Pages

Monday, September 2, 2019

የእምነት ነጻነት ወይስ አስተዳደራዊ ጥያቄ?

በፍቃዱ ኃይሉ

ሰሞኑን "የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት አደራጅ ኮሚቴ" ያነሳው ጥያቄ የውዝግብ መንስዔ ሆኗል። ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ስለሆነም፣ ምናልባት ደግሞ ለከፍተኛ ግጭት መንስዔ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ይህንን መጣጥፍ የምጽፈውም፣ ከዚህ በፊት ስለማውቃቸው መሰል ውዝግቦች እና ድርድሮች የማውቀውን (የማስታውሰውን ያክል) ለማካፈል ነው። በስተመጨረሻ በወቅታዊው ውዝግብ ውስጥ የዴሞክራሲ እና የመብት ተሟጋቾች ጉዳዩን እንዴት መመልከት አለባቸው የሚለው ላይ የራሴን ነጥብ አስቀምጣለሁ። ይህንን የምጽፍበት ምክንያት የጥያቄውን ምንነት፣ የአቀራረቡን ሁኔታ፣ የቤተ ክርስቲያኗን አቋም እና የምዕመኑን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ማስገባት ለመብት ተቆርቋሪዎች ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ ነው።

በዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ የሒደቱ መገምገሚያ መሥፈርቶቻችን 1ኛ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት የለበትም፤ 2ኛ፣ ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም፤ 3ኛ፣ በውዝግቡ ግጭት እንዳይነሳ እና ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግሥት የመከላከል ኀላፊነት እና ተወዛጋቢ አካላትም ይህንን የማስወገድ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ነው። 

የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ጉዳይ

ያደግኩበት ሰፈር “ራስ ካሣ ሰፈር” ይባላል። የራስ ካሣ መኖሪያ ጊቢ ፊት ለፊት አንቀፀ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አለ። ቤተ ክርስቲያኑ “ጭቁኑ ሚካኤል” በሚል ሥም ነው የሚታወቀው። ይህንን ሥያሜ ያገኘው ከቤተ ክሕነት ጋር በነበረው ውዝግብ ነው። በወቅቱ እዚያው እኛ ሰፈር የሚገኘው የገነተ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሥር ነበር ሚካኤል ቤተ ክርስትያንም የሚተዳደረው። እናም ባንድ ወቅት የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች (ቀሳውስቱ እና ዲያቆናቱ) በገነተ እየሱስ አስተዳደር ሥር መሆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ጎድቶታል ብለው ተቃውሞ አሰሙ። የራሳችን አስተዳዳሪ ይሾምልን ብለው ቢጠይቁም የቤተ ክሕነት ኀላፊዎች አልተባበሯቸውም። ስለሆነም ፀብ ውስጥ ገቡ።
 
በዚህ መሐል የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች “ነጻነታቸውን አወጁ” - ማለትም “በገነተ እየሱስ አስተዳደር አንመራም” አሉ። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ አግኝተው ነበር። ስለሆነም ምዕመኑ በሚሰጠው ሙዳየ ምፅዋት “ጭቁኑ ሚካኤል” ራሱን ማስተዳደር ጀመረ። በወቅቱ በቤተ ክሕነት ቁጥጥር ሥር ባሉ ቤተ ክርስቲያኖች እንዳያስተምሩ ተከልክለው የነበሩት አባ ገብረመስቀልም ሚካኤልን የተከታዮቻቸው ማሰባሰቢያ እና ማስተማሪያ ደብራቸው አድርገውት እንደነበር አስታውሳለሁ። አንዳንዴ የቤተ ክሕነት ሰዎች የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በማስወጣት እና በሌሎች በመተካት ችግሩን ለመፍታት ሲሞክሩ፣ ምዕመኑ እምቢ በማለት ተከላክሎላቸዋል። በስተመጨረሻ ግን ቤተ ክሕነት የደብሩን ጥያቄ በመቀበል ለሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ራሱን የቻለ አስተዳደር በመመደብ ውዝግቡ ተፈትቷል።

ጭብጥ አንድ፤ ቤተ ክሕነት እና የአስተዳደር ጉዳይ በርካታ ውዝግቦች ያሉበት፣ እና ወደ ፊትም የሚኖርበት ውስጣዊ ጉዳይ ነው።

ቤተ መቅደስ እና ቤተ ክሕነት

ብዙዎች እንደ አንድ ቢመለከቷቸውም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ሁለት ዓይነት መዋቅሮች አሉ። በርግጥ ተመጋጋቢ ናቸው። አንዱ መዋቅር መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ መቅደስ ሲሆን፥ ሌላኛው አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ ክሕነት ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ መቅደሱ ሲሆን፥ አስተዳደራዊ አገልግሎቱን (የሀብት፣ የሰው ኃይል እና መሰል ቁጥጥር እና አስተዳደር) የሚሰጠው ደግሞ ቤተ ክሕነት የሚባለው ነው። በቤተ ክርስትያን ውስጥ ሥር የሰደደ ሙሰኝነት እና ጥቅመኝነት ተንሰራፍቷል የሚባለው በቤተ ክሕነቱ ውስጥ በሚሠራው ሥራ ነው። የሙስናው ደረጃ ዲቁናና ቅስና ለመቀበል ከሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ጀምሮ እስኩ ደብር እና አስተዳደራዊ ክፍሎች ውስጥ ባሉ እርከኖች በሙሉ የሚስተዋል እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ።