Pages

Monday, July 30, 2018

ብሔርተኝነት፤ ቅዱስ ወይስ እርኩስ?

በዚህ ርዕስ ረዥም መጣጥፍ መጻፍ ከጀመርኩ ረዥም ግዜ ሆነኝ፡፡ እስካሁን አላለቀም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ጉዳዩ ስሜት የሚነካ እና በስሜት የሚነዳ ስለሆነ ፈርቼው ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋስኦዋችንን በተከታተልኩት ቁጥር የተረዳሁት አንድ ነገር ቢኖር "ብሔርተኛ ነኝ" በሚሉ እና "ብሔርተኛ አይደለሁም" በሚሉት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ብሔርተኝነትን የማመን እና የመሸሸግ ችሎታ ልዩነት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንዴ ልዩነቱ ግለሰቦቹ የሚያራምዱት ብሔርተኝነት የሚያቅፋቸው ሰዎች ቁጥር የበዛ መሆኑ ‹ብሔርተኝነቱን› የመሸሸግ ዕድል ያገኛል፡፡ በጣም በተሳሳተ መደምደሚያ ላለመጀመር ያክል "ብሔርተኝነት" ደረጃው እና ልኩ ይለያይ ይሆናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከውስጡ የወጣለት ሰው የማግኘት ዕድላችን ጠባብ ነው ብለን እንስማማ፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ‹ብዙኃን ብሔርተኛ ናቸው› የሚል መደምደሚያ ይዤ ነው ይህንን የምር አጭር ያልሆነ መጣጥፍ፣ ረዘመብኝ ካልኳችሁ መጣጥፌ ጨልፌ እና ጨምቄ የማስነብባችሁ፡፡

የመጀመሪያው አንቀፄ እንደሚያመለክተው ‹ብዙኃን ብሔርተኞች ናቸው›፡፡ ‹ብሔርተኝነት ቅዱስ ነው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ ማንሳት ‹ብዙኃን ቅዱስ ናቸው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ እንደማንሳት ያስፈራል፡፡ ቢሆንም እንጋፈጠዋለን።

ብሔርተኝነት ሲበየን

ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ለብሔርተኝነት ያላቸው ንቀት የትየለሌ ነው፡፡ ንቀቱ አንድም ብሔርተኝነት ‹ማኅበራዊ ፈጠራ› (social fabrication) ነው ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሰው ልጅን ያክል ባለ ብሩሕ አእምሮ በአጋጣሚ በበቀለበት ማኅበረሰብ ብቻ መበየን ከእውነታው የራቀ ስለሚሆን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የብሔርተኝነት የመዝገበ ቃላት ፍቺው "ተመሳሳይ ባሕል ያላቸው ሕዝቦች ፖለቲካዊ ነጻነት መፈለግ" ወይም "በአገር በጣም የመኩራት ስሜት" ነው (P.H. Collin (2014))፡፡

ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ብሔርተኝነትን የሚበይነው እኔንም በሚያስማማ መልኩ ነው፡- "የአንድ ግለሰብ ታማኝነት እና ቁርጠኝነት ከሌሎች ግለሰቦች እና ቡድኖች ፍላጎት በላይ ለብሔረ-መንግሥቱ (nation state) ማድላት ላይ የተመሠረተ ርዕዮተዓለም ነው"። በዚህ መሠረት ቀጣዮቹን ርዕሰ ጉዳዮች እያነሳን እንጥላለን፡፡

ሰዎች ለምን ብሔርተኛ ይሆናሉ?

ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ብሔርተኛ የሚሆኑት ፈቅደው እና አቅደው ሳይሆን ባጋጣሚ ነው፡፡ አጋጣሚው የሚጀምረው ‹የት እና ከማን ተወለዱ?› ከሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ብሔርተኝነትን በንባብ እና በውይይት ሊያዳብሩት ይችላሉ እንጂ የሚጀምሩት ግን በውርስ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ብሔርተኝነት ራሳቸውን በአንድ የብሔር አባልነት የሚጠሩ ሰዎች እስኪኖሩ ድረስ አይኖርም፡፡ የሆኑ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እና የሚያስተሳስራቸው ማኅበራዊ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን በአንድ ማንነት ለይተው መጥራት ሲጀምሩ ወይም በሌሎች በዚያ ማንነት መጠራት ሲጀምሩ ብሔርተኝነት ተጀመረ ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብሔርተኝነት በስሎ እና ጎርምቶ የሚወጣው እነዚያ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ እና/ወይም በማንነታቸው ሳቢያ በሌሎች እየተጠቁ እንደሆኑ ሲያስቡ ነው፡፡ ብሔርተኝነት የሚጎመራው የጋራ ማንነት ላይ ጥቃት ያደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡ የተለየ ማንነት እንዳላቸው የሚታመኑ ጠላቶች ሲኖሩ ነው፡፡

Sunday, July 22, 2018

የማንን ግዛት ማን ያስተዳድር?

ነገሮችን አቃልሎ እና ሸንሽኖ ለመረዳት መሞከር ጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢኖርም፥ ሁሌም ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም። አገርን የሚያክል ትልቅ ፅንሰ-ሐሳብ በግለሰብ ርስት ዓይን  ለመረዳት መሞከርም ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ ስህተቶች አንዱ ነው። በኢትዮጵያ 'እከሌ የተባለው ግዛት የማን ነው?' እና 'እከሌ የተባለውን ግዛት ማን ያስተዳድር?' የሚሉት ጥያቄዎች ዐውድ በጣም አሳፋሪ እና 'ገና በዚህ ጉዳይ እንኳ መግባባት አልቻልንም እንዴ?' በሚል ራሳችንን እንድንታዘብ የሚያደርግ የዘወትር ገጠመኝ ነው። 

'አዲስ አበባ የማነች?' የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ መስማት አስደናቂ አይደለም። የቡድን ሥም እየጠሩ፣ ታሪክ እየደረደሩ የባለቤትነት ማስረጃ ለማምጣት የሚሞክሩትን ሰዎች መከራከሪያ ማድመጥም የከተማዋን ኅልውና ያክል አዲስ ነገር አይደለም። የዚህ ጽሑፍ መነሻም የምክትል ከንቲባዋን ሹመት ተከትሎ የዚህ ክርክር እንዳዲስ ማገርሸት ነው። አዲስ አበባ የማን ነች? እነማን ናቸው ሊያስተዳድሯት የሚገባቸው? መጀመሪያ ግን ኢትዮጵያ ራሷስ የማነች?

ኢትዮጵያ የማነች?

ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ኢትዮጵያ የምንላት ሕዝቧን፣ ግዛቷን፣ መንግሥቷን እና ሌሎች የዓለም መንግሥታት የሚቀበሉትን ሉዓላዊነቷን ነው። ሉዓላዊነት የአገር ፅንሰ-ሐሳብነት መገለጫ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች "የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች" ናቸው (አንቀፅ 8)። ይህ ማለት 'ኢትዮጵያ የኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግራዋይ፣ ወዘተ የጋራ ንብረት ናት' የሚል ትርጉም ይሰጣል። ከላይ ሲታይ 'ኢትዮጵያ የሁሉም ናት' የሚል ጭብጥ ያለው ይመስላል። ነገር ግን በዚህ ብያኔ እያንዳንዱ ዜጋ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለድርሻ መሆን አይችልም። 'የኢትዮጵያ' የሚባሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አባል ያልሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት መሆን አይችልም።

