Pages

Thursday, April 2, 2020

የዐቢይ አሕመድኹለት ዓመታት!

ከወር በፊት፣ ከጓደኞቼ ጋር የሆነ ኮንሰርት ልንገባ በር ላይ ስንደርስ ከኛ የቀደሙት ትኬታቸውን ሊያስመልሱ ሲከራከሩ ደረስን። በር ላይ ያለው ሰውዬ ለማግባባት በማሰብ ትኬት ይመለስልን የሚሉትን ወጣቶች "የኛ የመጀመሪያው ኪሳራችን እናንተን ማስከፋታችን ነው" አለ። አንዱ ጎረምሳ ከአፉ ነጥቆ "ባክይ ዐቢይ አሕመድ አትሁንብኝ" ብሎ ሁላችንንም በሳቅ አፈረሰን።

እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ቅቤው" እያሉ ሲጠሯቸው እሰማለሁ፤ በአራዳ ልጆች አነጋገር "ፎጋሪው" እንደማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያረጋገጧቸው ነገሮች ቢኖሩ በንግግራቸው አባባይ መሆናቸውን ነው።

ንግግራቸው ታዲያ ብዙዎችን ያስደስት እንጂ፥ የኔ ቢጤዎችን ግን ብዙ ጊዜ ያበሽቃል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግሮች ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ፣ ከመንፈስ ማነቃቂያ መጽሐፍት ምክሮች እና ከሳይንሳ ለበስ ግምቶች አያልፉም። ዐቢይ ለጆሮ የማይረብጥ ነገር የሚያወሩት ስለ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲያወሩ ብቻ ነው ባይ ነኝ

"አዳኝም መንገድም"

ዐብይ አሕመድ የኖሩበት የፕሮቴስታንት ባሕል ሳይጫናቸው የቀረ አይመስለኝም፥ ችግሮችን ሁሉ በስብከት እና በምክር እንዲሁም በመተቃቀፍ መፍታት የሚቻል ይመስላቸዋል። ብዙ ንግግሮቻቸው በምክር የተሞሉ ናቸው። ብዙዎቹ መግለጫዎቻቸው እና ንግግሮቻቸው ውስጥ የአማካሪያቸው ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የረዥም ዓመታት የተረታ ተረት ዘይቤዎች ይስተዋላሉ። (አንድ ጊዜ "እየወጋች ምትጠቅመው መርፌ" መስለው ያወጡት መግለጫ ሥር "እናመሰግናለን ዳንኤል ክብረት" የሚል አስተያየት አይቼ እስከዛሬ ያስቀኛል።) ይህ ዘይቤ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ከሥነ ምግባር ጦት የመነጨ ነው ከሚል የሚመነጭ ስለሆነ፥ እንዲህ ብትሆኑ እና ብታደርጉ ኖሮ እንዲህ አትሆኑም የሚሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት መንግሥት የሥነ ምግባር አስተማሪ፣ መካሪ ወላጅ ወይም አሳዳጊ (paternalistic) ሚና ለራሱ ሰጥቷል። በዚህ አሠራር ሕዝብ ታዳጊና አጥፊ ሕፃን ነው ማለት ነው። ለዚህ ነው መንግሥት በቲቪ የምታዩትን ማስታወቂያ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የምታነቡትን መረጃ እኔ እመርጥላችኋለሁ ማለት እየቃጣው ያለው።