Pages

Friday, November 4, 2011

ኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ በኋላ፤ ሰጥቶ የመንጠቅ ዘመነ መንግስት

From Addis Ababa, Ethiopia
በርግጥ ይሄ የአገሪቱ ቅርጽም ኢሕአዴግ አመጣሽ ነው:: 
ስጦታ ወይስ ንፍገት የሚለውን ግን እናንተው ፍረዱ::
ኢሕአዴግ (ሕወሓት) ከአሸባሪነት ወደ አሸባሪ ሰያሚነት በተሸጋገረባቸው ሃያ ዓመታት ውስጥ ብዙ ተግባራትን መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ ተግባራቱ፤ ገሚሱ ለፓርቲው ሕልውና፣ ጥቂቱ ለአገሪቱ ሕልውና (ፓርቲው ያለርሷ አይኖርምና)፣ ቀሪው ደግሞ እንዲሁ ማድረግ ደስ ሲለው ያደረጋቸው ነገሮች ናቸው፡፡ አሁን የምጽፈውም ለኢትዮጵያ የትኞቹ ፌሽታ፣ የትኞቹ መዐት ይዘው መጡ የሚለውን ለማስታወስ ያክል ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ ስጦታ ውሃ በወንፊት መሆኑን የታዘብኩ ስለመሰለኝ ነው፡፡

