Pages

Wednesday, April 19, 2017

‘ኢትዮጵያዊ ርስበርስ መባላቱን፥ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?’

ትላንት
     ነብይ ባገሩ አይከበርም
ዛሬ
     ነብይ ባገሩ አይኖርም
ነገ
     ነብይ ባገሩ አይፈጠርም
(በዕውቀቱ ሥዩም)

ፌስቡክ የትውልዳችን ማንነት ገመና ገላጭ ነው። የመግቢያዬ ግጥም ገጣሚ፣ በትውልድ ፈርጥነቱ ሊወደስ ሲገባው፥ የሚናገረውን እንኳ በማያውቅ መደዴ ሲዘለፍ መዋል የጀመረው ፌስቡክ ላይ ከወጣ ወዲህ ነው። ነገሩ የኛ ትውልድ፣ የፌስቡክ መንደር ድክመት ብቻ ነው ብዬ ባምንና ባልፈው ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን እንደጨጓራ ራሱን የበላው 'ያ ትውልድ'ም፣ የ'ያ ትውልድ' አሳዳጊም፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያው ሆኖ መሰለኝና ብዕሬን ለቁዘማ መዘዝኩ።

አሁን ኢትዮጵያ 'ፈላስፋ' ነበራት ለማለት የምናጣቅሰው፣ ፈረንጆቹ "ኢትዮጵያዊ አይደለም" ሲሉ 'ዘራፍ' ብለን የምንሟገትለት ዘርዐ ያዕቆብ፣ በሐሳቡ ምክንያት ከትውልድ አገሩ አኵሱም ተሰዷል፣ ለማኝ ሆኖ ዋሻ ውስጥ ኖሯል፣ ጎንደር ዘልቆ ራሱን ቀይሮ ዕድሜውን ለመጨረስ ተገዷል። እርግጥ ነው ይህ መልካም ሰው የማሳደድ አባዜ የዓለም አባዜ ነበር። ይሁን እንጂ አባዜው ዛሬ ለቀሪው ዓለም 'ነበር' ሲሆን ለኛ ግን 'ነው' ሆኖ ዘልቋል። የግሪኩ ሶቅራጠስ፣ አፍላጦንን፣ አፍላጦን አሪስጣጣሊስን… እየተኩ ሲያልፉ የእኛዎቹ ዘርዐ ያዕቆብ እና ወራሹ ወልደ ሕይወት በወላድ አገር ምትክ አጥተው መካን ሆነው ቆመዋል። ከዓለም በከፋ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሐሳብ ይዞ መምጣት በንጉሡም፣ በጳጳሱም፣ በምዕመኑም ያስቀጣል(ነበር)። ልዩነቱ ይኼ ነው።

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጊዜ ለንጉሥ አንሰግድም ያሉት አባ እስጢፋኖስ እና ደቂቆቻቸው ዕጣ ፈንታ መስዋዕትነት ነበር። በየዘመኑ የተለዩትን፣ የተሻሉትን ስንገድል ነው የኖርነው። እንደካሮት ቁልቁል የማደጋችንም ምሥጢር ይኸው ይመስለኛል። ዐፄ ዮሓንስ ፬ኛ በሐሳብ ልዕልና እንደሚያምን ሰው ታሪካዊውን የቦሩ ሜዳ የሊቃውንት ሙግት ካሰናዱ በኋላ አሸናፊውን ራሳቸው ቀድመው የሚደግፉትን ቡድን አድርገው ሲያበቁ፣ ፍርዳቸው የተቃወመውን ሁሉ ምላሱን እዚያው አስቆርጠዋል።