Pages

Sunday, January 29, 2012

አፍንጫ ሲመታ ዓይን አያለቅስም ወይ?

From Addis Ababa, Ethiopia

አንድ የቆየ ቀልድ አስታውሳለሁ፡፡ ኒው ዮርክ ውስጥ አንዲትን ሕፃን ልጅ ውሻ ሲያባርራት ያየ አንድ ሰው ውሻዋን በያዘው አጠገቡ ባገኘው ዱላ መትቶ ይገድልና ልጅቷን ያድናታል፡፡ ይህንን ይመለከት የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ወደሰውየው ይቀርብና ‹‹እሺ፤ ጀግናው አሜሪካዊ - እስኪ የልጅቷን ሕይወት እንዴት እንዳተረፍክ ንገረኝ?›› ሰውየው ‹‹ኧረ እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም›› አለ፡፡ ‹‹እሺ፤ ጀግናው የኒው ዮርክ ሰው..›› ብሎ ጋዜጠኛው ሊቀጥል ሲል÷ ሰውየው ‹‹ኧረ የኒው ዮርክም ሰው አይደለሁ፤ ለጉብኝት ነው የመጣሁት›› ይለዋል፡፡ ጋዜጠኛው ፈገግ ብሎ ‹‹ታዲያ የምን አገር ሰው ነህ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ሰውዬው ‹‹የሳውዲ አረቢያ›› ሲል ይመልሳል፡፡ በማግስቱ የኒው ዮርክ ጋዜጦች ‹‹አንድ አክራሪ ኢስላሚስት በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ውሻ ቀጥቅጦ ገደለ›› የሚል ዜና ይዘው ወጡ፡፡

ጆርጅ ቡሽ በዘመናቸው ከሰሯቸው ስህተቶች በሙሉ የከፋ ሊባል የሚችለው በሽብርተኞች ላይ ባወጁት ዘመቻ ‹‹ሽብርተኛ›› ማለት ‹‹ሙስሊም›› ማለት እንዲመስል ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህንን ለማስተባበል መንግስታቸው ቢደክምም ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎች የተወናበደ አመለካከት አፍርተው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ብስጭት ሃይማኖታዊ ሕልውናቸውን ለማዳን የፈለጉ የሚመስሉ ምስኪኖች አልቃይዳን ለመደገፍ ተገድደዋል፡፡

አሜሪካ የምታደርገው ማናቸውም ነገር በሌላው ዓለም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ሉላዊነት (globalization) ባመዛኙ አሜሪካዊነት (americanization) መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ሐቅ ነው፡፡ የአሜሪካ ተጽዕኖ ለሁሉም የዓለም አገራት ይዳረሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ይሄ ተጽዕኖ ይንፀባረቅ ይሆናል የሚለው ስጋት ለብዙዎቻችን ልብ የሚያርድ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተለያየ እምነት ተከታዮች (በተለይም ሙስሊም እና ክርስቲያን ሕዝቦች) ተቻችለው እንደሚኖሩባት ከአፈታሪክ በላይ በተግባር ማረጋገጥ የቻለች አገር ነች፡፡ ለዚህ እማኝ ለመጥራት ሰዎች ማነጋገር አይገባኝም፡፡ የኔ ቤተሰቦች እና የአጥር ድንበር የሚጋሩን ጎረቤታችን ዓይነተኛ ምሳሌዎች ነን፡፡ ለክርስትያን በዓል የክርስቲያን ጠላ፣ የሙስሊም ቀሪቦ፣ ለሙስሊሙም እንደዚያው እየተባለ ሁለት ድግስ በሚደገስበት ሁለት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግኩት፡፡

የሁለቱ ቤተሰቦች ወዳጅነት የሙስሊሙንና ክርስትያኑን ማሕበረሰብ ወዳጅነት የሚገልፀው ካልመሰላችሁ፡፡ የማሕመድ ሰልማንን ‹‹ፒያሳ - ማሕሙድጋ ጠብቂኝ››ን አንብቡ፡፡ ትግራይ ውስጥ መስኪድ ለማሰራት በመተባበሯ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የተሰጣትን የምስክር ወረቀት ይነግራችኋል፡፡ ይህን መሰሉን ነገር ከመስኪዱም፣ ከቤተክርስቲያኑም ማግኘት ይቻላል፡፡

