Pages

Friday, January 27, 2012

የኢትዮ ቴሌኮም ቁልቁለት

ፎቶ፤ www.stockphotopro.com

ሐሙስ ዕለት አመሻሹ ላይ ስልኬ ካርዱን ጨርሶ የጀመርኩትን ወሬ አቋረጠኝ፡፡ ወዲያው ካርድ ገዛሁና ሞልቼ ወሬዬን ለመቀጠል ተጣደፍኩ፡፡ ምን ዋጋ አለው? አዲሱ *805* የካርድ መሙያም ሆነ የቀድሞው 904 ገንዘቤን ሊቀበሉኝ አልቻሉም፡፡ ብስጭቴ እየተጋጋለ ደጋግሜ ስሞክር አመሸሁ፤ አልተሳካም፡፡ በማግስቱ ካርዱን ለወሬው የማድረስ ሕልሜ አልቆ፣ ገንዘቤን ከኪሳራ ለማዳን ማለዳ ጀምሬ መቀጥቀጤን ቀጠልኩ÷ በቀላሉ የሚሆን አልነበረም፡፡ በመጨረሻ እኩለ ቀን ሲቃረብ 805 – “Sorry, the operation failed. Bye” የሚለውን የተለመደ ጽሁፍ ካስነበበኝ በኋላ÷ ካርዴ እንደተሞላ የሚነግር አጭር የጽሁፍ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ደስ አለኝ ልበል?! ደስ ሊለኝ ግን አይገባም፤ ምክንያቱም ፍዳዬን ሳይ አድሬ ያረፈድኩት በኔ ጥፋት ሳይሆን በቴሌኮሙ የቴክኒክ ድክመት ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከየት ወዴት?
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የስንት ዓመት ስሙን በጥላ ቢሱ ኢትዮ ቴሌኮም የቀየረው የለውጥ ርምጃ የሚጀምረው በስም ለውጥ ነው ከሚል መርኅ ይመስላል፡፡ የራሱን የሚመስል ስም ያጎናፀፈው ፍራንስ ቴሌኮም ቴሌን ማስተዳደር ሲጀምር÷ የተጣለበት ተስፋ (ትርፍ መጨመር ቢሆንም) የተዘበራረቀውንና ዘመናዊነት የጎደለውን አሠራር እንዲያፀዳ በማሰብም ጭምር መሆኑም ይታወቃል፡፡ ግን እየሆነ ያለው የተባለው ነገር ነውን?

ፈረንሳዊው አስተዳደር ሥራውን አሀዱ ያለው የሞቱና ድርጅቱን የለቀቁ ሠራተኞን በኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ ነበር፡፡ በርግጥ ያንኛው ለዚህንኛው ሲያስረክብ የተፈጠረ ስህተት ነው ተብለን አምነን ነበር፤ እየቆየን እየተመለከትን ያለነው ግን የዛኔውን እምነታችንን ዛሬ ላይ ቆመን እንድንጠራጠረው የሚያስገድድ ነገር ነው፡፡

ቴሌ ‹‹የኔትዎርክ ማስፋፊያ›› አድርጓል ከመባሉ በፊት ይገጥመን የነበረው÷ አታካች ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው›› አሁን የለም፡፡ የሌለው ችግሩ ተቀርፎ ወይም ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በአገልግሎት ተዳርሰው ግን አይደለም፡፡ ‹‹የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም›› በሚል ቁጣ ተተክቶ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ከልካይ የመሰለ እና የሚያበሳጭ ዓረፍተ ነገር የመረጠበት ምክንያት ምስጢር ነው፡፡ በተጨማሪም divert የተደረጉ ስልኮች ላይ ስንደውል “This party cannot accept your call” የሚል ሰንካላ ነገር እየተናገሩ÷ የደውልንለት ሰው እኛን ብቻ ያገደን እስኪመስለን ድረስ ያደናግሩናል፡፡ በበዓላትና በሰንበት ቀናት ‹‹ኔትዎርክ›› ማግኘት አስቸጋሪ ሁኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሒሳብ ምሽት አካባቢ ላይ መሙላት የሞት ሽረት ትግል የሚጠይቅ ነገር እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ቴሌኮሙ ወዴት እየተጓዘ ነው?

ቋንቋችንን መልሱልን?
ቀደም ሲል፤ ስልኬ (ወይም ‹ኦፕሬተሯ›) ታናግረኝ የነበረው በአማርኛ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሲም ካርዱን ስገዛ አንዴ መርጫለሁ፡፡ አሁን ግን ያለኔ ፈቃድ በእንግሊዝኛ ብቻ ታናግረኛለች፡፡ ለምን?... ነው ወይስ ለፈረንሳዮቹ እንዲገባቸው ተብሎ ነው? ፈረንሳዮቹ የሚጠቀሙት በእኔ ስልክ ነው አንዴ?

