Pages

Monday, January 20, 2020

#ምርጫ2012: እነማን ያሸንፋሉ?

#EthioElection2020: What to Expect When You're Expecting Ethiopian Election!

ወቅቱን የጠበቀ፣ ፉክክር ያለበት፣ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ጎጆ ውስጥ የመሐል ዋልታ ነው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ ማለት በየአራት፣ አምስት ዓመቱ የሚመጣ ምርጫ ብቻ አይደለም፤ በኹለት ምርጫዎች መካከል ያለ የዜጎች ተሳትፎም የሚረጋገጥበት ስርዓት ነው። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አይደለም የሚባለው። ነገር ግን በምርጫ መካከል የዜጎች ተሳትፎ (በተለይም በነጻ ሚዲያ እና ሲቪል ድርጅቶች አማካይነት የሚደረግ የዜጎች ተሳትፎ) የሌለው ዴሞክራሲ የይስሙላ ዴሞክራሲ ነው። ወቅቱን የጠበቀ (periodic) ምርጫ የሌለው ዴሞክራሲ ግን ከናካቴው የይስሙላ ዴሞክራሲ እንኳን ሊባል አይችልም። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አዋጭ ስርዓት ነው ብለን የምናምን ሰዎች፥ በጥቅሉ ምርጫን፣ በተለይ ደግሞ የዘንድሮውን የኢትዮጵያን ምርጫ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና የወል ትብብር መከታተልና ማድረግ የሚኖርብን። 

ባለፉት ኹለት ዓመታት የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ወዲህ የተዘጋውን የፖለቲካ ምኅዳር ለመክፈት ከበፊቱ የተሻለ ተነሳሽነት ታይቷል። የሲቪክ እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ያጠበቡትን ሕጋዊ ማዕቀቦችን ለማሻሻል ጥሩ የሚባል ጥረት ተደርጓል። የመንግሥት ተቋማትን ተአማኒ እና "ነጻ" ለማድረግ ቃል ተገብቷል፣ ጥቂት የተቋማት ጥገናዊ ለውጥም ተደርጓል። ይኼ ሁሉ የተሐድሶ ሙከራ ግን በፉክክር በደመቀ፣ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ካልታጀበ "እቃቃው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ" መሆኑ ነው። 

First Things First
ምርጫ ቦርድ ይታመናል?

ይኼንን ጥያቄ ለመመለስ ነገሩን ከበርካታ አቅጣጫዎች መመልከት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ተአማኒ መኾን ያልቻለበትን ምክንያት እናስታውስ። ዋነኛው ምክንያት የገዢው ፓርቲ መሣሪያ በመሆኑ ነው። 

ምርጫ ቦርድ የገዢው ፓርቲ መሣሪያ ነበር ስንል ከመገለጫዎቹ አንዱ የፓርቲዎችን ጠብ የሚገላግልበት መንገድ ነበር። በተለይ ትልልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጣዊ ውዝግብ ሲኖራቸው (አንዳንዶች እንዲያውም የውዝግቡ ለኳሾች ራሱ ገዢው ፓርቲ አስርጎ የሚያስገባቸው ሰዎች ናቸው ብለው ያምናሉ)፣ የመፍትሔ ውሳኔው ብዙ ጊዜ ፓርቲዎቹን የሚያሽመደምድና የተፎካካሪነት ቁመና የሚያሳጣ ነበር። በሌላ በኩል፣ ትልልቆቹን ፓርቲዎች ለመሰንጠቅ ካለው ቁርጠኝነት ውጪ ትንንሾቹን እና ሕጋዊ መሥፈርቶችን የማያሟሉ የይስሙላ ፓርቲዎችን ዕውቅና ሰጥቶ እያባበለ ማቆየቱ ደግሞ ሌላው የቦርዱ ሐሳዊነት መገለጫ ነበር። በአጭሩ ገዢው ፓርቲን እንደ ቤተኛ፣ ለአቅመ ፉክክር የደረሱትን ተቃዋሚዎች ደግሞ እንደ ባዕድ ሲያስተናግድ ከርሟል። ከዚህ በተረፈ ያለው ምርጫ ቦርድን አያገባውም፤ ኢሕአዴግ ሌላውን የጫወታ ሜዳ (ሚዲያዎችን እና ሲቪል ድርጅቶችን በማዳከም ወይም ወደ ራሱ ተለጣፊ በማድረግ ሜዳውን) እንዲያጋድል በማድረግ ራሱ ተጫውቶ፣ ራሱ ሲያሸንፍ ከርሟል።