና ለእኛ እድገትና ዘመነኝነት ከእኛ በስተቀር ሞክሮ የሚሳካለት አይኖርም፡፡

በርግጥ ሌላም የማይካድ ሐቅ አለ፡፡ ፈረንጆች ከጥቁሮች ይልቅ ውጤታማ እና ‹ኢንተሊጀንስ ኮሸንታቸውም› ከፍ ያለ እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ብዙዎቹ ይሄንን ከዘረኝነት ነጥለው አያዩትም፡፡ ለኔ ግን የሚያስደንቅ ግኝት አይደለም፡፡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ፈረንጆች ከጥቁሮች የበለጠ የትምህርትና የተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ አላቸው፡፡ ‹ኢንተሊጀንስ ኮሸንት› ከተፈጥሮ ባሻገር÷ የቀለም ትምህርት የሚያጎለብተው ጉዳይ መሆኑን ከመናገር የበለጠ ይኼ የተለየ ትርጉም የሌለው መሆኑን መረዳት ግድ ይላል፡፡

ነገር ግን በፈረንጅ የስልጣኔ ደረጃ እና ፍላጎት ላይ ተመስርተው የሚነደፉትም ሆነ የሚቀየሱት ጥብቆና ጎጆዎች ማንፀባረቅ የሚችሉትም ሆነ የሚስማሙት ለራሳቸው ለፈረንጆቹ ብቻ እንደሆነ ሊዘነጋ የማይገባው እውነታ ነው፡፡

ስልጣኔ አንድ መስመር ይዞ የሚጓዝ፣ አንድ ትርጉም ያለው የሒሳብ ቀመር አይደለም፡፡ ሕዝቦች በእሴቶቻቸው እና በማሕበራዊ ማንነታቸው ላይ ተመስርተው የሚያበጁት በየዘመኑ የሚዘምን የአስተሳሰብና የአተገባበር ዘዬ ነው፡፡

የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት
‹‹ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተደፈረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ናት፤›› የሚለው ነጠላ ዜማችን ነው፡፡ ነጠላ ዜማዎች ከአልበሙ ይዘት አፈንግጠው የተሻሉ ቢሆኑ አልበሙ ላይ የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም፡፡ በግሌ ‹‹ፈረንጅን እግዚአብሔር ፅድ’ት አድርጎ የፈጠረው ፍጡር ነው›› የሚሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገጥመውኛል፡፡ በርግጥም እያንዳንዳችን ራሳችንን ለመታዘብ የምንጥር ከሆነ ‹‹የፈረንጅ›› እና ‹‹የሐበሻ›› ነገሮችን የምናይበት ዓይን እኩል አይደለም፡፡ ስለዚህ በተዘዋዋሪ የነሱ ተገዢ ያውም አምላኪ መሆናችን ካልቀረ÷ ፀጥለጥ ብለን ተገዝተን ሙሉ ማንነታችንን ደምስሰው፣ ሙሉ ማንነታቸውን እና ሙሉ ስልጣኔያቸውን ቢያወርሱን ምንም አልነበረም፡፡ ቅኝ የመገዛትና ያለመገዛት ልዩነቱ ማንነትና እሴትን ጠብቆ ማኖር ነው ከተባለ ግን አሁን ከዚያ የበለጠ እየሸረሸርነው እንደሆነ መናገር አይከብድም፡፡

የፈረንጅ አምልኮ ጮክ ብለው የሚናገሩለት፣ የሚያኮራ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም ዘወትር የምናቀነቅነውን የሦስት ሺኅ ዓመት የነፃ ሕዝብ ፍካሬ መሬት አውርዶ ዘጭ የሚያደርግ ቅሌት ነው፡፡ ስለዚህ ይብቃ - ቻው፣ ቻው ሲኞሪታ!

ይቀጥላል:- የሐበሻ አምልኮ በኢትዮጵያ

4 comments:

