Pages

Thursday, October 20, 2011

“ደረሰኝ ሳይቀበሉ፥ ሒሳብ አይክፈሉ”

ሰሞኑን ጉምሩክ ከሚሰሩ ሰዎች የሰማሁት ዜና የተለመደ ዓይነት ቢሆንም፥ እንደተለመደው ከመገረም አልዳንኩም፡፡ ጉምሩክ የላካቸው አሥር ጥንዶች አሥር ስጋ ቤቶች ውስጥ ገብተው ቁርጥ እና ጥብሳቸውን ከበሉ በኋላ ከአሥሩ ስጋ ነጋዴዎች አንዱ ብቻ ደረሰኝ ሲያቀርብ ቀሪዎቹ ዘጠኙ ያለደረሰኝ ሒሳብ በመቀበል ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ስታትስቲክስ ውሸታም ነው ቢባልም፣ በዚህ ስሌት እኮ 90 በመቶ የሚሆኑት የሥጋ ነጋዴዎች ታክስ ያጭበረብራሉ ማለት ነው፡፡

ይህንን ዜና ስትሰሙ ለማን አዘናችሁ፣ ወይም በማን አዘናችሁ? ነጋዴዎቹ ምነው ቀድመው መረጃ ቢያገኙ ወይም ምን ዓይነት መንግስት ነው ያለው ብላችሁ ከተማረራችሁ፥ ለፍርድ የቸኮላችሁ ይመስለኛል፡፡ ነጋዴዎቹስ ቢሆኑ ለሕጉ ለምን አይገዙም?

በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ያልተመለሱ ሕዝባዊና መንግስታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሁሉም በእኩል ደረጃ አሳሳቢዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ አንዱ የሕግ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው በሕግ የበላይነት ጉዳይ ሁላችንም እንስማማለን፡፡ ልዩነታችን በአተገባበሩ ላይ ነው፡፡ ሌላው በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ጥያቄ የሕግ የበላይነት ከማን የሚለው ነው - ከሕዝቡ፣ ከመንግስት ወይስ ከሁለቱም?


የሕግ የበላይነት በየፈርጁ
የመንግስት ነጠላ ዜማ ‹‹ሕገ መንግሰቱን በኃይል ለመናድ›› የምትለዋ ሐረግ ናት፡፡ እስከዛሬ እኛ (ተቃዋሚዎች) ከፖለቲካ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች የምንላቸውን ባሰረ ቁጥር የሚጠቀምባት ቃል ይህችው ‹‹ሕገ መንግሰቱን በኃይል ለመናድ›› የምትል ክስ ናት፡፡ የሚታሰሩት ሰዎች በሙሉ በሕገ መንግሰቱ ላይ እንዲህ ጠላት የሆኑበት ምክንያት ግልፅ ባይሆንም፡፡

በእኔ አመለካከት ‹‹ሕገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ›› ከሚራወጡ ሰዎች (ሥራዬ ብለው የሚራወጡ ካሉ ማለቴ ነው) አንዱ ራሱ መንግስታችን ነው፡፡ የፀረ ሙስና ክስ በግልፅ በሚሞስኑ ሰዎች ላይ ሲመሰረት አይተን አናውቅም፣ ይልቁንም ሕጉ ወደ ባለስልጣኖቹ የሚያነጣጥረው ባለስልጣናቱ ከገዢው ፓርቲ አመለካከት ያፈነገጠ ሐሳብ ሲያመጡ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ እድሜ ለግምገማ፡፡ ግምገማ ማለት ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት፣ ንብረት እና ጊዜ አላግባብ የተጠቀሙ የገዢው ፓርቲ አባላት ንስሐ ገብተውና ለፓርቲያቸው ያላቸውን ታማኝነት አጠናክረው እንዲነፁ የሚረጩት ሂፆጵ ነው፡፡ ስለዚህ ለነርሱ ሲሆን ሕግ የበላይ አይደለም፡፡

በዚሁ ስሌት የኢሕአዴግ አባል እና ደጋፊ የሆኑ ነጋዴዎች የሚሰሩት ሕጋዊ ጥሰት በተመሳሳይ መንገድ የማይማር መሆኑን ማረጋገጫ የለንም፡፡ በርግጥ ከሚናፈሱ ወሬዎች (ከወሬም በላይ የጠነከሩ መረጃዎችን) እያጣቀስን ማውራት እንችል ነበር - ሰበብ ፈልገው (ካሻቸው አዲስ ሕግ አውጥተውም ቢሆን) ያስሩናል እንጂ፡፡