ስጦታ
በ20 ዓመታት ውስጥ የመንግስት ኃላፊነትን (በጉልበቱም ቢሆን) ከወሰደ በኋላ አንዳንድ ለውጦችን አምጥቷል፡፡ ሆኖም የመጡትን ለውጦች ካየናቸው አብዛኛዎቹ የተፈፀሙት በመጀመሪያው አምስት ዓመታት ብቻ መሆኑ ያስገርመናል፡፡ ሆኖም እዚህ ስጦታ እያልኩ የምዘረዝራቸውን ነገሮች ሁሉ መልሶ እንዴት እንደሚወስዳቸው ወረድ ብለን፤ በሌላ ንዑስ ርዕስ እንመለከተዋለን፡፡
  • ግንቦት 13፤ 1983 ‹‹ብሶት የወለደው ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን›› ቤተ መንግስት ‹‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም›› ሲል ተቆጣጠረው፡፡ ይህም በወታደራዊው መንግስት (ዘመነ መንግስት) በመንግስታዊ ጭቆና፣ በጦርነትና በኢኮኖሚ ድቀት ስትታመስ ለከረመችው ኢትዮጵያ መልካም ዜና ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋን በብዙዎች ዘንድ አኖረ፤
  • ሕዳር 29፤ 1987 የፕሬስ፣ የገበያና የመደራጀት ነፃነትን ከብሔሮች መገንጠል ጋር የሚያካትተው ሕገ-መንግስት ፀደቀ፤ ይህም ለኢትዮጵያ መፃዴሞክራሲያዊነት ተስፋ ጫረ፤
  • ከግንቦት እስከ ሰኔ 1987 ድረስ ምንም እንኳን ዋነኛ ተወዳዳሪ የተሰኘው ኦነግና ሌሎችም ከምርጫው በጫና ብዛት ራሳቸውን ቢያገሉም፣ ‹‹ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት የመጀመሪያው›› ኢትዮጵያዊ ምርጫ ተካሔደ፤
ንፍገት
የኢሕአዴግ መንግስት መንፈግም ይችልበታል፡፡ ምንም እንኳን አቶ ልደቱ አያሌው አንዴ እንደገለፁት ሕገ መንግስቱ ‹‹አንዴ ንፉግ፣ አንዴ ቸር›› ቢሆንም ‹‹በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር›› እጁን የማይፈታባቸው ንፍገቶች፤ ወይም በሌላ አነጋገር የኢሕአዴግ መሪዎች የሚከተሉትን ጉዳዮች ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ከመቸር ‹‹ፀጉራቸውን መንጨት›› ይቀላቸዋል፡፡
  • ሚያዝያ 1985 የዛሬዎቹ የኢትዮጵያና ኤርትራ ገዢዎች እንደነገሩን ‹‹በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው›› ኤርትራ ተገነጠለች፤ የኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነትም ቻው፣ ቻው ተባለ፤
  • በዘመነ ‹‹መሬት ላራሹ›› እንቅስቃሴ ተፀንሶ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የመሬት ባለቤትነት ጉዳይም በመንግስት ስር እንዲሆን በሕገመንግስቱ ተደነገገ፤
  • የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት (በመለስ አጠራር ‹‹ገንዘብ ማተሚያው ማሽን››) እና ሌሎችም ጥቂት አትራፊ ኩባንያዎች ለነፃ ገበያው የተነፈጉና በመንግስት ቅኝ ተገዢነት እንዲተዳደሩ ተደነገገ፤
  • የቀበሌ መታወቂያዎች ›ዜግነት› የሚለውን ‹ብሔር› በሚል እንዲተኩ ተደረገ፤ በዚህና መሰል ድርጊቶችም የዜግነት (የብሔራዊ ስሜት) ጉዳይ እንዲመናመን ሆኖ ተነፈገ፡፡
ሰጥቶ መንጠቅ
ኢሕአዴግ መጀመሪያ ወይ ዴሞክራሲያዊ ነበር ወይም ደግሞ የፈለገውን ያህል ነፃነት ብሰጣቸው የትም አይደርሱም ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን እኔ በዚህ ጽሁፍ ለኢሕአዴግ ልራራለት እንኳን ብፈልግ ድርጊቱ አይፈቅድልኝምና እላይ የነገርኳችሁን ‹ስጦታ› በሙሉ መልሶ እንደወሰዳቸው ስነግራችሁ ‹‹መርዶ ነጋሪነት›› እየተሰማኝ ነው፡፡
  • ሰኔ 1990 ለዘላቂ ሠላም መገነጣጠላቸው ይበጃል የተባለላቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ ‹‹በድንበር ምክንያት›› ተጣሉ፤
  • ታሕሳስ 1992 የወቅቱ ባሕልና ማስታወቂያ ሚኒስቴርር 10,000 ብር የባንክ ተቀማጭ የሌላቸውን 12 ጋዜጦች ፈቃዳቸውን ሊያድሱ ሲሉ ዘጋቸው፤
  • ሕዳር 1995 የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማሕበር በመንግስት ታገደ፡፡ እገዳው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢነሳም የመንግስት ኃይሎች በፈቃዳቸው/በጉልበታቸው የራሳቸውን የቦርድ አባላት ተክተውበታል፤
  • ግንቦት 1997 ‹‹የስኒ ማዕበል›› በሚል ተንቀው የነበሩት ተቃዋሚዎች እና ኢሕአዴግ በምርጫ ውጤት መስማማት አቃታቸው (ሁለቱም አሸናፊዎች ነን አሉ) ይህንን ተከትሎ ለተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ (ተቃውሞው በኢሕአዴግ ላይ ነበር) ተጠያቂዎች ናችሁ በማለት ሕዳር 1998 ከ100 በላይ የተቃዋሚ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን አሰረ፡፡ (የኋላ ኋላ አገርን በመክዳትና ሕገመንግስቱን በኃይል ለመናድ በሚል ከሷቸዋል)፤
  • ጥር 1998 መንግስት በሕዳሩ አመጽ ተሳትፋችኋል በሚል 11,000 ሰዎችን በማሰር ‹‹አደገኛ ቦዘኔዎችን›› የመቆጣጠር አቅሙን አሳየ፡፡
  • ጥር 2001 የኢትዮጵያ መንግስት የውጪ መያዶች (እና የአገር ውስጦቹም በተዘዋዋሪ) ሰብአዊ መብት ላይ እንዳይሰሩ የሚያደርግ ሕግ አወጣ፡፡ የሕዝብን ድምጽ እና የማወቅ መብት የማፈኑን ስራ በትጋት ቀጠለበት፡፡
  • ጋዜጠኞች በማስፈራሪያ ብዛት አገር እየለቀቁ መሰደድ ጀመሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ቪኦኤ ‹‹የተቃዋሚዎች ልሳን›› ሆነ ተብሎ ተዘጋ፣ በርካታ ድረአምባዎች (websites) ታፈኑ፤ ባጭሩ በሕገመንግስቱ የተፈቀደው የመናገር ነፃነት ስለኢሕአዴግ መልካም ነገሮች ብቻ ሆነ፡፡
  • ሕዝቦች በቢሮክራሲ ከለላ ምንም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ ተደረገ፤
  • በአራተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ፤ ግንቦት 2002 ኢሕአዴግ 99.6 በመቶ በሆነ ድምጽ ምርጫ በማሸነፍ ፓርላማውን ከተቃዋሚዎች ነፃ አወጣ፤
  • ጋዜጠኞችና የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በ‹‹አሸባሪነት እየተጠረጠሩ›› መታሰር ጀመሩ
  • እያለ፣ እያለ ይቀጥላል…
እናም የኢሕአዴግ መንግስት ጉዳይ ከዚህ በፊት ከጓደኛዬ ሰምቼ እንዳወራሁት ‹‹አምስት ብር እየሰጡ፤ አሥር ብር መንጠቅ ነው፡፡››

1 comment:

  1. ይሁና! ካንተ ባላውቅም..ሰጥቶ፤ ሰጠ፤…የሚሉት ቃላት ለኢሕአዲግ የሚስማማው አይመስለኝም ነበር፡፡ ለመንጠቅ፤ መስጠት ያለበት አስመሰልከው እኮ…በእኔ አስተያየት ነገሩ 5 ብር ሰጥቶ 10 ወሰደ ሳይሆን፤ 5 ብር እነጥቃለሁ ብሎ 10 ብር ነጠቀ ነው፡፡ ይፈቀድልኝና ላስረዳ፤-ኤርትራን ሊገነጥል ፈልጎ፤ ሌሎቹም እንዲገነጠሉ መንገድ አበጀ፡፡ ደርግን ሊገድል መጥቶ፤ ሕዝቡንም ገደለ፤ አማራን ሊበቀል መጥቶ ጉራጌንም ተበቀለ፤ ለአሜሪካ ሊታዘዝ ፈልጎ፤ ለቻይናም ታዘዘ፡፡ አስር ዓመት ሊገዛ ፈልጎ፤ ለዘለዓለም ገዛ፡፡….ዛሬ ጨለምለምተኛ ሆንኩ አይደል፡፡

    ReplyDelete