  1. ፈረንጅ የሚለው ቃል French ከሚለው የመጣ ይመስለኝ ነበር፡፡
    ጽሑፉ ደስ ይላል፡፡ ፈረንጅን ስንከተል መኖራችን እኔንም ሆነ ሌሎችን ሲከነክን የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ መድሀኒቱ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ መድሀኒቱን ለማወቅ፤ ችግሩን ማወቅ አንድ እርምጃ ነው ብዬ በማሰብ አንተ ግን እንደ ችግሩ ምክንያት ያስቀመጥከው ነገር ገመገምኩት፡፡…እና ትንተናህ ብዙ አላሳመነኝም፡፡
    ፈረንጅ ማምለክ የኢትዬጵያ ብቻ ችግር፤ መነሻውም ክርስትና አድርገህ ማስቀመጥህ አኒክዶታል ወይም የተጋነነ ጄኔራላይዜሽን መሰለኝ፡፡ ለምን ብትለኝ ‹‹ፈረንጅን የሚያመልኩ›› ብዙ ሀገሮች እና ሕዝቦች በዙሪያችን አሉና፡፡ብዙዎቹ ክርስቲያን አይደሉም፡፡ ነገሩ የመላው አፍሪካ..የመላው አዳጊ እና ታዳጊ ሀገር ችግር ነው፡፡ ሕንድና ቻይና፤ ዓረቡ እና ላቲን አሜሪካው ፈረንጅ ለመምሰል ሲሽቀዳደሙ አላስተዋልክም፡፡ ከፈረንጆችም ውስጥ ደንበኛ ፈረንጅ ለመሆን የሚደረግ ጥረት አለ፡፡ ባለ ወርቃማ ጸጉር መሆን፤ ረጅም እና ፈርጣማ መሆን፤ ባለ ሰማያዊ ዓይን መሆን…ወዘተ፡፡ ጸጉሯን ብሎንድ ለማድረግ ሃይላት የማትቀባ ሴት ፈረንጅ ያለች እንዳትመስልህ፡፡ ነገሩ በእኛ ብሶ ታየ እንጂ፤ በሁሉም ቤት ያለ ግሎባል ችግር ነው ባይ ነኝ፡፡ መፍትሔውም ከእኛ በላይ የሆነ ግሎባል ይመስለኛል፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. ለነገሩ ፈረንጅ የሚለው ቃል÷ French ከሚለው ቃል ጋር በድምጽ በጣም እንደሚዛመዱ አስተውያለሁ፡፡ ይሄ ጽሁፍ ethiopianreview.com ላይ ተለጥፎ አይቼዋለሁ፤ እዚያም አንድ ሰው ይህንኑ በአስተያየቱ ጠቁሟል፡፡ እኔም በጽሁፉ ላይ መላምቴን ነው ያስቀመጥኩት፡፡
      እንዳልከው ፈረንጅን የሚያመልኩ ብዙ ሃገራት (ወይም ፈረንጆች) ሊኖሩ ይችላሉ፤ ቢሆንም የእኛ አገር የባዕድ (የፈረንጅ አምልኮ) ግን - ያው ስለውጪው ዓለም (ስለፈረንጆች) ማወቅ ከጀመርንበት ዘመን ይጀምራል ባይ ነኝ፡፡ በርግጥ ከዚያ በፊትም በንግድ እናውቃቸው ነበር፡፡ ቢሆንም በበላይነት ዘመን የምታውቃቸውን ሰዎች ከማምለክ (ወይም ለመምሰል ከመሞከር ይልቅ)፣ አምላክን ይዘው የአምላክ ቤተሰብ ሁነው የመጡ ሰዎችን ለመምሰል መሞከር ይቀላል፡፡ ለዚያ ነው ክርስትና ላይ ጣቴን የቀሰርኩት፡፡
      በነገርህ ላይ÷ ethiopianreview ላይም ብዙዎቹ አስተያየት የሰጡት ይቺን የክርስትናን ወደኢትዮጵያ መግባት ተከትሎ የመጣ የባዕድ አምልኮ ‹‹የምታብጠለጥል›› ሁለት አንቀጽ መሠረት አድርገው እንጂ በጥቅል የጽሁፉ ይዘት ውስጥ ለማስተላለፍ የሞከርኩት መልዕክት ላይ አይደለም፡፡ አንዴ፤ ገጠርነታቸው ካልለቀቃቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሄጄ ያየሁትን ‹‹ድሮ›› (አንተ በአንድ ጽሁፍህ እንደጠቀስከው በ‹ታይም ሜሽን› የተመለስኩ ነበር የመሰለኝ፤) እናም ያንን ‹‹ድሮ›› ተከትለን ብንመጣ የት እንደርስ እንደነበር (ወይም ማን እንሆን እንደነበር) የምጽፍ ይመስለኛል፡፡

      Delete
  2. ከገመቱ ምሁራዊ ግምት መገመት ነው አለበለዚያ የሰሙትን ብቻ መናገር ቀደም ብሎ የፈረንሳይ የእንግሊዝ ሰዎች ባማካሪነትና በሙያ ይገቡ ስለነበረ ከፍሬንች ፈረንጅ ተባለ ነበር በሰፊው የሚታወቀው ዛሬ ታዲያ foreign የሚል ቃል የሚያውቅ ተወለደና ጋለል ብሎ በኩራት ታሪክ ሊፈጠርልን ኤጭ።

    ReplyDelete
  3. Naod is right. ፈረንጅ የሚለው ቃል French ከሚለው የመጣ ነው::

    ReplyDelete