ኢሕአዴግ አንድ ለማጥቃት የሚፈልገው ቡድን ሲኖር (ለምሳሌ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማሕበራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንበላቸው…) አዲስ ሕግ ያወጣል፡፡ ሕጉ ከሕገመንግስቱ ጋር የሚጣረስ ነገር ቢኖረውም ግድ አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር የልማታዊ መንግስት ቅርጽ ይዞ እንዲሄድ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንኳን መንግስት ሕገ መንግስቱ ራሱ በየጊዜው ከሚፈለፈሉት ሕግጋት በላይ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብም ከዚህ ትችት አንፃር ነፃ ነው ለማለት ይከብደኛል፡፡ በርግጥ ሕዝባችን ባሕላዊነቱ ከዘመናዊነቱ የሚበልጥበት፣ ከተፃፈ ሕግ ይልቅ በቡና ላይ እና ጠጅ ቤት የተወራ ወሬ የሚያምንበት ዝንባሌ ይታያል፡፡ ሕዝባችን ሕግ ሲጥስ በአብዛኛው ካለማወቅ አልፎ፣ አልፎ በሕጉ አለማመን እና ጥቂቶች ለክፋት ነው፡፡ የሕዝባችን አለማወቅ በሁለት ይከፈላል - አንደኛው ሕጉን ከናካቴው አለማወቅ፣ ሌላኛው ደግሞ ጥቅሙን አለማወቅ ነው፡፡

በሕግ አለማመን ለአንድ ሃገር ትልቅ በሽታ ነው፡፡ የሁሉ ነገር ማሰሪያ ሕግ ነው፡፡ በሕግ አለማመን የሚከሰተው በርግጥ በብዙ ምክንያቶች እንደሆነ ቢታመንም በዋነኝነት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ላይ የሚወጡ መንግስታት ባሉባቸው አገራት ውስጥ የሚበረታ በሽታ ነው፡፡ ሕዝቦች በሕግ ለማመን በሕጉ መሰረት መንግስታት ሲለዋወጡ፣ ባለስልጣናት ሲሻሩ እና ሲሾሙ በማየት በረዥም ጊዜ ሒደት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ስላላዩ በሕግ ባያምኑ አይፈረድባቸውም ማለትም እንችላለን፡፡
ስለሆነም በኢትዮጵያ ሕግ መጣስም ሆነ ሕግ ሲጣስ እያዩ እንደዋዛ ማለፍ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ነገሩ ‹‹በኔ ካልደረሰ›› ቢመስልም፤ በያንዳንዳችን መድረሱ የማይቀር ነገር ነው፡፡ አንዳንዴ ሕጉን የሚጥሰው ‹‹ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ›› በሚለው ብሒላችን ልንጋፋው የምንፈራው ዓይነት ሰው ሊሆን ይችላል፣ አንዳንዴ ሕጉን የሚጥሰው በጣም የምንቀርበው ወዳጃችን ወይም የቤተሰባችን አባል ይሆናል፣ ወይም ደግሞ ሌላ ጊዜ እኛው ራሳችን እንሆናለን፡፡

መፍትሄው የመንግስትን ቀናነትና የረዥም ጊዜ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ በርግጥ በሕግ የበላይነት ጉዳይ የሕዝቦችም ፈቃደኝነት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝቦች ሕጉን ያወጣውን መንግስት ወደዱትም ጠሉትም፣ ለሕግ የበላይነት ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ የሕግ አውጪውን አካል መታገል ወይም ሕጉን መቀየር ቢፈልጉ እንኳን በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ ሁነው መታገል አለባቸው፡፡ ሕዝቦች በሕግ የበላይነት ካላመኑና ካላከበሩት ከመንግስታቸው ሕግ አክባሪነትን መጠበቃቸው የዋህነት ነው፡፡ ሕዝቦች ሕጋዊ ግዴታቸውን አክብረው ሲንቀሳቀሱ ከሕግ አስከባሪው መንግስ መብታቸውን የመጠየቅ ሞራላዊ ብቃት ይኖራቸዋል፡፡

የታክስ ሕግና የነጋዴዎች አኩኩሉ
የአገራችን ነጋዴዎች በታክስ ሲማረሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ የወር ደሞዝተኞች ከገቢያቸው የሚቆረጠውን ከ10 እሰከ 35 በመቶ የሚዘልቅ ታክስ በማስታወስ የነጋዴዎች ሮሮ ቀልድ ነው ባዮች ናቸው፡፡ በርግጥም ነጋዴዎች (ሁሉም ማለት ባንችልም ብዙዎቹ) የሚከፍሉት ግብር ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን ሳይሆን በጣም ጥቂት ነው፡፡

እንዴት?
‹ካሽ ሬጂስተር› ከመጣ ወዲህ ጥቂት የማይባሉ የንግድ ተቋማት ገቢያቸውን ለመደበቅ ቢቸገሩም ሁሉም ግን በአግባቡ እያስመዘገቡ ነው ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ እንዲያውም የማሽኑ መኖር ገቢያቸውን አሳንሰው ሲናገሩ ለመታመን ያበቃቸው ነጋዴዎች አሉ፡፡

