Skip to main content

ጨርቆስና ቦሌ - ሕይወትን እኛ እንደኖርነው!


ጨርቆስና ቦሌን ምን አገናኛቸው? በርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም ጨርቆስና ቦሌ ተለያይተው አያውቁም - በቀልድም በድንበርም፡፡ በኑሮ መቀለድ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የኑሮአችን አካል ነው፡፡ የጨርቆስ እና የቦሌ ጉርብትናም በኢትዮጵያ እየሰፋ ለመጣው የኑሮ ደረጃ ልዩነት በርካታ አዳዲስ ቀልዶችን አበርክቷል፡፡ ምንም እንኳን የጫወታዬ ዓላማ ቀልዶቹን ለአደባባይ ማብቃት ባይሆንም አንድ ስሜቴን የነካ ቀልድ ግን ሳላስታውስ ማለፍ አይቻለኝም፡፡ ቀልዱ የተነገረው ወንድማማቾቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ መንግስታችን በወቅቱ ‹‹ፈንጂ ማክሸፊያ›› ወጣቶች ያስፈልጉት ነበርና‹ወዶ ዘማች› የሚለው ቃል ወረት ሆኖ ነበር፡፡ እናም የሃገራቸው መወረር ያስቆጣቸው የቦሌ ልጆች ገንዘብ አዋጥተው ለጨርቆስ ሰፈር ‹ወዶ ዘማቾች› ደሞዝ እንዲከፈል አበረከቱ ተብሎ ተቀለደ፡፡

ከዚህ ቀልድ በኋላ ግን አንድ ጥያቄ በጭንቅላቴ ሲጉላላ ከረመ፡፡ ‹‹የሃብታምና የድሃ ሕይወት የዋጋ ልዩነት ስንት ነው?››

ደግነቱ - ጥያቄው መልስ የለውም፡፡ ሃብታም በእምነበረድ ያስነጠፈውን ወለል ብርድ ለመቆጣጠር የስጋጃ ምንጣፍ ይደርብበታል፤ ድሃ ደግሞ መንግስት ለእግረኛ ያስነጠፈውን አስፋልት (ለምቾቱ መርጦና) አቧራውን እፍ ብሎ ይተኛል፡፡ ይህ የሕይወት መልክ ነው፡፡ የሕይወት ዋጋ ልዩነቱም እንዲያ ነው - የጨርቆስና የቦሌ፡፡

ከሰሞኑ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ሰሞነኛ አባባል ግን መልስ ባትሰጥም ታፅናናለች - ድሃም ተኩኖ ይኖራል፣ ሃምታምም ተኩኖ ይሞታል፡፡

በሃገራችን ያለውን የሃብት ልዩነት መገመት እንጂ በፐርሰንት አሰልቶ መናገር ከባድ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ በድሃ ሰፈር (ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ) ተወልጄ ያደግኩ ‹የድሃ ልጅ› እንደመሆኔ - ለምሳሌ ያክል -የሃብታም ልጆች ምንና እንዴት እንደሚያስቡ የገባኝ (ያውም ከገባኝ!)  የልጅነት እድሜዬን ከጨረስኩ በኋላ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ የሃብት መጠን ልዩነታችን የአኗኗር ዘያችንን እንዴት እንዳለያየው በደንብ የገባኝ ሰሞን የደነገጥኩት ድንጋጤ እስከዛሬም አልለቀቀኝ፡፡

ሃብታም ስለ ድሃ
የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ ተማሪ እያለሁ የተማሪዎች የቤት ለቤት አስጠኚ በመሆን ኪሴን እደጉም ነበር፡፡ ከተማሪዎቼ አንዱ የቅዱስ ዮሴፍ የወንዶች ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ቤቱ ቦሌ አካባቢ ነበር፡፡ ወላጆቹ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት በመኪና ያመላልሱታል፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቹም፣ ጎረቤቶቹም ከሱ የተለየ ሕይወት የላቸውም፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በጥናታችን መሃል አስደንጋጭ ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡

ጥያቄውን ያቀረበው ለአኩያ ጓደኞቹ ቢሆን ምንም አስደንጋጭ ባልሆነም ነበር፤ ይሁንና የጠየቀው እኔን ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንድም ተማሪ በመኪና ተሸኝቶ በማይመጣበት ትምህርት ቤት የተማርኩ፣ እርሳስ ሲያልቅብኝ የቀጣዩ ወር ደሞዝ እስኪመጣ ድረስ እኩለ ቀን ላይ ከትምህርት ቤት ከምትወጣው እህቴ ጋር የምዋዋስ፣ ከተጣጣንም ከአስተማሪዬ እየተደበቅኩ ወሩን በመግፋት የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩ በመሆኔ ‹ለካ እንደዚህም የሚያስቡ ልጆች አሉ!› ብዬ ደነገጥኩ፤ ተገረምኩ፡፡

‹‹አዲስ አበባ ውስጥ መኪና የሌለው ሰው አለ እንዴ?›› ብሎ ነበር የጠየቀኝ ተማሪዬ፡፡ መጀመሪያ ላይ ጥያቄው አበሳጭቶኝ ነበር፤ ኋላ ላይ ሳስበው ግን እኔ የሱን ኑሮ በቅጡ ባለማወቄ እሱ መቼ ተበሳጭቶብኝ ያውቃል ብዬ ብስጭቴን ተውኩት፡፡ እሱ የሚያውቀው ሕይወት የቦሌ ነው፣ ከቦሌ ባሻገር ያለውን ሕይወት በምን ይረዳዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ድሃ ነች›› ብሎ መናገር የኢትዮጵያ ድህነት ምን ያህል እንደሆነ ትክክለኛ ምስል መስጠት እንደማይቻለው በማሰብ የተማሪዬን ጥያቄ ከራሴ የቀድሞ ውስጣዊ ጥያቄ ጋር አመሳሰልኩት፡፡

ድሃ ስለሃብታም
በፊት፣ በፊት አሸንዳ/ጎረንዳዮ የተባለ ሥራ እሰራ ነበር፡፡ ለሁኔታዎች በጣም ከመላመዴ በፊት ለመስሪያ ቤት ደምበኞቼ የሚሰራውን ሥራ ዋጋ ተመን መናገር ያስበረግገኝ ነበር፡፡ ያስፈራኝ የነበረው ግን ለደምበኞቼ የምነግራቸውን ዋጋ እኔ ካደግኩበት ዋጋ አንፃር እመለከተው ስለነበር ነው፡፡ የሚገርመው ግን የአብዛኞቹ ደምበኞች ምላሽ ነበር፡፡ ‹‹አንተ ሥራውን ጥሩ አድርገህ ሥራው እንጂ ዋጋው አያጣላንም፡፡ እንዲያውም ጉርሻ ይኖርሃል›› ይሉኛል፡፡ (እኔ የማውቀው እናቴ ያን ያህል ብር ክፈይ ብትባል ስቅስቅ ብላ እንደምታለቅስ ነው፡፡) እኔን ለመናገር የሚያሸማቅቀኝ ዋጋ ለነሱ ምናቸውም አይደል - የጨርቆስና የቦሌ ነው ጉዳዩ፡፡

ሰው ያልኖረውን ኑሮ በስም እንጂ በመልክ አያውቀውም፡፡ በራሴ እና በዙሪያዬ ካሉ ሰዎች አመለካከት እንኳን በመነሳት ብቻ ስለኢትዮጵያ ድህነት የምናስበውም ከእንጦጦ ተራራ ሳንዘል ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን በኋላ ቀር ግብርና የሚተዳደሩ፣ ለመብራትና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ያልታደሉ፣ የመንገድና የመገናኛ አማራጭ የሌላቸው ስለመሆኑ ዘልቆ የሚገባን እንዴት ነው?

