Pages

Monday, November 7, 2011

In T1me - ጊዜ ገንዘብ (ገንዘብ ጊዜ) ቢሆን ኖሮ!

From Addis Ababa, Ethiopia
“Occupy Wall Street” በሚል መፈክር አንድ በመቶ የሚሆኑ ባለፀጎች የሚመሩትን የኢኮኖሚ ፖለቲካ 99 በመቶዎቹ ሊንዱት እየተፍጨረጨሩ ባለበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ In Time የተሰኘ ፊልም ወጥቷል፡፡ ፊልሙ ጊዜን መገበያያ ገንዘብ አድርጎ አምጥቶታል፡፡ መገበያያ ብቻ ግን አይደለም፤ ሕይወትም ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ያለው ሰው ሃብታም፣ ትንሽ ጊዜ ያለው ሰው ደግሞ ድሃ ነው፡፡ ድሃው ቶሎ ይሞታል፣ ሃብታሙ ግን ዘላለም የመኖርም ዕድል አለው - በስህተት ካልሞተ፡፡

የፊልሙ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሃብታቸውና ሕይወታቸው (ጊዜ) እጃቸው ላይ ታትሞ/በተፈጥሮ መሆኑ ነው/ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ማኪያቶ ለመጠጣት 5 ደቂቃ ሲከፍሉ፣ መኪና ለመግዛት ደግሞ ዓመታትን ያወጣሉ፡፡ ስጦታ ይሰጣጣሉ፣ ይሰራረቃሉ፣ ያተርፋሉ ይከስራሉ፡፡ ብዙዎቹ ድሆች ከሰዓታት የበለጠ ስለሌላቸው ሕይወታቸውን ለማሳደር ሲሉ ይዋከባሉ፡፡ ሃብታሞቹ ደግሞ ከእጃቸው ተርፎ ማዕከላዊ ቁጥጥር ሲስተም ውስጥ የሚያጠራቅሙት ዓመታት አላቸው፡፡

በፊልሙ ውስጥ ፖሊስ - ጊዜ ጠባቂ፣ ድንበር - የጊዜ ዞን፣ ባንክ - የጊዜ ማበደሪያ በመባል ይታወቃል፡፡

In Time ሊያስተላልፍ የሞከረው ነገር ሃብታሞች ብዙ ገንዘብ ባካበቱ ቁጥር የሚያካብቱት ከድሃው የተቆነጣጠረ መሆኑን ነው፡፡ ገንዘብ ዕድሜን ቢቀጥል ኖሮ (በርግጥም ይቀጥላል) እነርሱ እየኖሩ ድሃው ይሞታል እንደማለትም ነው፡፡ የፊልሙ ዋና ገፀ ባሕርይ (ጀስቲን ቲምበርሌክ ይተውነዋል) ጊዜን ከሃብታሞቹ እየዘረፈ ለድሆቹ ሲያከፋፍል ይታያል፡፡ ነገርዬው ሶሺያሊዝም ይመስላል፡፡ ዘመናችን ሶሺያሊዝምን እየናፈቀ ይሆን የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ነፃ ገበያ ብሎ ነገር አበቃለት ይሆን?

አንድ ለዘጠና ዘጠኝ
አንድ ለዘጠናዘጠኝ የሚባለው የመቶኛ ንጽጽር አሜሪካ ውስጥ እውን ይሆናል፡፡ አፍሪካ/ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ኢኮኖሚውን መምራት የሚችሉ ባለፀጎች ቁጥር አንድ በመቶ መድረስ አይችሉም - በጣም ጥቂት በመሆናቸው ንጽጽሩ ከዚያም በላይ የሰፋ ነው፡፡ እስኪ የትውልደ ኢትዮጵያዊውን ቢሊዬነር (አል አሙዲን) ብር እንዘርዝርላቸው እና ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት ጋር እናወዳድረው፡፡

አል አሙዲን ካላቸው 12 ቢሊዬን ዶላር (204 ቢሊዮን ብር ባሁኑ ምንዛሬ) ላይ ሳይጨምሩበት ሳይቀንሱበት በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ብር እያጠፉ ቢኖሩ ከዛሬ ጀምሮ ለመጪዎቹ 559 ዓመታት መኖር ይችላሉ፡፡ 99 በመቶ የሚልቀው ድሃ ግን በቀን አንድ ዶላር ማግኘት አቅቶት ይዋትታል፡፡ በአደጉት አገራት የተነሳው ቀውስ ይህን መሰሉን እውነታ ለመቀየር ጓጉቷል - ግን የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ ለምን?

