Pages

Tuesday, October 24, 2017

የምርጫ ስርዓቱ መሻሻል ጉዳይ

ብዙ ሰው ችላ ብሎታል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ግን "መደራደራቸውን" ቀጥለዋል። ከኢሕአዴግ ጋር እየተደራደሩ ያሉት ፓርቲዎች ምንም ሕዝባዊ ቅቡልነት/ውክልና የላቸውም ማለት ይቻላል። ለዚያ ነው "ድርድሩ" ጆሮ ያጣው። ዞሮ ዞሮ ኢሕአዴግ "ድርድሩን" ሲጠራ በተነሳበት ዓላማ ሊጠናቀቅ ተዳርሷል። የምርጫ ስርዓቱን ማሻሻል። ኢሕአዴግ ውጤቱን "በድርድር" የተገኘ ለማስመሰል ስለፈለገ እንጂ ቀድሞውንም ስርዓቱን ለማሻሻል ወስኗል። ለምን እና እንዴት?

፩) ቀዳሚ አሳላፊ (First Past The Post /FPTP) የተባለው የአሁኑ ስርዓት ድምፅ አባካኝ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት የምርጫ 2002 የአዲስ አበባ ውጤትን እናመጣለን። በወቅቱ ከመረጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ 54% ኢሕአዴግን መረጡ፣ 37% መድረክን መረጡ፣ 9% ሌሎች ተቃዋሚዎችን መረጡ። ነገር ግን ከአንድ ተቃዋሚ በስተቀር ፓርላማ ባለመግባቱ በጥቅሉ የ46% የአዲስ አበባ መራጮች ድምፅ ባክኖ ቀርቷል።

፪) ብዙ መራጭ ባላቸው የምርጫ ክልሎች ብዙ ድምፅ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ሲወድቁ፣ ትንሽ መራጭ ባለባቸው የምርጫ ክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች ባነሰ ድምፅ አልፈዋል። ለምሳሌ በዚያው የ2002 ምርጫ ወቅት በአንድ የምርጫ ክልል 42,555 ድምፅ ያገኙት የመድረክ ተወዳዳሪ አቶ ዑርጌሳ ዋኬኔ ፓርላማ አልገቡም፤ ነገር ግን በሌላ ምርጫ ክልል 12,753 ድምፅ ያገኙት የኢሕአዴግ ተወዳዳሪ ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሌ ፓርላማ ገብተው ነበር።

፫) የምርጫ ስርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና (proportional representation /PR/) ቢሆን ኖሮ ለአዲስ አበባ ከተተዉት 23 የምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ 12ቱ በኢሕአዴግ፣ 9ኙ በመድረክ እና ቀሪዎቹ ሁለቱ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ይሔዱ ነበር። (በዚያው በ2002ቱ ምርጫ)

ይሔ ቅሬታ ሲነሳ ሰንብቶ ነበር። ኢሕአዴግ ግን ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ወቅት ባገኘው ድምፅ መሠረት ስርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ቢሆንም ኖሮ ማለፉ አይቀርም ነበር። ምክንያቱም፣

ሀ) ከምርጫ 97 ወዲህ መራጩ ሕዝብ በምርጫው ስርዓት ዴሞክራሲያዊነት ተስፋ ቆርጧል። ለመምረጥ የሚሔዱትም ወይ የቀበሌ ባለሥልጣናትን የሚፈሩ ተቃዋሚዎች፣ ወይም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ወይም ጥቂት በምርጫ ፖለቲካ መቁረጥ ያቃታቸው መራጮች ብቻ ናቸው።

ለ) ኢሕአዴግ ምርጫው አንድ ዓመት ሲቀረው ገለልተኛ ሚዲያዎችን ከበፊቱ የበለጠ በማፈን ወይም በማገድ፣ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችን በማሰር፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመሰንጠቅ እና የመንግሥት ሚድያዎችን እና የመንግሥት ተቋማትን ለቅስቀሳ በመጠቀም ራሱን ብቸኛ ተወዳዳሪ አድርጎ ያቀርባል።

ሐ) ኢሕአዴግ ለታይታ ያክል ተቃዋሚ የፓርላማ አባል እንዲኖረው ቢፈልግም፣ በየምርጫ ክልሎች የሚያሠማራቸው ካድሬዎች በሙሉ በኋላ ላይ ላለመገምገም ሲሉ በራሳቸውን የምርጫ ክልል ኢሕአዴግን አሸናፊ ለማድረግ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዘዴ ተጠቅመው ያሸንፋሉ። 100% ውጤት የተገኘው በነዚህ ተንኮሎች እና ዘዴዎች ነው።

ስለዚህ (ሐ) ላይ የተጠቀሰው ችግር ሳይፈጠር (ካድሬዎቹ አሉታዊ ግምገማ ሳይቀርብባቸው) ተቃዋሚ ፓርላማ የማስገቢያው መንገድ የ"ተመጣጣኝ ውክልና" በመጠቀም መሆኑን ኢሕአዴግ ተረድቷል። ነገር ግን ደግሞ ድንገት የምርጫ 97 ዓይነት ነገር ተከስቶ በቀላል የተቃዋሚዎች ዳግማዊ መነቃቃት በተመጣጣኝ ውክልና የሚገኘው ውጤት የተቃዋሚዎቹን ድምፅ ድምር ከኢሕአዴግ ሊያስበልጠው እንደሚችል ያውቃል። ለዚህ ነው "ቅይጥ ትይዩ" (Mixed-Parallel) የሚባል የስርዓት ማሻሻያ ይዞ የመጣው።

በጣም የሚያሳዝነው ተቃዋሚዎች "ቅይጥ ትይዩ" የተባለው የምርጫ ስርዓት ምን ዓይነት እንደሆነ አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ እንዲያስረዳቸው መጠየቃቸውም ጭምር ነው።

በተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት ከግል ተወዳዳሪዎች ውጪ ፓርቲዎችን ወክለው የሚቀርቡ ግለሰቦች አይኖሩም። ፓርቲዎቹ ባገኙት ውጤት ልክ ነው ለወንበሮቹ ሰው የሚመድቡት። ቅይጥ ትይዩ የተባለው ስርዓት የተወሰኑ ወንበሮች በቅድሚያ አላፊ ስርዓት፣ የተወሰኑ ወንበሮች ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና የሚገኝበት እና ሁለቱንም የምርጫ ስርዓቶች ጎን ለጎን ማስኬድ የሚቻልበት ስርዓት ነው። ይህ የምርጫ ስርዓት አንድ ፓርቲ ለረዥም ዓመታት የገዛባቸው አገሮች የተከተሉት ስርዓት ነው። በተለይ የምርጫ ክልሎቹን በደጋፊዎቹ አሰፋፈር ማወቀር (gerrymandering) የቻለ ፓርቲ ዘላለም አሸናፊ  የሚሆንበት ስርዓት ነው።

ተቃዋሚዎቹ ስለተጠቆመው የምርጫ ስርዓት ኢሕአዴግ ካብራራላቸው በኋላ ነው "መደራደራቸውን" የቀጠሉት። አሁን 11 ፓርቲዎችን ያቀፈው ቡድን 60:40 (ማለትም 60% ቀዳሚ የሚያልፍበት፣ 40% ተመጣጣኝ ውክልና) እንዲሆን "የመደራደሪያ" ምጥጥን በማቅረብ "ቅይጥ ትይዩ" ስርዓትን ተቀብለዋል።

በበኩሌ፣ ትክክለኛው "ሕዝባዊ ስርዓት" የሚለካው በምርጫው ውጤት ሳይሆን በምርጫዎች መካከል ባለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይህ ደግሞ ያለ ሲቪል ማኅበራት፣ ያለ ገለልተኛ ብዙኃን መገናኛና ለሕዝብ ወገንተኛ የሆኑ ተቋማት በሌሉበት ይሳካል ብዬ አላምንም። ሆኖም፣ የምርጫ ስርዓቱም ቀላል ቁም ነገር ነው ብዬ አላስብም። ስለዚህ፣ ለእንደኛ ዓይነቱ አገር ድምፅ አባካኙ ቀድሞ አላፊ ስርዓት አዋጭ ነው ብዬ አላምንም። የተሻለው ተመጣጣኝ ውክልና ነበር። ይህ ግን ቀድሞም የይስሙላ በተባለው ድርድር፣ በፓርቲዎች አላዋቂነት ሳቢያ የማይሆን ሆኗል። ኢሕአዴግ በራሱ ፍላጎት የጀመረውን ድርድር እንደፍላጎቱ እየጨረሰው ነው።

Sunday, October 15, 2017

የባንዲራ ማኒፌስቶ!

