“Occupy Wall Street” በሚል መፈክር አንድ በመቶ የሚሆኑ ባለፀጎች የሚመሩትን የኢኮኖሚ ፖለቲካ 99 በመቶዎቹ ሊንዱት እየተፍጨረጨሩ ባለበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ In Time የተሰኘ ፊልም ወጥቷል፡፡ ፊልሙ ጊዜን መገበያያ ገንዘብ አድርጎ አምጥቶታል፡፡ መገበያያ ብቻ ግን አይደለም፤ ሕይወትም ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ያለው ሰው ሃብታም፣ ትንሽ ጊዜ ያለው ሰው ደግሞ ድሃ ነው፡፡ ድሃው ቶሎ ይሞታል፣ ሃብታሙ ግን ዘላለም የመኖርም ዕድል አለው - በስህተት ካልሞተ፡፡
የፊልሙ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሃብታቸውና ሕይወታቸው (ጊዜ) እጃቸው ላይ ታትሞ/በተፈጥሮ መሆኑ ነው/ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ማኪያቶ ለመጠጣት 5 ደቂቃ ሲከፍሉ፣ መኪና ለመግዛት ደግሞ ዓመታትን ያወጣሉ፡፡ ስጦታ ይሰጣጣሉ፣ ይሰራረቃሉ፣ ያተርፋሉ ይከስራሉ፡፡ ብዙዎቹ ድሆች ከሰዓታት የበለጠ ስለሌላቸው ሕይወታቸውን ለማሳደር ሲሉ ይዋከባሉ፡፡ ሃብታሞቹ ደግሞ ከእጃቸው ተርፎ ማዕከላዊ ቁጥጥር ሲስተም ውስጥ የሚያጠራቅሙት ዓመታት አላቸው፡፡
በፊልሙ ውስጥ ፖሊስ - ጊዜ ጠባቂ፣ ድንበር - የጊዜ ዞን፣ ባንክ - የጊዜ ማበደሪያ በመባል ይታወቃል፡፡
In Time ሊያስተላልፍ የሞከረው ነገር ሃብታሞች ብዙ ገንዘብ ባካበቱ ቁጥር የሚያካብቱት ከድሃው የተቆነጣጠረ መሆኑን ነው፡፡ ገንዘብ ዕድሜን ቢቀጥል ኖሮ (በርግጥም ይቀጥላል) እነርሱ እየኖሩ ድሃው ይሞታል እንደማለትም ነው፡፡ የፊልሙ ዋና ገፀ ባሕርይ (ጀስቲን ቲምበርሌክ ይተውነዋል) ጊዜን ከሃብታሞቹ እየዘረፈ ለድሆቹ ሲያከፋፍል ይታያል፡፡ ነገርዬው ሶሺያሊዝም ይመስላል፡፡ ዘመናችን ሶሺያሊዝምን እየናፈቀ ይሆን የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ነፃ ገበያ ብሎ ነገር አበቃለት ይሆን?



