Pages

Tuesday, October 11, 2011

ኢትዮጵያውያን ለምን ዲቪ አይሞሉ?

From Addis Ababa, Ethiopia
ባለፈው ዓመት በዚህ ሰሞን ዲቪ ለኢትዮጵያውያን ስሞታ ይስ ስጦታ? የሚል መጣጥፍ ጽፌ ነበር፡፡ በዚያ ጽሁፍ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን ልባቸው ከሃገራቸው ውጪ ነው በማለት በማሕበረሰቡ የቁም ቅዠት፣ በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ፈርጄ ‹‹ኢትዮጵያውያንን እንደበረሃ አሸዋ ከተበተኑበት የሚሰበስባቸው ማን/ምን ይሆን?›› የሚል ጥያቄ አስፍሬ ነበር የደመደምኩት፡፡

የስደት እና የዲቪ ጉዳይ ዛሬም ስላላባራ (በቅርቡ የሚያቧራም ስለማይመስል) በዚህ ሐሳብ ዙሪያ አሁንም እንድጽፍ የሚጎተጉተኝ ስሜት አላጣሁም፡፡ በዚያኛው ጽሁፍ ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ ብልም ከዓመት በኋላ ተገቢ ሁኖ ያገኘሁት ጥያቄ ግን ‘ለምን አይሰደዱ?’ የሚለውን ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ ለሚለው ጥያቄ በርካታ መልሶችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ዋና፣ ዋናዎቹ ምክንያቶች ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ፖለቲካዊ ነፃነት ማጣትና የተሻለ ትምህርት ፍለጋ ናቸው፡፡ ከተማሩ በኋላ መመለስ ልምድ ባይሆንም፡፡ (አወይ የዋህነት! ከተማሩ በኋላ መመለስ ቀርቶ፤ ለሴሚናር፣ ለዎርክሾፕ፣ ለዘገባ ወይም ለጉብኝት ሄዶ መመለስስ የታለና?!)


ነገር ግን ኢሚግሬሽን በር ላይ ከሚኮለኮሉ ሰዎች መካከል ወደውጭ ሃገራት የሚሔዱበት ምክንያት ከሦስቱ የትኛውን እንደሆነ ብንጠይቅ ለመጀመሪያው እጃቸውን የሚሰጡ እልፍ እንደሚሆኑ ለመገመት ጠቢብ መሆን አያስፈልግም፡፡

መንግስት ኢኮኖሚው እየተመነደገ እንደሆነ በሚደሰኩርበት ጊዜ የዕለት ጉርሻን ማግኘት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚስቶች የተለያየ ፅንፍ ይዘው እየተሟገቱ ነው፡፡ አንዳንዶች ዕድገቱ የወረቀት ነው (ተጭበርብሯል) ይላሉ፣ አንዳንዶች ዕድገቱ አለ ግን ብዙሐኑን ስላላማከለ ጥቂቶች ሲመነደጉ ቀሪዎቹ በድህነት አረንቋ ውስጥ ይማቅቃሉ ይላሉ፡፡ እነዚህኞቹ አገሪቱ ያላትን አቅም ሙሉ በሙሉ እያሟጠጠች ሊሆን ስለሚችል ወደፊት ከነጥቂት ባለጸጋዎቿ የምትንኮታኮትበት አካሔድ ነው እያሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቀሪዎቹ የኢሕአዴግ ቲፎዞ ኢኮኖሚስቶች ዕድገቱ የእውነት ነው፣ አገር አማን ነው፣ ገበሬው ሚሊዬነር እየሆነ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡

በክርክሩ መሃል ግን እየተጨፈለቅን ያለነው ብዙሐን ኢትዮጵያውያኖች ዕድገትን በየራሳችን ኑሮ እንተረጉመዋለን፡፡ ኑሮ ዘንድሮ የሁሉም ነገር ዋጋ የሚጨምርበት ነገር ግን ገቢያችን አምናና ካቻምና ከነበረው ፈቀቅ የማይልበት ነው፡፡ በአምና የገቢ መጠን የዘንድሮን ኑሮ እንዲኖር የተገደደ ዜጋ ስለ አንድ አገር ምጣኔያ ሃብታዊ ዕድገት የሚኖረውን ግንዛቤ ያህል ብዙሐኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም አለው፡፡  

ምከንያቶቹን ምን በላቸው?
እኔ በግሌ ለዓመታት ወደውጪ መውጣትን (ስደትን) በመደገፍ እና በመቃወም መካከል ስወዛወዝ የከረምኩ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተቃውሞዬ ፀንቻለሁ፡፡ ይሄንን አቋሜን ለሰዎች ሳቀርብ ‹‹እኔ ከአገሬ መውጣት አልፈልግም፥ ምክንያቱም…›› እያልኩ የማስቀምጣቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡ (ኩራት በአገር ነው፣ እዚያ ሂጄ የምሰራውን እዚህ እበለጽግበታለሁ፣ ምናምን….) እንዲያም ሆኖ አሁን ግን ሁሉም ምክንያቶች አልቀው ‹‹ምክንያቱም›› ካልኩ በኋላ ዝምታ ሁኗል መልሴ!