ይሄ ወዳጅነት፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ማጣት የሚፈልግ ማንም የለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ አነስተኛ ግጭቶች ነገሮችን እያከረሩ ከመሄድ ዕድላቸው ይልቅ ተኮንነው የመምከናቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ነገሩ እንዲከር የሚፈልጉ ቢኖሩም እንኳን ተራ ጽንፈኞች፣ ጥላቻን የኑሮ መርሕ አድርገው የሚኖሩ ሰዎች ከመሆን አያልፉም፡፡ የጋራ ዳራችን፣ መጪ ታሪካችንን እንድናበላሸው እንደማይፈቅድልን የማይገባቸው ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በአወሊያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ እየተሰማ ያለው ብሶት ብዙም ሲስተጋባ አይታይም፡፡ ለምን ለሌሎቻችን እና በተለይም የሕዝቡን ብሶት ለሕዝቡና ለመንግስት ማድረስ ያለባቸው ሚዲያዎችን አላነጋገረም የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ እኔ በግሌ ስለእስልምና አስተምህሮት ያለኝ ዕውቀት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ቢሆንም የአወሊያ ተማሪዎች የተቃውሞ ድምጽ ከምን እንደመነጨ ለማጣራት ሞካክሬያለሁ፡፡

የአወሊያ ተማሪዎች ‘‹‹አሕባሽ›› የተባለ አስተምህሮት በግድ እንድንማር ተፈርዶብናል÷ ይህንን አናስተምርም ያሉ ዑስታዦቻችን (መምህራኖቻችን) ተባረውብናል፤ ከዚህ ድርጊት ጀርባ መንግስት እጁ አለበት’ ሲሉ ነው ለተቃውሞ የተነሱት፡፡ በጥቅሉ ‹የሚቃወም ካለ ችግር አለ› የሚል አቋም አለኝ፤ አባቶቻችን ‹‹ያልተፈሳው አይሸትም›› እንደሚሉት፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ‹አሕባሽ› ምንድን ነው? ተማሪዎቹ ለምን ተቃወሙት? እንደተባለው የመንግስት እጅ ካለበት÷ መንግስት ለምን ፈለገው?

እነዚህን ጥያቄዎች የመረጥኩት በብልሐት ወይም ደግሞ ከልቤ አስቤበት አልነበረም፡፡ ሆኖም (እ.ኤ.አ. 2007 የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆጠራ) 34በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን /ሙስሊሞችን/ ጉዳይ ጉዳዬ ብዬ የማሰብ ግዴታ ስለነበረብኝ ነው፡፡ በርግጥ በውስጤ ለተፈጠሩ ጥያቄዎች ጥቂት መልሶችን ማግኘቴ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ‹አሕባሽ› የተባለው አስተምህሮት ከኢትዮጵያ ወደሊባኖስ በተሰደዱ ኢትዮጵያዊ ሼህ የተመሰረተ ስለመሆኑ፣ መንግስት የአሕባሽ አስተምህሮት ‹‹ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትን ይቀንሳል›› የሚል ግምት (ልብ በሉ ማረጋገጫ ሳይሆን ግምት) እንዳለ፣ መንግስትም ይህንን ግምት ሊያምንበት የሚችልበት ብቻ ሳይሆን ‹‹ምናልባት ሊፈጠር የሚችለውን የሃይማኖት ግጭት›› በአሕባሽ አስተምሮት መቆጣጠር የሚ’ቻልበት ዕድል አለ ብሎ እንደሚያምን ያልተረጋገጡ መረጃዎችን አገኘሁ፡፡ ነገር ግን መጠየቅ የነበረብኝ ሌላ ጥያቄ መሆኑ የገባኝ ኋላ ላይ ነው፡፡ መጠየቅ የነበረብኝ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት መንግስትና ሃይማኖት በየግል ጉዳዮቻቸው ጣልቃ ላይገባቡ ቃል ከተጋቡ በኋላ÷ ‹በርግጥ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ይሆን? እንዴት ተደርጎ?› የሚል ጥያቄ ነበር፡፡

እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በፓትርያርኩ (አቡነ ጳውሎስ) ላይ እምነት የላቸውም፡፡ በአጭር አማርኛ ‹ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያላቸው የመንግስት ሹመኛ ናቸው› ብለው ያምናሉ፡፡ እኔም እንደገለልተኛ ወገን መስክር ብባል ሰውየው ከዚህ የፀዱ ናቸው ብዬ መናገር አልችልም፡፡ በተለያዩ ቡራኬዎቻቸው አስታክከው ስለ‹ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ› ሲደሰኩሩ በቴሌቪዥን መስኮት ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መጅሊሱን (በኢ.ኦ.ቤ.ክ ቋንቋ ሲኖዶሱን እንደማለት?) አያምኑበትም፡፡ የመንግስት ሥራ አስፈጻሚ ወይም ወኪል አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