Tuesday, July 3, 2018

ለውጥ እና ውዥንብር

አሁን ያለንበት ሁኔታ "ታስሮ የተፈታ ጥጃ" ሁኔታ ነው። መዝለል እና መቦረቅ - የነፃነታችንን ልክ መፈተን የምንፈልግበት ወቅት ነው። ምክንያቱም ነፃነታችን ከእስር የተፈታው ገና አሁን ነው፣ የዴሞክራሲ ባሕል አልነበረንም፣ በዚያ ላይ ያልተመለሱ እልፍ ጥያቄዎች አሉን። ይሁን እንጂ ሲደክመን እንሰክናለን። መዝለል ስለምንችል ብቻ አንዘልም። መርገጥ ስለምንችል ብቻ አንራገጥም። ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በተደራጀ፣ በሕጋዊ እና ሠላማዊ መንገድ ታግለን ማስመለስ እንጀምራለን። ከዚያ በፊት ግን ዝላያችን እና እርግጫችን ለገዢዎቻችን የለውጡን ተስፋ ለመቀልበሻ፣ እኛን መልሶ ለመርገጫ ምክንያት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

አንዲት ኤርትሪያዊት የትዊተር ተጠቃሚ፣ 'ሰውያችሁ ባለ ግርማ ሞገስ እና ጥሩ ተናጋሪ በመሆኑ እንዳትሸወዱ፣ የእኛም መሪ እንደዛ በመሆኑ የለውጡን ተቋማዊነትን ሳናረጋግጥ ነው ለዚህ የተዳረግነው' የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያውያን አቻዎቿ አስተላልፋለች። አዎ፣ የዛሬው ታላቁ አምባገነን ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የዛሬ 27 ዓመት ገደማ በኤርትራውያን ዘንድ ታላቅ ሕዝባዊ ይሁንታ ያለው መሪ ነበር።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከራሳቸው መጠበቅ" በሚለው ጽሑፌ 'ብዙዎቹ ነጻ አውጪዎች ኋላ አምባገነን ይሆናሉ' ማለቴን እንደ ጅምላ ድምዳሜ የወሰዱብኝ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። እኔ ለማመልከት የፈለግኩት በአንድ ወቅት 'ነጻ አውጪ' የነበረ፣ ሌላ ግዜ 'አምባገነን' እንደማይሆን አያረጋግጥም ነው። ይህ እንዳይሆን ብቸኛው ዋስትና 'ቁጥጥርና ሚዛን' (check and balance) ነው። ትላንት ጓደኞቼ ስለ ኢዲ አሚን ዳዳ አንድ ጽሑፍ እያስነበቡኝ ነበር። ከዓለማችን የምንግዜም አምባገነኖች አንዱ የሆነው ኢዲ አሚን በሥልጣን አፍላው ዘመን በምዕራባውያን ሚዲያዎች ሳይቀር የተንቆለጳጰሰ ሰው ነበር። ሰውን አምባገነን የሚያደርገው ተቋማዊ ነጻነት አለመኖሩ እና የግለሰቦች ሥልጣን አለመገደቡ ነው። 

ኢትዮጵያ ለውጥ ለምን አይዋጣላትም?

ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት አሁን ያለንበትን የለውጥ ተስፋ ጥላሸት ለመቀባት ወይም ተቀልብሷል ለማለት አይደለም። ለውጡ ከግለሰቦች በጎ ፈቃድ ወደ ተቋማዊ እውነታነት እንዲሸጋገር ካለኝ ጥልቅ ጉጉት ነው። ሁሉም ሰው የለውጡን አካሔድ በጥንቃቄ እንዲመለከተው ስለምፈልግ ነው።

ኢትዮጵያ እንዲህ የለውጥ ተስፋ ውስጥ የገባችው አሁን ብቻ አይደለም። የንጉሣዊው ስርዓት መደርመስ እና የመሬት ላራሹ መታወጅም ግዙፍ ሕዝባዊ ይሁንታ እና ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። የምርጫ 1997 ዋዜማ አገራችን የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ልታካሒድ ነው በሚል ትልቅ ተስፋ