‹‹ኩራት በአገር ነው›› የሚለው ቃል አፈ ታሪክ ሊሆን እየተቃረበ ይመስለኛል፡፡ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ብሎም በመብት እና ግዴታ ለመንቀሳቀስ ዛሬ በኢትዮጵያ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አባልነት፣ ‹እንትንነት› ወይም ደጋፊነት አንደኛ ዜግነት ነው፡፡ (‹‹’ሰዎች’ ሁሉ እኩል ናቸው፤ አንዳንድ ‘ሰዎች’ ግን ከሌሎቹ የበለጠ እኩል ናቸው›› እንዳለው ጆርጅ ኦርዌል በሽሙጥ!) በሁለተኛ ዜግነት ደግሞ ኩራት የለም፡፡

‹‹እዚያ ሂጄ የምሰራውን እዚህ ሰርቼ እበለፅግበታለሁ›› የሚለው አባባልም ቢሆን እያለፈበት ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት እዚህ የሥራ ዕድሉ የለም፤ ሁለተኛው ምክንያት ሥራው ቢኖርም ሠርቶ መበልፀግ ቀርቶ በልቶ ማደርም እየከበደ ነው፡፡ በየእለቱ የገንዘባችን የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ እና የመንግስታችን ፖሊሲ ገበያውንና አቅርቦቱን እያመሰው ነው፡፡ ስለዚህ ይህም አባባል አገር ውስጥ ለመቆየት ምክንያት አይሆንም፡፡

አሁን እጄ ላይ ቀረችኝ የምላት ምክንያት አንድ ናት፡፡ እሷም ‹‹ቢደላኝም፣ ባይደላኝም በዙሪያዬ የምወዳቸውና የሚወዱኝ ጓደኞችና ቤተሰቦች አሉኝ፡፡ እነሱ እስካሉ ድረስ ከአገሬ ሌላ የተሻለ ስፍራ የለኝም›› የምትል ምክንያት ናት፡፡ ‹‹ለሞትም ቢሆን ባገር ይሻላል›› እንዲሉ!

ዕድሜ ክብርና ኩራት
በሌላ በኩል ግን የማይሸሹት ዕዳ አለ፡፡ ዕድሜ፡፡ ዕድሜ ሰውን ቆሞ አይጠብቀውም፡፡ ከአሁን፣ አሁን የአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ተለውጦ እኔም ሰርቼ የማድግበት ጊዜ ይመጣል እያሉ መጠበቁ ደግ ነው፡፡ ግን እስከመቼ?

ተስፈኛ መሆን እንችላለን፡፡ ተስፈኝነት ግን እውነታውን አይለውጠውም፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያም እና መለስ በድምሩ 37 ዓመታት ገዝተውናል፡፡ በሁለቱም አመራሮች የአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ከድጡ ወደማጡ እየተንሸራተተ ሄደ እንጂ እመርታ አላሳየም፡፡ እነዚህ እውነታዎች ይለወጣሉ እያለ ተስፋ ያደረገ ሰው ቢኖር ከዕድሜው ላይ 37 ዓመታትን ቆርጦ እንደጣለ ይቆጠራል፡፡ አማካይ ዕድሜ 47 ዓመት በሆነባት አገር 37 ዓመታትን እንደዋዛ ማባከን አያዋጣም፡፡

ስለዚህ ለኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ላለመውጣት ክብርና ኩራት ምክንያት አይሆኑም፤ ለምን ቢሉ…. ዕድሜ ክብርና ኩራት አይገባውም፤ ዝም ብሎ ይጋልባል እንጂ!

ይህንን ጽሁፍ መለስ ብዬ ስቃኘው የሐዘን እንጉርጉሮ ይመስላል፡፡ ነውም፡፡ እስከዛሬ የኢትዮጵያውያንን ፍልሰት በተመለከተ ወገቤን ይዤ ተከራክሬያለሁ፡፡ ተገቢ አይደለም በማለት፡፡ ዛሬ ድንገት ተነስቼ ተገቢ ነው ብዬ ጮክ ብዬ ለመከራከር ሞራላዊ ብቃት የለኝም፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊ ግለሰቦች ነባራዊውን እውነታ በግላቸው መለወጥ ላይችሉ ነገር፥ የራሳቸውንም የማሕበረሰቡንም ጊዜ ከሚያባክኑ በመሰደድ ዕድላቸውን ቢሞክሩ የሚያስሞግሳቸው እንኳን ባይሆን የሚያስወቅሳቸው ሊሆን አይገባም ባይ ሁኛለሁ፡፡

ለዚህም ነው ሰሞኑን ዲቪ የሚሞሉ ሰዎችን ሳይ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለምን ዲቪ አይሞሉ?›› የምለው፡፡

No comments:

Post a Comment