Pages

Monday, February 11, 2019

ለውጡ እና የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ


አሁን እየተካሔደ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ፍኖተ ካርታ የለውም በሚል በተደጋጋሚ ተተችቷል። ይልቁንም፣ ሲሆን ሲሆን ለብዙኃን መገናኛዎች አጀንዳ በማበጀት፥ ሳይሆን ሳይሆን ደግሞ “ሚዲያዎች ምን አሉ?” የሚለውን እያሳደዱ መልስ በመስጠት የተጠመደ ለውጥ ነው የሚለው የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል። ብዙኃን መገናኛዎች በለውጡ ላይ ይህንን የሚያክል ትልቅ ተፅዕኖ እንዳላቸው ከታወቀ ዘንዳ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። ለውጡ ፍኖተ ካርታ ባይኖረውም፥ ብዙኃን መገናኛዎቹ ግን ፍኖተ ካርታ ሊኖራቸው ይገባል፤ “ምን-ለምን-ለማን ነው የሚጽፉት ወይም ለተደራሲዎቻቸው የሚያቀርቡት?” የሚለውን በነሲብ ሳይሆን በነቢብ ቢያድርጉት መልካም ነው በሚል ዓላማ ይህ ጽሑፍ እንደ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።

የብዙኃን መገናኛዎች ሚና በጥቅሉ

በመሠረቱ የብዙኃን መገናኛዎች ሚና “ትርክት ማኖር” ነው። ዜና፣ ትንታኔ፣ ምርመራ፣ ማጋለጥ… ሁሉም አንድ ዓላማ አላቸው። በትርክት መብለጥ ነው። አንድ ጥሬ ሐቅ ከብዙ አንግሎች ‘ሪፖርት’ ሊደረግና ሊተነተን ይችላል። ሰዎች ያንን ጥሬ ሐቅ እንዴት መረዳት እንዳለባቸው የሚወስኑበት ደጋግመው ከሰሙት ወይም ደግሞ ይበልጥ ካሳመናቸው ትንታኔ አንፃር ነው። ስለዚህ ሁሉም ብዙኃን መገናኛዎች ዋነኛ ዓላማቸው ሐቁን ለዜጎች ማድረስ ነው ቢባልም ቅሉ፥ ዋናው ቁም ነገር ሐቁን የሚተነትኑበት መንገድ ነው።

ለምሳሌ ያክል የአድዋ ጦርነትን ብናስታውስ፣ ለኢትዮጵያውያን የምሥራች ሲሆን፥ ለጣሊያኖች ደግሞ መርዶ ነው። የጣሊያን ብዙኃን መገናኛዎች መርዶውን ለዜጎቻቸው ያደረሱት በቁጭት ሲሆን፣ ‘የተነተኑትም ለሽንፈት የዳረገን ምንድን ነው? ለወደፊቱስ ምን ማድረግ አለብን?’ በሚል ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ቢኖራት ኖሮ ትንታኔው በተቃራኒው ታቀርብ ነበር። ስለሆነም የብዙኃን መገናኛዎች የመጨረሻ ግብ ለቆሙለት ወገን ወይም ግብ ተሥማሚውን ‘ትርክት መፍጠር’ እና ያንን ትርክት ገዢ (mainstream) ማድረግ ነው።