እናም የአወሊያ ተማሪዎች የለኮሱት ‹‹ዑስታዦቻችን መባረር የለባቸውም፣ ያለምርጫችን የአሕባሽ አስተምሮትን አንጎነጭም፣ መጅሊሱ ይውረድልን›› አቤቱታ በየመስኪዶቹ አርብ፣ አርብ ለሶላት በሚሰባሰቡ ሙስሊሞች ተቀጣጥሏል፡፡ ጥያቄው አማኞቹ የሚያምኑትን እና መማር የሚፈልጉትን ነገር የመምረጥ መብት አላቸው፣ ወይስ ከላይ የተሰጣቸውን ብቻ ዝም ብለው እንዲቀበሉ ነው የሚለው ነው፡፡ ብዙዎቹ የተቃውሞው ተሳታፊዎች የአሕባሽ አስተምህሮት እንዲስፋፋ መንግስት በመጅሊሱ በኩል ግፊት ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ ካነበብኳቸውና ከሰማሁዋቸው ዜናዎች ተረድተዋል፡፡ የጠነከረ ማረጋገጫ ባይኖረኝም ለማመን አልቸገረኝም፡፡ እዚህ ጋር ነው ሃይማኖታዊ አመለካከታችንን ገለል አድርገን ከሙስሊም ወንድሞቻችን ጎን ቆመን እንድታገል የምንገደደው፡፡

ሙስሊም ወንድም እህቶቻችን የእምነት ነፃነታቸው ካልተከበረላቸው፣ ነገ ሌሎችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ዛሬ አሕባሽ በግፊት ሙስሊሞች ላይ ከተጫነ፣ ነገ ደግሞ ሌላ ነገር የኦርቶዶክስ ወይም ሌላ እምነት ተከታዮች ላይ አይጫንም ማለት አይቻልም፡፡

ከሙስሊም ወገኖቻችን ጎን ቆመን መታገልና የጉዳዩን በሰላማዊ እና ጥቅማቸውን ባስከበረ መንገድ መፈፀም አለመፈፀሙን መከታተል የሚኖርብን ‹‹ነግበኔ›› በሚል ስሜት ብቻም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን አባቶቻችን የገነቧት በጋራ መስኪድም ቤተክርስትያንም በመገንባት መሆኑን መተረክ ብቻ ኢትዮጵያዊነትን መውረስ አይቻልም፡፡ ለተናጠል ችግሮቻችን ሳይቀር በጋራ መፍትሄ በማፈላለግ እንጂ፡፡

ሰሞኑን በተፈጠረው የአወሊያ ተማሪዎች ተቃውሞ ላይ ብዙ የዜና አውታሮች አስተያየትም፣ ዘገባም ከማስፈር ተቆጥበዋል፡፡ ምናልባት ፍራቻቸው የሙስሊሞች የውስጥ ጉዳይ ነው በሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም መንግስት እንደፈራነው በጉዳዩ ውስጥ እጁ የሚኖርበት ከሆነ ጉዳዩን ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንዲሉ አፍኖ ሊያስቀረው ይችላል፡፡

ስለዚህ እኛም ‹የሙስሊሞች ጉዳይ ለሙስሊሞች› ከማለታችን በፊት፣ ወይም በጽሁፌ ራስጌ እንዳስቀመጥኩት ቀልድ ስለጽንፈኞች እያወራን ጽንፈኞች እንዳንሆን ሲባል - ሚዲያዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲዘግቡት እና መጀመሪያውንም፣ ሒደቱንም፣ መጨረሻውንም እንዲያሳውቁን እመክራለሁ፡፡ ጉዳዩ የሁላችንም ነው፡፡

1 comment:

  1. በጣም አሪፍ ጽሁፍ: እንደው በደፈናው ተከባብረን የኖርንባት አገር: እያልን ብንለፈልፍ ምንም ትርጉም የለውም: ተግባር ላይ ካልተገኘን: ኦርቶዶክሱ ሲጮህ ሙስሊሙ አብሮ ካልጮኅ: ሙስሊሙ ሲጮህ ኦርቶዶክሱ ካላገዘው: ሁሉም የራሱ ጉዳይ ካልን: በምንድናው ተክባብረን የምንኖረው:መከባበር ማለት ቁስሉ ሲሰማኝ ህመሙ ሲያመኝ እንጂ አለመጣላት አለመነታረክ ከሆነማ መፈራራት እንጂ በከባበር አይባልም......ጥሩ ጅማሬ ነው ግን ብዙ ይቀራል

    ReplyDelete