ዓይነስውራን ምን ይዋጣቸው?
ዓይነስውራን ካርድ ለመሙላት የሰው ዕገዛ ግዴታ ያስፈልጋቸው ይሆናል? ሒሳባቸውን ለማዳመጥ ግን የቀድሞው 904 (በድምጽ) እንጂ የአሁኑ 804 (በጽሁፍ) አይጠቅማቸውም፡፡ ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም 904ን በ804 አገልግሎት እተካዋለሁ ሲል (መጀመሪያ እስከ ‹ጃንዋሪ 31› ተብሎ ነበር፤ አሁን ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል) ሲል ወይም 904 አይቋረጥም የሚል ቃል ለመስጠት ሳይደፍር የቀረው እነዚህ ወገኖች ምን ይሁኑ ማለቱ ወይም ምን አስቦላቸው ይሆን?

ከማስታወቂያው እኛ ምን ተጠቀምን?
ኢትዮ ቴሌኮም የራሱን ማስታወቂያዎች ሲልክ ‹ያው ለኛው ነው› ብለን ዝም ልንለው እንችላለን፡፡ ነገር ግን ገንዘባችንን እየከፈልን የምንገለገልበትን ስልክ ተጨማሪ ገንዘብ እየተቀበለበት የማስታወቂያ መሸቀጫ የሚያደርገን በምን ሒሳብ ነው? እኛ ተገልጋዮቹ ቴሌ ማስታወቂያ ለቆብን ከሚያገኘው ገቢ የምንጠቀመው በምን መንገድ ነው? ማስታወቂያ የሚነገርላቸው ታሪፉን ይጋሩናል?

ድንቄም ‹‹ኢትዮጵያን ከመጪው ዘመን ጋር ማገናኘት!››
የቴሌ መፈክር ‹‹ኢትዮጵያን ከመጪው ዘመን ጋር ማገናኘት›› ቢሆንም የአሁኑን ዘመን እያስመለጠን ይገኛል፡፡ እኔ በዚህች አጭር ጽሁፍ የገለጽኩት ከቴሌ ኃላፊነቶች መካከል አንዷን፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎትን መዝዤ፣ ያውም ከዚያ ውስጥ ጥቂቶቹን አጀንዳዎች ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ ግን ለግሉ ዘርፍ የማይፈቀደው የገዢው ፓርቲ ‹‹የምትታለብ ላም›› ቴሌ በችግር ተተብትቦ እኛንም እየተበተበን ይገኛል፡፡

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ÷ በቴሌኮሙኒኬሽን ንዑስ ርዕሱ ውስጥ ‹‹… በዋጋም ሆነ በጥራት ተወዳዳሪ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዲረጋገጡ ለማድረግ ያለውን የቴሌኮም ካምፓኒ ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በማስተካከል ተቋማዊ አቅሙ መሠረታዊ ለውጥ እንዲያሳይ ይደረጋል…›› ይላል፡፡

‹‹የትራንስፎርሜሽኑ›› ዘመን ተጋምሷል፤ በዕቅዱ ውስጥ ‹‹ያለው ቴሌኮም›› ተብሎ የተጠቀሰው ቴሌ ግን በሥርነቀል ውድቀት ውስጥ እንጂ መሻሽል ውስጥ እንዳልሆነ ለባለቤቶቹ ስናረዳቸው ሐፍረት እየተሰማን ነው፡፡ መፍትሔው ‹‹ያለው ቴሌኮም›› የተባለለትን ቴሌኮም አገልግሎት ለግል ተወዳዳሪዎች መፍቀድ አሊያም ታማኝ ካድሬ ኃላፊዎቹን አንስቶ ሥራውን ማቀላጠፍ ለሚችሉ ባለሙያዎች መልቀቅ በቻ ነው፡፡

4 comments:

 1. ይሄው እኔም የገዛሁት ካርድ አልሞላም ብሎኝ:ይዥው እዞራለሁ::
  ምን ላድርግ 25 ብር እኮ ነው::

  ReplyDelete
 2. The massage saying ‹የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም› is very disrespectful. I wonder what they feel when they hear it. May be it is because they do not respect themselves it is a reflection. I thank u for mentioning only a single point of the whole scenario.

  ReplyDelete
 3. Giving the Telecom Sector to private investors is even going to be a terrible mistake. Because private owned corporate are even more greedy.
  I think the second choice, i.e. removing dumb cadres from the top positions and replacing them with people who have knowledge and experience would be great !

  ReplyDelete
 4. ይሄው እኔም የገዛሁት ካርድ አልሞላም ብሎኝ:ይዥው እዞራለሁ::
  ምን ላድርግ 25 ብር እኮ ነው::

  ReplyDelete