ሰባት ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ዓለማችን አንድ በመቶ ባለጸጎች ብቻ የሚጠቀሙባት ባትሆን መልካም ነበር - ሚዛናዊም አይመስልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ መራር እውነት በስተጀርባ አንድ በመቶ የሚሆኑት ‹‹ዕድለኞች›› ምንም እንኳን በመቶኛ ሲሰላ ከድሆቹ ያነሰ ግብር ቢከፍሉም፣ በኑሮ ሲሰላ ደግሞ በልተው ከሚተርፋቸው ጥቂቱን ብቻ ቢሰጡም ዓለማችን የቆመችው ግን በነርሱው የማይናቅ ድጋፍ ነው፡፡ የምናያቸው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች የተገነቡት፣ እንደዘንዶ የሚተጣጠፉት አውራጎዳናዎች የተዘረጉት፣ በርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ያገኙት በእነ ማይክሮሶፍት፣ በእነ አፕል፣ በእነ ዎል ማርት እና በእነማክዶናልድ ፈጠራና ገንዘብ ነው፡፡

በርግጥ እነዚህ ትልልቆቹ መሰረታቸውን የጣሉት በትንንሾቹ ዜጎች ላይ ቢሆንም ሁሉንም ከላይ ሁኖ ለሚመለከተው መንግስት ሥራ ፈጣሪዎችን ‹‹እናንተ አናሳ (minority) ናችሁ፤ ገደል ግቡ!›› ለማለት የሚያስደፍረው አይሆንም፡፡ ወይም በቀላል አማርኛ ‹‹እናንተ ለፍታችሁ ያፈራችሁትን ሃብት አከፋፍላችሁ - ከቀሪው ሕዝብ ጋር እኩል ተቸገሩ ወይም ኑሩ›› ሊባሉ አይችሉም፡፡ በአጭሩ አንድ በመቶ የተገመቱት ባለፀጎች ከብዙሐኑ የበለጠ መደመጣቸው የግድ ነው፡፡ እንዲያ ከሆነ ከሰው በተለየ ጠንክሮ መሥራት ለምን ያስፈልጋል?

የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝቦች ድህነት
አገራት (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በኢኮኖሚ አደግን እያሉ ሕዝቦቻቸው ግን ወደባሰ የድህነት አዘቅት ሲወርዱ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት GDP ዕድገት ሁለት ዲጂት አስመዝግቢያለሁ ሲል ስምነት ዓመት ሞላው፡፡ ግለሰቦች ግን እየደኸዩ ነው፡፡

የሕዝቦችን (የግለሰቦችን) የኑሮ ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ የሚገልፁት UNDP – ዓመታዊ Human Development Index (HDI) እና Legatum Institute – World Prosperity Index ናቸው፡፡ ሁለቱም 2011 ኢትዮጵያን 174/187 እና 108/110 ሰጥተዋታል፡፡

Human Development Index (of 187 countries)
  • HDI – 174th
  • Life expectancy at birth – 59.3 years
  • Education index – 0.237
  • GNI per capita in PPP terms - $971
  • Inequality-adjusted HDI – 0.247
  • Multidimensional poverty index – 0.562%
  • Adjusted net savings (of GNI) – 8.3%

World Prosperity Index (0f 110 countries)
  • Economy – 104th (last year: 106th)
  • Entrepreneurship and Opportunity – 108th (last year: 109th)
  • Governance – 101st (last year: 99th)
  • Education – 107th (last year: 108th)
  • Health – 107th (last year: 108th)
  • Safety and Security – 106th (last year: 103rd)
  • Personal freedom – 110th (last year: 93rd)
  • Social capital – 86th (last year: 85th)
  • Total average – 108th (last year: 107th)

HDI 2011 ሆነ Prosperity Indexቁንጮ ውጤት  ያስመዘገበችው ኖርዌይ ናት፡፡ HDI 2011 ውራ የሆነቸው በማዕድን ሃብቷ ብልፅግና የምትታወቀው ኮንጎ ናት፡፡ አሜሪካ በሁለቱም 4 እና 10 ደረጃ አግኝታለች፣ ባለጠንካራ ኢኮኖሚዋ ቻይና ደግሞ 101 እና 52 ሁናለች፡፡ ሆኖም ጥቂት አሜሪካውያን ሲያምፁ፤ ምንም ኢትዮጵያውያን ወይም ቻይናውያን በጎዳና ላይ አለማመፃቸው ሃገራቱ ‹‹አመርቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት›› ስለሚያስመዘግቡ ነው ብሎ ማሰብ መሳለቅ ነው፡፡ እውነታው እነዚህኞቹ ሃብት ብቻ ሳይሆን ነፃነትም ስለሌላቸው ነው፡፡

ማንን እንከተል፤ ቻይናን ወይስ ነፃ ኢኮኖሚ?
ይሄ ምሁራዊ አስተያየት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለሰው በሚገቡት መለኪያዎች መገመት እና መፍረድ የማይቻል አይደለም፡፡

በሁለቱም ኢንዴክሶች ቀዳሚውን ደረጃ የያዙት ሃገራት ነፃ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ ምዕራባውያን ናቸው፡፡ ኖርዌይ - ምንም እንኳን ቅይጥ ኢኮኖሚ ብትከተልም ጠንካራና ግዙፍ የመንግስት ተቋማቶቿ በነፃነት ከሚንቀሳቀሰው የግሉ ዘርፍ ጋር እየተወዳደረ ለዓመታት መዝለቅ የቻለ እና ከሁሉም በላይ ለሕዝቦች ሚዘናዊ የሃብት ክፍፍል ተመራጭ ሆኗል፡፡ በዓለማችን 2ተኛ ደረጃ የተሰጠውን የቻይናን ግዙፍ ኢኮኖሚ የተመለከትን እንደሆነ ግን በሁለቱም ኢንዴክሶች ከአማካይ ስፍራ የተሻለ ሊያገኝ አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያውያን በቁጥር ብቻ ሲታይ የሚያምረውን፣ ለሚዛናዊ የሃብት ክፍፍል ጨርሦ የማይበጀውን የቻይናን ኢኮኖሚ በመከተል ለመንግስት ሚዲያ ፍጆታ ከሚውል ቁጥር የተሻለ የሕይወት ለውጥ እንደማያመጣ በኑሯችን መመስከር ችለናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በገበያው ውስጥ የሚተገብረው የተጋነነ /አንዳንዴም ቅጥ ያጣ/ ጣልቃ ገብነት አደገ ከሚባለው GDP በስተቀር የሃብት ልዩነቱን ፈፅሞ የማይጠብ በሚመስል ክፍተት አራርቆታል፡፡ የብዙሐን ኢትዮጵያውያን የኑሮ መሻሻልን እንደማያመጣ አውቆ የኢኮኖሚ ፖለቲካ ባላንጣዎቹ የሚያቀርቡትን ሐሳብ ማድመጥ አለበት፡፡

መነሻችን ላይ በጠቀስነው ፊልም ውስጥ ሶሻሊዝም መሰል መፍትሔ ቢጠቆምም፤ ለእውነተኛው ዓለም ችግር ግን ሶሻሊዝም መፍትሄ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል መቶ በመቶ ነፃ ገበያ በየትኛውም ዓለም ሊመሰረት አይችልም፡፡ ስለዚህ ተገቢና በጥናት ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ቁጥጥር የሚደረግበት ነፃ ገበያ ብቸኛው መፍትሄ ነው - እላለሁ፡፡ ዕውቀቱ ያለው ተጨማሪ ሐሳብ ይሰንዝርበት፡፡

No comments:

Post a Comment