የገመና 2፣ እና የሰው ለሰው ድራማዎች (ሶጵ ኦጴራዎች?) ሁለቱም ተወዳጅ ጀግና ከመፍጠሩ ይልቅ፣ የሚጠላ ጀግና የመፍጠሩ ሙከራ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ዘመነኞቹ የሶጵ ኦጴራ ደራሲዎች መጥፎ እና ጥሩ ሰዎችን እየፈጠሩ ከማባላት የድሮ የታሪክ አወቃቀር ስልት እየወጡ፣ ከሕይወት ውጣ ውረድ ጋር ታግለው የሚያሸንፉ ጀግኖችን በመፍጠር ላይ አተኩረዋል፡፡ የኛዎቹ ደራሲዎች የሚፈጥሯቸው ጀግኖች ግን የሚፈተኑት ለእኩይ ተግባር የተፈጠሩ በሚመስሉ ሰዎች ነውና በዚያው አካሔድ እያነሳን እንጥላቸዋለን፡፡
ሁለቱም ርዕሳቸው በርዕሴ ላይ የተጠቀሱ ተከታታይ ድራማዎች በቁጥር የማይታወቁ መሪ ተዋናዮችን የሚያሳትፉ ናቸው፡፡ (ልብ ብላችሁ እንደሆነ ብዙዎቹ ተወዳጅ ሶጵ ኦጴራዎች በአማካይ አምስት መሪ ተዋናዮች ብቻ ይኖሯቸዋል፡፡) እነዚህ በርካታ ገጸባሕርያት ሁሉንም ጉዳይ እየነካኩ ቢያደነጋግሩንም፣ በልማታዊው የኢቴቪ ፍላጎት መሰረት ልናተኩርባቸው የሚገቡን ጥቂት የታሪክ መስመሮች እንዳሉ ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ነገር ግን የደራሲዎቹ ምልከታና የኢቴቪ ፍላጎት አልተጣጣመም ይሆናል፤ ከኢቴቪ ፍላጎት ጋር የተጣረሰ መልክት እየተላለፈ እንደሆነ አሁን አሁን እየገባኝ መጥቷል፡፡
ገመና 2 የሰው ለሰውን ያህል ልብ የማሸበር አቅም አላገኘም፡፡ የሰው ለሰዉ አስናቀ ወደጅ መስሎ የሚሰራቸው ሴራዎች፣ በድራማው ውስጥ እንድናደንቀው የሚፈለገው መስፍንን ያለዕውቀቱ አንድ ርምጃ እየቀደመ ያርበደብደዋል፤ እኛንም እንደተመልካች ያርበደብደናል፡፡ ‘ፌሚኒስቱ’ ገመና 2 ግን እኩይዋ ለምለም፣ ጀግናችን የሆነችውን ሜላት የምታርበተብትበት መንገድ ያን ያክል ጠንካራ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይመስላል ከሰሞኑ የሰው ለሰዉ አስናቀን የሚመስል መሰሪ ለማምጣት እየተጉ ያሉት - ሰውዬው አቶ ጌታቸው ናቸው፡፡ በሃብታቸው ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት (ወይም እንደሆኑ የሚሰማቸው) ሰው ማለት ናቸው፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ሁለት ተከታታይ ድራማዎች የሚሸበሩት በእውነተኛ የኢትዮጵያውያን ችግሮች አይደለም፡፡ በሁለቱም ድራማዎች ውስጥ ያሉት ባሕርያቶች ሃብታሞች ናቸው፤ ብዙሐኑ ኢትዮጵያዊ ግን ድሃ ነው፡፡ በሁለቱም ድራማዎች ውስጥ ያሉት ሰዎች ያሉባቸው ችግሮች የክፉ ግለሰቦች ሴራ ነው፤ የብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ችግር ግን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነው፡፡ ለነገሩ የዘነጋሁት ቁምነገር እነሱ ኢቲቪዮጵያውያን ሲሆኑ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናችንን ነው፡፡
እኔም እንደድራማዎቹ ሁሉን መነካካት አምሮኝ ነው እንጂ አጀንዳዬ እሱ አይደለም፡፡ ደራሲዎቻችን የሚያሸንፉ ተወዳጅ ባሕርያትን ከመፍጠር ይልቅ የሚሸነፉ መፍጠሩ ለምን ቀለላቸው? ከሰናዮቹ የበለጠስ ለምን ለእኩዮቹ ጀግንነትን ማጎናፀፍ አስፈለጋቸው? ምናልባት በሃገራችን የሚያውቁት እውነታ ይኸው ብቻ ሆኖባቸው ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች በጭንቅላቴ ውስጥ እየተንጫጩ ነው፡፡
እውነታው ምንድን ነው?
እውነታው በሃገራችን የጠቅላይ ሚነስትሩን ሴራና ኢ-ሃገራዊ ስሜት ሁላችንም እናውቃለን፡፡ (እናንተ፤ እዚህችጋ ይቅርታና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ሰሞኑን ‹‹የመለስ አባት ባንዳ ነበሩ፡፡›› ብለው የጻፉት እውነት ነው እንዴ?) የሆነ ሆኖ ምርጫውን 99 በመቶ ድምጽ የሚያሸንፉት እሳቸው ናቸው፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚመሰክረው ለሳቸው ነው፣ የመስሪያ ቤቶቻችን አለቆችም የሚመሰክሩት ለርሳቸው ነው፡፡ በሰው ለሰው ድራማ ውስጥ አስናቀም ቁርጥ መለስ ዜናዊን ነው - ሰው መሳይ በሸንጎ!
በገመና 2 ድራማ ውስጥ ለምለም በባለቤቷ በአቶ አካሉ ሥራ አስኪያጅነት ይተዳደር የነበረውን የእርዳታ ድርጅት በእጅ አዙር ስታሾረው እንመለከታለን፡፡ በርግጥ ድራማው ላይ ስንት ዓመት እንዳመሉ ከኖሩበት ድርጅት ውስጥ የአቶ አካሉ ድንገተኛ መገንጠል ባያሳምንም÷ የለምለም ሚና፣ ጨካኝነት እና አርበጅባጅነት ግን ቀዳማይ እመቤት እያሉ የሚጠሯቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት አዜብ መስፍንን አስታወሰኝ፡፡ (በነገራችን ላይ ቀዳማይ እመቤት የሚባሉት የፕሬዚደንቶች ሚስቶች አይደሉም እንዴ?) ፈላጭ ቆራጭነታቸው በገደምዳሜ የሚነገርላቸው ወ/ሮ አዜብ የእጅ አዙር ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆኑም አይደል? የገመና 2 ደራሲዎችስ ቢሆኑ ለምለምን የመሰለ ገጸ ባሕሪ ያገኙት ከእውነተኛው ዓለም አይመስላችሁም?
እናም እላችኋለሁ፤ የገመና (አንድ) ደራሲ (አዶኒስ) ያልቻለውን ሰናይ ምግባር ያለው ጀግና የመፍጠር ሙከራ የዘንድሮዎቹ የገመና 2 እና የሰው ለሰው ደራሲዎችም መፍጠር ያቃታቸው እውነተኛውን የሃገራችንን ገጽታ ለማንፀባረቅ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት አይመስላችሁም?
Comments
Post a Comment