እስኪ ጨዋታዬን ጠምዘዝ ላድርገውና ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከጫካ ትግል ወጥተው የቤተ መንግስትን ሕይወት ከጀመሩ ሁለት ዓሥርት ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡ በዓመታት ከደበዘዘው የችግር ዘመናቸው ትዝታ ውስጥ የኢትዮጵያን ድህነት ከቁጥር በዘለለ ወይም ከነስሜቱ የሚረዳ አቅም ይኖራቸው ይሆን? ይህንን ያለነገር አላነሳሁትም፡፡ ይልቁንም በየጊዜው ለኑሮ ውድነት፣ ለኃይል እጥረት እና ለሌሎችም እንደምክንያት የኢኮኖሚያችን እና የፍላጎታችን መጨመር መሆኑን መናገራቸው የኛም የአኗኗር ከሳቸው የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተለወጠ መስሏቸው እንደሆነ ብዬ ነው፡፡

በነገራችን ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (አባታቸው እንደተናገሩት) ‹‹የመቶ እና የሃምሳ ብር ኖቶችን ለይተው አያውቋቸውም፡፡›› እሳቸው ምን አለባቸው፤ ለ20 ዓመታት ጤፍና በርበሬ አልገዙ፣ የቤት ኪራይ አልከፈሉ፣ ሱሪና ቀሚስ አልገዙ፣ የትምህርት ቤት አልከፈሉ፣ በታክሲ አልተሳፈሩ፣ ነዳጅ አልገዙ፣ በርገር አልበሉ፣ የት ሒሳብ ሲከፍሉ ያውቁታል?

ያልኖሩበትን ኑሮ መገመት ይከብዳል፡፡

የጫወታዬን ርዕስ ‹ጨርቆስና ቦሌ› ብዬ መሰየሜ የሚያስቆጣችሁ ሰዎች ካላችሁ፤ ይቅርታ አልጠይቃችሁም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ጨርቆስና ቦሌ የሚወክሉት እኛ በዚህ ስም የምናውቃቸውን ተጎራባች መንደሮች ሳይሆን ተቀራርበው ግን ሳይተዋወቁ የሚኖሩትን ብዙ ድሆችና ጥቂት ሃብታም ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልዩነት በየትኛውም ዓለም ያለ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ልዩነቱን ለማጥበብ የታደሉ ብዙ ሃገራት ግን ይገኛሉ፡፡

ለመደምደም ያክልም ዛሬ ይህንን ልዩነት ያወራሁባችሁ አዲስ ነገር ነው ብዬ፣ ወይም ልዩነቱን ለማጥበብ የሚያስችል ‹‹ፖለቲካዊ አማራጭ›› ይዤላችሁ አይደለም፡፡ እንዲያው ተገርሜ ላስገርማችሁ ብዬ እንጂ!

Comments

  1. ደስ የሚል ጽሑፍ ነው፡፡ የልጁ ጥያቄ አስቆኛል፤ አንተም ያልሰራኸው ስራ አለመኖሩ ገርሞኛል፡፡ ታዲያ ጨዋታህን ወደ ራሴ እንዲህ ተረጎምኩት፡፡… እኔ እዚህ ሀገር ደኃ የጨርቆስ ልጅ ነኝ፡፡ ከነጓዜ እና ደሞዜ ኢትዬጵያ ብመጣ ግን (አልችልም እንጂ) ዕጣ ክፍሌ ከቦሌ ልጆች ጋር ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ እሳቤ ታዲያ ኢትዬጵያ ራሷ ‹ጨርቆሴ› ትሆንና፤ አሜሪካ ደግሞ ‹ቦሌ› ይሆናል ማለት ነው፡፡ ድህነት አንጻራዊ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ትልቁ እና እውነተኛው ድህነት ግን፤ አንተ እንደጠቆምከው፤ ሁሌም እንደምትጠቁመው፤ የመሪ ድህነት፤ የፖሊሲ ድህነት፤ የአስተሳሰብ ድህነት ነው፡፡

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...