ልጅ እያለን፣ ታላላቆቻችን እኛን እርስበርስ እያደባደቡ ሲዝናኑብን እንዲህ ያደርጉ ነበር። ምራቃቸውን መሬት ላይ ሁለት ቦታ ላይ እንትፍ እንትፍ ይሉና፣ "ይቺኛዋ ያንተ እናት፣ ያቺኛዋ ደግሞ ያንተ እናት ናት" ይሉናል። ከዚያም "ማነው የማንን እናት የሚረግጠው?" ሲሉ፣ አንዱ ቀድሞ የሌላኛውን "እናት" (በትፋት የራሰውን አፈር) ከረገጠ ድብድቡ ይጀመራል። የተተፋበትን አፈር የረገጠውን ልጅ ዝም ማለት፣ እናትን አስረግጦ ዝም እንደማለት ነበር የሚቆጠረው። የውርደት፣ የሽንፈት ስሜት አለው። በልጅነት ዐሳባችን የእናታችንን ትዕምርታዊ መገለጫ ማስደፈር እናታችንን ከማስደፈር ዕኩል ስለሚሰማን ወትሮ ከማንደፍረው ሰው ጋር ሳይቀር እንጋጫለን።

የባንዲራ ትዕምርትም እንደዚሁ ነው። ሰንደቅ ዓላማ የአገርና የአገራዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ ትዕምርት (‘ሲምቦል’) ነው። ሁለት አገራት ወደጠብ ሲገቡ በሕዝባዊ ተቃውሞ ሰልፎች ላይ ባንዲራ ማቃጠል፣ በፊት በፊት ፋሽን ነበር። አሁንም ድረስ ባንዲራ የማቃጠል ተቃውሞ አለ።

የባንዲራ ትዕምርታዊነት ሰፊ በመሆኑ ቬክሲሎሎጂ የሚል የጥናት ዘርፍ ተቋቁሞለታል። በባንዲራ መከባበርም፣ መናናቅም ይገለጻል። ሕዝባዊ ሐዘን ይገለጽበታል። ደስታ ይበሰርበታል። የአገር ፍቅር ልክ ይመዘንበታል።

“ከብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን” ባሻገር!

አቶ መለስ "ባንዲራ ጨርቅ ነው” ብለው ሲናገሩ የሳቱት ጉዳይ ይህንን ትዕምርታዊ ውክልናውን ነው። በርግጥ ይህንን አሉ በተባለበት ወቅት አገሪቱ ከአንድ ይፋዊ ሰንደቅ ዓላማ ወደ በርካታ ባንዲራዎች እየተሸጋገረች ስለነበር፣ "ባንዲራ ጨርቅ" ብቻ ከሆነ ያንን ሁሉ ለውጥ ለምን ማድረግ እንዳስፈለጋቸው መጠየቅ ነበረባቸው። አቶ መለስ ይህንን ብዙ ሕዝብ የሚያስከፋ ‘የአፍ ወለምታ’ የባንዲራ ቀን እንዲከበር በማድረግ ነው ለማረም የሞከሩት። የመጀመሪያውን ክብረ በዓልም ራሳቸው ባንዲራ እየሰቀሉ ነው ያስጀመሩት። ነገር ግን ንግግራቸው እስከዛሬም በአሉታዊ ሚና ይጠቀስባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ - ባንዲራ በኢትዮጵያ፣ በፊት በፊት የአንድነት መገለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ማንፀባረቂያ (ማኒፌስቶ) ሆኗል። በኢትዮጵያውያን የሚውለበለቡት የባንዲራዎች ብዛት የፖለቲካ አመለካከታችንን ያክላል። ልሙጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ እንዲሁም ባለኮከቡ። አልፎ አልፎ ባለ ‘ሞኣ አንበሳውም’ አለ። የገዳው ጥቁር፣ ቀይና ነጭ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልሉ ጥቁር፣ ነጭና እና ቀይ (መሐሉ ላይ ዛፍ)። የኦነጉም ባንዲራ አለ። እነዚህ አነታራኪዎቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ በ2003 የተሻሻለው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ከወጣ ወዲህ (ሌሎቹ ባይጠቀሱም) ቢያንስ ‘ኮከብ የሌለውን’ ባንዲራ ማውለብለብ ተከልክሏል (ለብሶ መታየትን ግን የሚከለክል ሕግ አላየሁም። ቢሆንም አገር ውስጥ ከላይ የጠቀስኳቸውን ባንዲራዎች ይዞ ወይም ለብሶ መገኘት ለቅጣት ወይም እንግልት ይዳርጋል።) ነገር ግን በዳያስፖራ  የተቃውሞ ሰልፎች ላይ እንደየሰልፉ ዓይነት - በተለይ ሁለቱ (‘የኦነግ’ የሚባለውና ልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ) ባንዲራዎች የማይቀሩ ናቸው። አሁን አሁን፣ በተለይ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ከሕወሓት ጋር ትከሻ መለካካት ጀምረዋል ከተባለ በኋላ ሕዝባዊ ሠልፎች ላይ ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸውን ባንዲራዎችን ማውለብለብ እዚህም ተለምዷል።

እንደምን በአንድ ባንዲራ እንኳ መስማማት ተሳነን?