አንዳንድ ነጋዴዎች ማሽኑን የሚጠቀሙት ለሚጠረጥሩት ሸማች ብቻ ሲሆን፣ ሲጠራጠሩ እንዲያውም ‹‹እሱ እቃ የለንም›› ብለው ሸማቹን መመለስ ይቀናቸዋል፡፡ በተለይ አከፋፋዮቹ ለቸርቻሪ ነጋዴዎች የሚሸጡት ደንበኞቻቸውን ብቻ እየመረጡ ነው፡፡ ማታ፣ ማታ ለይስሙላ ሪፖርት ማድረግ ስለሚኖርባቸው ጥቂት ደረሰኞችን የውሸት እየቆረጡ ይጥላሉ፡፡ አከፋፋዮቹ ይህንን የሚያደርጉት አንድም ታክስ ለመከፈል ፈቃደኛ ካልሆኑ ተወዳዳሪዎቻቸው ላለማነስ ሲሆን፣ አሊያም ደግሞ የሚሸጡትን ዕቃ ያስገቡት በኮንትሮባንድ ስለሚሆን እና የተሸመተበት ደረሰኝ ስለሌላቸው (በስተመጨረሻ ሒሳብ ማወራረድ ስለማይችሉ) ነው፡፡

ከነዚህኞቹ አከፋፋዮች የሚሸምቱት ቸርቻሪዎችም በበኩላቸው የነርሱኑ መንገድ ይከተላሉ፡፡ ምክንያቱም ያለደረሰኝ የሸመቱትን ዕቃ በተ.እ.ታ (V.A.T.) ቢሸጡ ጉምሩክ የገቢ መጠናቸውን ካየ እና 15 በመቶ የተ.እ.ታ ድርሻውን ከቆረጠ በኋላ ከቀሪው ላይ ሌላኛው 15 በመቶ ቸርቻሪዎቹ ያተረፉት ነው ብሎ በማሰብ የግብር ግምቱን በዚያ መሰረት ይወስናል፡፡ ይህ ነጋዴዎችንም ሕዝቡንም የሚጎዳ ደካማ አሰራር ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ነጋዴዎቹ ከመቶ ብር ላይ 15 ብር እንደሚያተርፉ መገመቱ የተጋነነ ነው፤ በሌላ በኩል ነጋዴዎቹ በዚያ መንገድ እንደሚተመንባቸው ካወቁ ዋጋቸውን በዚያ መሰረት ማስተካከላቸው ስለማይቀር የዋጋ ንረትን ያስከትላል፡፡

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በነጋዴዎችና መንግስት አኩኩሉ መካከል የምትጎዳው አገሪቱ ናት፡፡ አንደኛ ነገር መንግስታችን ተገቢ የታክስ እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት አለበት (በዚህ ረገድ አሁን እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ይመስለኛል)፤ በሌላ በኩል ነጋዴዎች ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን አውቀው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ተቃውሞ የሚኖራቸው እንኳን ከሆነ ግዴታቸውን እየተወጡ ቢቃወሙ ያምርባቸዋል፡፡

ሌላው በኑሮ ውድነት የተሸነፈው ብዙሐኑ ነው፡፡ ብዙሐኑ የዕለት ጉርሱ እንጂ የሃገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አያሳስበውም፡፡ ስለዚህ የተ.እ.ታ. ደረሰኝ ሳይሰጠው ሲቀር የ15 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የተደረገለት ያህል ደስ ይለዋል፡፡ በዚያ ላይ የተቃውሞ ድምፁን የታፈነ እንደመሆኑ ታክስ መክፈል ከገዢው ፓርቲ ጋር የመተባበር ያህል ስሜት ስለሚሰጠው አለመክፈሉ (ታክስ ማጭበርበሩ) የመንፈስ እርካታን ያጎናጽፈዋል እንጂ አያሳፍረውም፡፡ በሌላ በኩል መንግስትም ቢሆን የሕዝብን ገንዘብ ለገዢው ፓርቲ ጥቅም የሚያውልበት በርካታ ገጠመኞች አሉ፡፡ በመንግስት ስራ ላይ ያሉ ካድሬዎቹ የመንግስትን ሃብት ለፓርቲ አገልግሎት ሲጠቀሙ ተዉ ሊላቸው የሚደፍር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሕዝብ ጉሮሮ ተነጥቆና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ተለምኖ በተሰበሰበ ገንዘብ የሚተዳደሩ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የገዢው ፓርቲውን አሸሸ ገዳሜዎች ሳይቀር ስፖንሰር በማድረግ በርካታ ገንዘብ ሲያባክኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡

ስለዚህ ገዢው ፓርቲም ልኩን ይወቅ፤ ሕዝቡም ተገቢውን ግብር ይክፈል፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ ማስተዳደር የምትችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አለቀ፡፡ ለዚህም ነው ርዕሴን ጉምሩክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነጋዴዎች በግልጽ ቦታ እንዲለጥፉት በሚጠይቃቸው ሐረግ እንዲሆን ያደረግኩት፡፡ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ፣ ‹ነግ በኔ ነውና› በታክስ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ይሄ፣ ይሄ ብለው ይንቀሱ እንጂ ‹‹ትክክል አይደለም›› አይበሉን፡፡ ትክክል ምንድን ነው?

No comments:

Post a Comment