Pages

Monday, January 2, 2012

እስኪ ስለዋጋ - ቆም ብለን እናውጋ!

From Addis Ababa, Ethiopia
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን ቆሞ የማይጠብቀን ነገር ቢኖር ዋጋ ነው፡፡ የሌላው፣ የሌላው ነገር ቀርቶ የአንበሳ አውቶቡስ ዋጋ እንኳን በተሳፈርንበት ዋጋ መመለስ እስከማንችል ድረስ በፍጥነት ነው የሚለዋወጠው፡፡ (“ማርያምን” አላጋነንኩትም!) ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጥቼ መሃል አዲሳባ መዋል ከጀመርኩ ወዲህ በዋጋ ጉዳይ እንደሳሙና እያደር እያለቅኩ፣ አሁን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፡፡

በሃገራችን ዋጋ የሚጨምሩባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኞቹ ግን የታክስ እና የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ናቸው፡፡ በጥቅሉ በሽታው መንግስት አመጣሽ ወይም ነጋዴ አመጣሽ ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ዛሬ፣ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ላይ ብስጭቱን እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡


ብስጭተ መንስኤ
አንድ መናኛ በርገር ቤት ገብቼ ሳበቃ ለበርገሩ 31 ብር ለአምቦ ውሃ ደግሞ 10 ብር እንድከፍል ተጠየቅኩኝ፡፡ እናንተ በኔ ቦታ ብትሆኑ ምን እንደምትሆኑ አላውቅም እኔ ግን ተበሳጨሁ፡፡ ለአምቦ ውሃ 10 ብር ከሚጠይቁኝ ለበርገሩ 40 ብር ቢጠይቁኝ ይሻለኛል፡፡ ቢያንስ እሱን እነርሱ ስለሰሩት ምን ያህል እንደሚያወጡበት አላውቅም፡፡ ቫት ከፋይ ቢሆኑ እንኳን አንድ ስድስተኛውን መንግስት ነው የቀማኝ ብዬ እንደተለመደው ቂሜን ቋጥሬ እወጣ ነበር፡፡ አሁን ግን የምቋጥረው ነገር አጣሁ - ገንዘቤንም ጭምር፡፡

ከአምስት ብር በታች ያስገቡትን አምቦ ውሃ ላቀረቡበት ብቻ ከእጥፍ በላይ ዋጋ ሲጠይቁኝ ተናደድኩ፡፡ ለነገሩ ጮክ ብዬ ከማማረር በላይ ማምጣት የምችለው ነገር ስላልነበረኝ ከፍዬ ወጣሁ፡፡ ስወጣ ታዲያ ከብስጭቴ በተጨማሪ ከኢሕአዴግጋ በመተባበር ነጋዴዎቹ የሚጨክኑብን ምን ሆነው ነው የሚል ጥያቄ ይዤ መውጣቴ አልቀረም፡፡

“በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት”
ነጋዴዎች እንደአርቲስቶቻችን ሁሉ ቀስበቀስ በመንግስታችን ሊግ ውስጥ ሳይጠቃለሉ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ ዋና ዋናዎቹ ነጋዴዎች ከተጠቃለሉ መቆየታቸውን ምስክር ራሳቸውን መጥራት እንችላለን (ሼሁ ‹‹]ኢሕአዴጎችን] እወዳቸዋለሁ! አራት ነጥብ›› እንዲሉ!) ቢሆንም እኮ ‹‹ልማታዊ›› መንግስታችን ‹‹ሕዝቤን እወዳለሁ›› እያለ በሚያወራበት በዚህ ዘመን እነሱ በጉሮሯችን እንዲህ መጨከናቸው ያስተዛዝባል፡፡

ብዙዎቹ ነጋዴዎች፡-  
  • ቫት እንዲያስከፍሉ ሲጠየቁ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር የዋጋ ማስተካከያ ነው፡፡ የዋጋ ማስተካከያው ለቫቱ የሚስማማ ዋጋ ማውጣት ዓላማው ቢሆንም ምርቃት ግን እንደሚጨምሩበት አትዘንጉ፡፡ (በርግጥ አንዳንድ ሊወደሱ የሚገባቸው ነጋዴዎችም እንዳሉ ይሰማኛል፤ ለምሳሌ የአራትኪሎው ማለዳ ካፌ ቫት ማስከፈል ሲጀምር ተጨማሪውን ቫት ከደንበኞቹጋ እኩል በመካፈል /በጥቅሉ ቢጨምርም/ የቀድሞ ዋጋው ላይ ቅናሽ ማድረጉ ሊያስወድሰው ይገባል፡፡ እሱ ካፌ በነገራችን ላይ፣ የእሁድ ጋዜጦችን እየገዛ ለደንበኞቹ በነፃ ማስነበቡም በራሱ ማንበብ ከሚከለክሉትም ከማይከለክሉትም ካፌዎች አንፃር ያስወድሰዋል፣ ያስወድደዋል፡፡)
  • አንድ ኪሎ ቅቤ 10 ብር ሲጨምር ምግብ ቤቶች የዋጋ ማስተካከያ የሚያደርጉት በአንድ ምግብ ላይ ቢያንስ አምስት ብር በመጨመር ነው፡፡ እኔ የምለው፣ አንድ ምግብ ግማሽ ኪሎ ቅቤ ይፈጃል እንዴ? አንድ ኪሎ ቡና 20 ብር ሲጨምርም ማኪያቶ ላይ 2 ብር ይጨምራሉ፡፡ ምን ለማለት ፈልገው ይሆን?
  • ከደንበኞቻቸው በሰበሰቡት ገንዘብ የግድግዳ ቀለማቸውን የሚቀይሩ ካፌዎችም ገና ለገና ቀለም ስለቀየሩ (ያውም እኛን የሚያስጠላንን ዓይነት ቀለም በመቀባታቸው) ሒሳብ ይጨምሩብናል፡፡ አሁን፣ አሁን የኔና የጓደኞቼ ስጋት የካፍቴሪያዎችና የምግብ ቤቶች እድሳት ነው - ዋጋ ጭማሪን ስለሚያስከትል፡፡
  • ስንቱን…?!


እናም የነጋዴዎቹን ነገር ስመለከት ‹‹የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አንተም አብረህ ዝረፍ›› የሚል ተረት ይመጣብኛል፡፡ እኛ በየዕለቱም ቢሆን እያማረርን የምንበላው፣ እንደነሱ ትርፋችንን በየዕለቱ መጨመር ስለምንችል እንዳልሆነ አይገባቸውም እንዴ? እኛ እኮ የምንበላው ሳንበላ መኖር ስለማንችል ነው፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እያለን የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፣ መጠጥና መጠለያ እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ሦስቱንም ማሟላት እንደማይቻል ስለገባን አንዱን ለሟሟላት እና ለሕዝብም ለመንግስትም በልተን እንደምናድር ለማስመስከር ካለን ‹‹ልማታዊ›› ፍላጎት በመነሳት (ብሎም ከሥራ ፍለጋና ከፌስቡክ ቻት የተረፈንን ጊዜ ለማሳለፊያ) ካፌ እና ሬስቶራንት ውስጥ ግማሽ ቀን ያህል ብንቆይ ጠላት መሰልናቸው እንዴ?

ስለዚህ ዋጋ መጨመርን እንደትርፍ ጊዜ መዝናኛ የምትጠቀሙበት ነጋዴዎቻችን፣ እባካችሁ በታኬታችሁ የምትረጋግጡት ሳር ሕይወቱን ለማዳን የእናንተን ትብብር እንደሚፈልግ ትዝ ይበላችሁ፡፡  

No comments:

Post a Comment