Friday, October 6, 2017

የአማራ ብሔርተኝነት እንቆቅልሽ (የመቋጫ መጣጥፍ)

"የአማራ ሥነ ልቦና" በሚል ርዕስ ቀደም ሲል የጻፍከት አጭር የእንግሊዝኛ መጣጥፍ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል። የጽሑፉ ዋነኛ ዓላማ ስለአማርኛ ቋንቋ ዕድሜ፣ ወይም ስለአማራ ሕዝብ ኅልውና ባይሆንም፣ ብዙዎቹ አንባቢዎች ግን የተረዱት በዚያ መንገድ ነበር። ወሳኙ ቁም ነገር እኔ የጻፍኩበት ዓላማ ሳይሆን አንባቢ ጋር ሲደርስ የሰጠው ስሜት ስለሆነ ይህንን ጽሑፍ አስከትያለሁ።

በመሠረቱ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት፣ እኔ የምፈልገው ዘውግ-ዘለል የዜግነት ብሔርተኝነት (civic nationalism) ነው፡፡ ይህን ስል ግን የዘውግ ብሔርተኝነትን እና በዘውግ መደራጀትን እቃወማለሁ ማለቴ አይደለም፤ በዘውግ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች እስካሉ ድረስ ያንን በመከልከል ማስቆም ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የዘውግ ቡድኖችን እና ፍላጎቶቻቸውን አቻችሎ በአንድ ለማኖር የዜግነት ብሔርተኝነት ማበበ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በዘውግ ስለተዋቀሩ እና የመንግሥታዊ አደረጃጀቱም ይህንን (ለዜግነት መብቶች በርዕዮተዓለም መደራጀት) ምቹ ሁኔታ ስላልፈጠረለት አገሪቷ የፉክክር ቤት ሆናለች። ስለሆነም፣ ይሔ እና መሰል ጽሑፎች፣ በአገራችን የተንሰራፋው በአሁኑ ወቅት የበለጠ ተቀባይነት ያለው የዘውግ ብሔርተኝነቱ አካሔድ ቢያንስ ወደፊት ወደ ዜግነት ብሔርተኝነትን እንዲያድርግ የማደርገው ጥረት አካል እንደሆነ ይታወቅልኝ።

አሁንም ከዚህ በፊት "የተጣመመ የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ" በሚል የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጆች ላይ አስተዋልኩት ብዬ የጠቃቀስኩት የጠራ ዘር እና የዘር ሐረግ በመቁጠር ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነት አዝማሚያ “ገና አፍላ ነው” በሚባለው የአማራ ብሔርተኝነት ላይም በጉልህ ያስተዋልኩ መሆኑ የጽሑፌ ዋና መነሻ ነው፡፡ የጠራ ዘር ፍለጋ እና የዘር ቆጠራ ፍልስፍና፣ ዘውግ ወይም ብሔርተኝነት ማኅበራዊ ሥሪት መሆኑን ክዶ በደም የሚወረስ ከማስመሰሉም በተጨማሪ፣ መሠረታዊ መብቶችን ለመጣስ ሰበብ ሆኖ ሊመጣ ይችላል።

ዶ/ር አድማሱ ከበደ ‹የአማራ ብሔርተኝነት ከተለመደው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የተለየ መንስዔ ይዞ ነው የተነሳው› በማለት ሲተነትኑ፣ ‹ከአማራ ብሔራዊ መነቃቃት አስቀድመው ብሔራዊ መነቃቃት ያገኙት ሌሎች የኢትዮጵያ የዘውግ ቡድኖች እንደሌላ ስለቆጠሩት (othering) የተፈጠረ ብሔርተኝነት ነው› ብለው ጽፈዋል::

በዚህ ግንዛቤ በታሪክ አማራ ማነው? አማርኛስ የማነው? እና የአማርኛ የዝግታ ዕድገት ዛሬ አማራ ስለምንለው ሕዝብ ‹ሌላነት› የሚነግረን ነገር አለ? የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳትና መልስ በመፈለግ የአማራ ብሔራዊ (የዘውግ ማንነት) መሠረቶች ምንነት ላይ መላምት አሳልፋለሁ። ይህም የአማራ ብሔርተኝነት ከዜግነት ብሔርተኝነት ጋር በመርሕ የማይጋጭ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የውይይት ዕድል በመስጠት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እምነት አለኝ።